በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

Ahmad Gharabli/AFP via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

መንግሥታት በተባበረ ክንድ ለአየር ንብረት ቀውስ መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መንግሥታት በተባበረ ክንድ ለአየር ንብረት ቀውስ መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 እሁድ፣ ኅዳር 20, 2022 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ የተጠናቀቀበት ቀን ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ የተጎዱ አገሮችን በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችል ታሪካዊ ውሳኔ ተላልፏል፤ ሆኖም ብዙዎች ይህ ብቻውን ችግሩን ከሥር መሠረቱ እንደማይፈታው ያምናሉ።

  •   የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኅዳር 19, 2022 እንዲህ ብለው ነበር፦ “የጠፋውንና የተጎዳውን ለመካስ ገንዘብ እንዲመደብ የተላለፈውን ውሳኔ በደስታ እቀበለዋለሁ። ሆኖም ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ግልጽ ነው . . . ፕላኔታችን አሁንም በአደጋ ቀጠና ውስጥ ነች።”

  •   “አውዳሚ የአየር ንብረት ጥፋት አሁንም በዓለማችን ላይ እያንዣበበ ነው።”—ሜሪ ሮቢንሰን፣ የቀድሞ የአየርላንድ ፕሬዚዳንት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የቀድሞ ኮሚሽነር፣ ኅዳር 20, 2022

 በተለይ ወጣቶች የምድራችን የወደፊት ዕጣ በጣም ያሳስባቸዋል። ታዲያ መንግሥታት ተባብረው በመሥራት ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ለመስጠት የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

መንግሥታት በጋራ የሚያደርጉት ጥረት ይሳካ ይሆን?

 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ብዙ ውጤት አያስገኝም። እርግጥ ነው፣ ለአየር ንብረት ቀውስ መፍትሔ ለማምጣት ቅን ዓላማ ይዘው ደፋ ቀና የሚሉ ይኖራሉ፤ ሆኖም አቅማቸው ውስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ሁለት ምክንያቶች ይነግረናል፦

  •   “የተጣመመ ነገር ሊቃና አይችልም።”—መክብብ 1:15

     ምን ማለት ነው? ፍጹም የሆነ መንግሥት የለም፤ ምክንያቱም ሰው ሰውን እንዲያስተዳድር አልተፈጠረም። (ኤርምያስ 10:23) ሁሉም መንግሥታት በጋራ ጥረት ቢያደርጉ እንኳ የዓለምን ችግሮች ለመፍታት አቅማቸው ውስን ነው፤ የፈለገውን ያህል ጥረት ቢያደርጉ አይሳካም።

  •   “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3

     ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎች ራስ ወዳድ ይሆናሉ፤ ዘላቂ ጥቅም ለሚያስገኝ ነገር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ አይሆኑም።

ተስፋ አለ!

 ደስ የሚለው ግን፣ የምድራችን የወደፊት ዕጣ በዓለም መንግሥታት እጅ ላይ አይደለም። አምላክ፣ ብቃት ያለው የዓለም መሪ ሾሟል፤ እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ እንዲህ ይላል፦

  •   “መንግሥትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙ ድንቅ መካሪ፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባትና የሰላም መስፍን ይባላል።”—ኢሳይያስ 9:6 የግርጌ ማስታወሻ

 ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ነው፤ ይህ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመ መስተዳድር ነው። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ ምድራችንን እና ነዋሪዎቿን የሚጠቅሙ ነገሮች ለማድረግ ኃይሉ፣ ጥበቡም ሆነ ፍላጎቱ አለው። (መዝሙር 72:12, 16) እሱ የሚመራው ሰማያዊ መስተዳድር “ምድርን እያጠፉ ያሉትን” ያጠፋል፤ ምድራችንንም ከደረሰባት ጉዳት ይፈውሳታል።—ራእይ 11:18፤ ኢሳይያስ 35:1, 7

 የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ውድመት ዘላቂ መፍትሔ ስለሚገኝበት መንገድ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? “የአየር ንብረት ለውጥ ያጠፋን ይሆን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።