በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ስላለው ረሃብ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ስላለው ረሃብ ምን ይላል?

 “ከረሃብ ነፃ የሆነ ዓለም።” እነዚህ ቃላት የዓለም መሪዎች የሰው ዘር ዋነኛ ጠላት ከሆነው ከረሃብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ራእይ የሚገልጹ ናቸው፤ መሪዎች ሁሉም ሰው ምግብ እንዲያገኝ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። a ሆኖም ረሃብ ከምድር ገጽ የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በዛሬው ጊዜ ያለው ረሃብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረ ነው

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት በሚጠራው በዘመናችን፣ የምግብ እጥረት እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ለዚህ የምግብ እጥረት ተጠያቂው አምላክ ባይሆንም ይህ ችግር እንደሚከሰት አስቀድሞ አስጠንቅቆናል። (ያዕቆብ 1:13) እስቲ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመልከት።

 “በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል።” (ማቴዎስ 24:7) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ረሃብ በስፋት እንደሚኖር ይጠቁማል። በምግብ ምርትና ስርጭት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎች በቅርቡ የሚከተለውን ሪፖርት አቅርበዋል፦ “ዓለማችን ረሃብን፣ የምግብ እጦትንና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ቢሆንም ችግሩ እየተባባሰ ነው።” b በበርካታ አገሮች የሚኖሩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ማግኘት አይችሉም። የሚያሳዝነው ብዙዎቹ በዚህ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።

 “እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር።” (ራእይ 6:5) በዚህ ትንቢት ላይ ምሳሌያዊው ፈረስና ጋላቢው፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚከሰተውን ረሃብ ያመለክታሉ። c ጋላቢው የያዘው ሚዛን የሚያገለግለው አነስተኛ መጠን ያለው ምግብ መዝኖ ለማከፋፈል ነው። ፈረሰኛው እየጋለበ ሳለ፣ የምግብ ዋጋ በጣም ስለሚጨምር ሰዎች መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ግብአቶችን በቁጠባ እንዲጠቀሙ የሚያስጠነቅቅ ድምፅ ተሰማ። (ራእይ 6:6) ይህ ሁኔታ በዓለማችን ላይ የተከሰተውን የምግብ እጥረት በትክክል የሚያሳይ ነው፤ በዛሬው ጊዜ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ጤናማ ምግብ ማግኘት ወይም መግዛት አዳጋች ሆኖባቸዋል።

ረሃብ የሚወገደው እንዴት ነው?

 ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ፕላኔታችን ለነዋሪዎቿ ከበቂ በላይ ምግብ ታመርታለች። ታዲያ ረሃብ እንዲከሰት ያደረጉት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ d ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ምን እርምጃ እንደሚወስድ ይናገራል?

 ችግሩ፦ መንግሥታት ሰዎችን ለረሃብ እየዳረገ ያለውን ድህነትና የኑሮ ልዩነት ማስወገድ አልቻሉም።

 መፍትሔው፦ ፍጹም ያልሆኑ ሰብዓዊ መንግሥታት ፍጹም በሆነ መስተዳድር ማለትም በአምላክ መንግሥት ይተካሉ። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) በዛሬው ጊዜ ብዙ ድሆች፣ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማግኘት አቅማቸው አይፈቅድም፤ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ግን ሁኔታው የተለየ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና። . . . በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:12, 16

 ችግሩ፦ ጦርነት ብዙ ውድመትና የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከትላል፤ ይህም የምግብ አቅርቦት እንዲገደብ ወይም እንዲቋረጥ ያደርጋል።

 መፍትሔው፦ “[ይሖዋ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል፤ የጦር ሠረገሎችን በእሳት ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:9) አምላክ የጦር መሣሪያዎችንም ሆነ ጦርነት የሚቀሰቅሱ ሰዎችን ያጠፋል። በመሆኑም ሁሉም ሰው ራሱን ለአደጋ ሳያጋልጥ በቀላሉ ምግብ ማግኘት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ይለመልማል፤ [ሰላምም] ይበዛል” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—መዝሙር 72:7

 ችግሩ፦ አስቸጋሪ የአየር ጠባይና የተፈጥሮ አደጋዎች በሰብልና በእንስሳት ላይ ጥፋት ያስከትላሉ።

 መፍትሔው፦ ወደፊት አምላክ የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች በመቆጣጠር ምግብ ለማምረት አመቺ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ] አውሎ ነፋሱ እንዲቆም ያደርጋል፤ የባሕሩም ሞገዶች ጸጥ ይላሉ። . . . በረሃውን ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጭ ያደርጋል። . . . የተራቡ ሰዎችን በዚያ ያኖራል። መሬት ላይ ዘሩ፤ ወይንም ተከሉ፤ መሬቱም ብዙ ምርት ሰጠ።”—መዝሙር 107:29, 35-37

 ችግሩ፦ ስግብግብና ምግባረ ብልሹ የሆኑ ሰዎች ለጤና ጎጂ የሆነ ምግብ ያመርታሉ፤ አሊያም ደግሞ ምግብ፣ ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳይደርስ ያደርጋሉ።

 መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ሐቀኝነት የጎደላቸውንና ምግባረ ብልሹ የሆኑ ሰዎችን በሙሉ ያጠፋል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ኢሳይያስ 61:8) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ አምላክ ሲናገር “ግፍ ለተፈጸመባቸው ፍትሕ ያሰፍናል፤ ለተራቡት ምግብ ይሰጣል” ይላል።—መዝሙር 146:7

 ችግሩ፦ በየዓመቱ ከሚመረተው የዓለም የምግብ አቅርቦት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ይባክናል ወይም በተለያየ መንገድ ይጠፋል።

 መፍትሔው፦ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምግብ አቅርቦት በአግባቡ ለተመጋቢዎች እንዲደርስ ይደረጋል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምግብ እንዳይባክን ጥንቃቄ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ከ5,000 የሚበልጡ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መግቦ ነበር። በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ “ምንም እንዳይባክን የተረፈውን ቁርስራሽ ሁሉ ሰብስቡ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል።—ዮሐንስ 6:5-13

 የአምላክ መንግሥት ለረሃብ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ከሥር መሠረታቸው ስለሚያስወግድ ሁሉም የሰው ልጆች የተትረፈረፈ ጤናማ ምግብ ማግኘት ይችላሉ። (ኢሳይያስ 25:6) የአምላክ መንግሥት እንዲህ የሚያደርገው መቼ እንደሆነ ለማወቅ “የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

a በ2015 በተደረገ ስብሰባ ላይ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት የተስማሙበት እስከ 2030 ሊደረስበት የታሰበ የዘላቂ ልማት አጀንዳ

b የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና የግብርና ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ ፈንድ ለግብርና ልማት የተባለው ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልጆች ፈንድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት ያወጡት የጋራ ሪፖርት።

c በራእይ መጽሐፍ ላይ ስለተጠቀሱት አራቱም ጋላቢዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።