በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

kovop58/stock.adobe.com

ነቅታችሁ ጠብቁ!

በእርግጥ ኦሎምፒክ አንድነት ያመጣ ይሆን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በእርግጥ ኦሎምፒክ አንድነት ያመጣ ይሆን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በ2024 እየተካሄደ ባለው የበጋ ኦሎምፒክ ላይ ከ206 አገሮች የተውጣጡ አትሌቶች ይካፈላሉ፤ ይህን ውድድር ወደ አምስት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንደሚከታተሉት ይገመታል። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የሆኑት ቶማስ ባክ “መላውን ዓለም በሰላም የሚያስተሳስር ክንውን አካል ነን” ብለዋል። አክለውም “የሰው ዘር ብዝሃነትን ተሻግሮ በአንድነትና በሰላም እንዲኖር በሚያበረታታው የኦሎምፒክ መንፈስ እንመራ” በማለት ተናግረዋል።

 በእርግጥ ኦሎምፒክ ብዙዎች የሚመኙትን እንዲህ ያለውን ዓላማ ያሳካ ይሆን? እውነተኛ ሰላምና አንድነት ይመጣ ይሆን?

ሰላምና አንድነት ሊያስገኝ ይችላል?

 የዚህ ዓመት የኦሎምፒክ ውድድር በሰዎች ዘንድ ከስፖርት ያለፈ ትርጉም ተሰጥቶታል። ውድድሮቹ ሰዎችን የሚከፋፍሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል። እነዚህ ጉዳዮች ከሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከዘረኝነት፣ ከሃይማኖታዊ ትችትና ከመድልዎ ጋር የተያያዙ ናቸው።

 እንደ ኦሎምፒክ ያሉ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ብዙዎችን ያዝናናሉ። ሆኖም እነዚህ ክንውኖች ዘላቂ ሰላምና አንድነት ከማምጣት ይልቅ ሰዎችን የሚከፋፍሉ አመለካከቶችና ድርጊቶችም ይንጸባረቁባቸዋል።

 መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች አንድነትን ማስፈን አዳጋች እንዲሆን የሚያደርጉ ባሕርያት እንደሚኖሯቸው አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይበልጥ ለማወቅ “መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ስለሚኖሩ ሰዎች ባሕርይ እና ምግባር ትንቢት ተናግሯል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ዓለም አቀፍ ሰላምና አንድነት​—አስተማማኝ ተስፋ

 መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም አቀፍ ሰላምና አንድነት እንደሚሰፍን አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል። ‘በአምላክ መንግሥት’ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በአንድነት እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል።​—ሉቃስ 4:43፤ ማቴዎስ 6:10

 የዚህ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ዙሪያ ሰላም ያሰፍናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

  •   “ጻድቅ ይለመልማል፤ [ሰላምም] ይበዛል።”​—መዝሙር 72:7

  •   “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ . . . ይታደጋልና። ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”​—መዝሙር 72:12, 14

 በዛሬው ጊዜም እንኳ የኢየሱስ ትምህርቶች በ239 አገራት የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው አድርጓል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን በሰላም መኖርን ተምረዋል። ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ” የሚል ርዕስ ያለውን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት አንብብ።