በዓለም ላይ ጥፋት እየመጣ ነው? አፖካሊፕስ ምንድን ነው?
“አፖካሊፕስ” የሚለውን ቃል ስትሰማ ምን ነገር ወደ አእምሮህ ይመጣል? ምናልባት ምድር ላይ ያለውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ የሚያወድም ዓለም አቀፍ ጥፋት ወደ አእምሮህ ይመጣ ይሆናል። አንዳንዶች በዓለም ላይ እንዲህ ዓይነቱ ጥፋት መምጣቱ እንደማይቀር ይሰማቸዋል፤ በተለይ እንደሚከተሉት ያሉ ዜናዎችን ሲያነቡ፦
“የኑክሌር ጦርነት፣ ታስቦበትም ሆነ በስህተት ወይም በቀላል አለመግባባት፣ በእርግጥ በዓለም ላይ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው።”—ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ
“ያለፈው አሥር ዓመት፣ ዓለማችን ታይቶ በማይታወቅ መጠን የተፈጥሮ አደጋዎችን ያስተናገደችበት ነው፤ አውዳሚ አውሎ ነፋሶች፣ ሰደድ እሳት፣ ድርቅ፣ የውቅያኖስ ኮራል መገርጣት፣ ከፍተኛ ሙቀትና የጎርፍ አደጋዎች ተከስተዋል።”—ናሽናል ጂኦግራፊክ
“አፍሪካ ውስጥ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ከነበረው ሁሉ የከፋ ሆኗል።”—ዚ አሶሲዬትድ ፕሬስ
ታዲያ ምድራችን አፖካሊፕስ ወይም የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባታል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ምድራችን ትጠፋለች?
በዓለም ላይ ጥፋት እየመጣ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲናገር “ዓለም” የሚለው ቃል የሚያመለክተው አምላክን የማይፈሩና ራስ ወዳድ የሆኑ የሰው ልጆችን ነው። አምላክ በኖኅ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ “ፈሪሃ አምላክ [በሌላቸው] ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ” ጥፋት ያመጣል።—2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:7
አንደኛ ዮሐንስ 2:17 “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ” ይላል። ይህ ጥቅስ እንደሚያሳየው አምላክ የሚያጠፋው ራሷን ምድርን ሳይሆን በምድር ላይ የሚኖሩ መጥፎ ምኞታቸውን የሚከተሉ ሰዎችን ነው።
የዓለም ፍጻሜ የሚመጣው መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዓለም ፍጻሜ የሚመጣበትን ጊዜ ለይቶ አይነግረንም። (ማቴዎስ 24:36) ሆኖም ፍጻሜው እንደቀረበ ይጠቁመናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሚከተሉት ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል፦
ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ ወረርሽኞችና ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ “በተለያየ ስፍራ” ይከሰታሉ።—ማቴዎስ 24:3, 7, 14፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ ራእይ 6:1-8
አብዛኞቹ ሰዎች ራስ ወዳድ ይሆናሉ። ለምሳሌ “ገንዘብ የሚወዱ፣” “የማያመሰግኑ” እንዲሁም “ራሳቸውን የማይገዙ” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ከ1914 ወዲህ በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር እንደሚስማማና የዓለም ፍጻሜ እንደቀረበ ብዙዎች ይሰማቸዋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት 1914 ምን የሆነበት ዓመት ነው?” እና “‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክት ምንድን ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
“አፖካሊፕስ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ትርጉም ምንድን ነው?
“አፖካሊፕስ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉም “መግለጥ” ወይም “መግፈፍ” ነው። ብዙውን ጊዜ ይሄ ቃል፣ የተሰወረን መረጃ ከመግለጥ ጋር በተያያዘ ይሠራበታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘ጌታ ኢየሱስ መገለጥ [ወይም አፖካሊፕስ]’ ይናገራል፤ ይህም ኢየሱስ ከምድር ላይ ክፋትን ለማስወገድና አምላክን ለሚያመልኩ ሰዎች ወሮታ ለመክፈል በታላቅ ኃይል የሚገለጥበትን ጊዜ ያመለክታል።—2 ተሰሎንቄ 1:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 1:7, 13
የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አፖካሊፕሲስ ወይም ራእይ ተብሎ ይጠራል፤ ይህ ስያሜ የተሰጠው ወደፊት የሚከሰቱ ሁኔታዎችን ስለሚገልጥ ነው። (ራእይ 1:1) ይህ መጽሐፍ ምሥራችና ተስፋ የሚሰጥ መልእክት ይዟል። (ራእይ 1:3) አምላክ ክፋትን ሁሉ እንደሚያስወግድና ምድርን ገነት እንደሚያደርጋት ይጠቁማል። በዚያን ጊዜ ሥቃይ፣ መከራ፣ ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ አይኖርም።—ራእይ 21:3, 4
ስለዚህ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምሩህ ለምን አትጠይቃቸውም?