በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

mustafahacalaki/DigitalVision Vectors via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ሰው ሠራሽ አስተውሎት—በረከት ወይስ እርግማን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰው ሠራሽ አስተውሎት—በረከት ወይስ እርግማን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ያለው አቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም መሪዎች፣ በሳይንቲስቶችና በቴክኖሎጂ ሰዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። እነዚህ ሰዎች፣ መልካም ጎን እንዳለው አምነው ቢቀበሉም አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል።

  •   “ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከዘመናችን ሁነኛ ቴክኖሎጂዎች አንዱ እንደሆነ አይካድም፤ የሰዎችን ሕይወት የማሻሻል ትልቅ አቅም አለው። . . . ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ይህ ቴክኖሎጂ የደቀነብን ስጋቶችም አሉ፤ የደህንነት ስጋቶችን በእጅጉ ሊጨምር፣ የግለሰቦችን መብትና ግላዊነት ሊጋፋ እንዲሁም ማኅበረሰቡ በዲሞክራሲ ላይ ያለውን መተማመን ሊሸረሽር ይችላል።”—ካማላ ሃሪስ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ግንቦት 4, 2023

  •   “ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሕክምናው ዘርፍ ተስፋ ሰጪ መፍትሔዎች እንዳመጣ አይካድም። በሌላ በኩል ግን በሰዎች ጤንነትና ደህንነት ላይ ብዙ ስጋቶች ደቅኗል።”—ቢኤምጄ ግሎባል ኸልዝ በተባለው ጽሑፍ ላይ ግንቦት 9, 2023 የወጣ ርዕስ፤ በዶክተር ፍሬድሪክ ፌደርስፔል የሚመራ ዓለም አቀፍ የሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ቡድን የጻፈው። a

  •   “ሰው ሠራሽ አስተውሎት አሁንም እንኳ የተሳሳተ መረጃ ለማዛመት መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። በቅርቡ የብዙዎችን ሥራ ይነጥቃል የሚል ስጋትም አለ። የኋላ ኋላ ደግሞ፣ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች የሚያሳስባቸው አንዳንዶች እንደሚገልጹት ለሰው ዘር ሕልውና አደጋ ሊፈጥር ይችላል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ግንቦት 1, 2023

 ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደፊት ለበጎ ዓላማ ይውል ይሆን ወይስ ለመጥፎ? ይህን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን ይላል?

የሰው ልጆች የሚሠሯቸው ነገሮች ስጋት የሚፈጥሩት ለምንድን ነው?

 የሰው ልጆች፣ የቴክኖሎጂ ግኝቶቻቸው ለበጎ ዓላማ ብቻ እንደሚውሉ ዋስትና መስጠት አይችሉም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ይነግረናል።

  1.  1. ሰዎች ቅን ዓላማ ይዘው ቢነሱ እንኳ ድርጊታቸው የኋላ ኋላ አስከፊ መዘዝ ይኑረው አይኑረው አስቀድመው ማወቅ አይችሉም።

    •   “ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።”—ምሳሌ 14:12

  2.  2. አንድ የፈጠራ ሰው ከእሱ በኋላ የሚመጡ ሌሎች፣ ሥራውን ለበጎ ዓላማ ይጠቀሙበት ለመጥፎ መቆጣጠር አይችልም።

    •   “[ሥራዬን] ከኋላዬ ለሚመጣው ሰው ትቼው [እሄዳለሁ]። ጥበበኛ ወይም ሞኝ እንደሚሆን የሚያውቅ ማን ነው? ሆኖም ከፀሐይ በታች በድካሜና በጥበቤ ያፈራሁትን ነገር ሁሉ ይወርሰዋል።”—መክብብ 2:18, 19

 የትኛውም የሰው ልጅ ሥራ እነዚህ ስጋቶች ያሉበት በመሆኑ ፈጣሪ የሚሰጠው መመሪያ ያስፈልገናል።

መተማመን የምንችለው በማን ነው?

 ፈጣሪያችን አንድ ዋስትና ሰጥቶናል፤ የሰው ልጆችም ሆኑ እነሱ የፈለሰፉት ማንኛውም ቴክኖሎጂ ምድርን ወይም የሰውን ዘር እንዲያጠፋ ፈጽሞ አይፈቅድም።

  •   “ምድር . . . ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4

  •   “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

 ፈጣሪያችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመሪያ ሰጥቶናል፤ ይህን መመሪያ መከተል ወደፊት ሰላማዊና አስተማማኝ ሕይወት ያስገኝልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት ይቻላል?” እና “የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?” የሚሉትን ርዕሶች አንብብ።

a “ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጅ ጤና እና ሕልውና ላይ የደቀናቸው ስጋቶች” ከተባለው ርዕስ የተወሰደ፤ የጽሑፉ አዘጋጆች፦ ፍሬድሪክ ፌደርስፔል፣ ሩት ሚቼል፣ አሻ አሶካን፣ ካርሎስ ኡማና እና ዴቪድ ማኮይ።