ብቸኝነትን በወዳጅነት ማከም—መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳህ ይችላል?
ብቸኝነት በ2023 እልባት ሊበጅለት የሚገባ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ሆኗል። መፍትሔ ይገኝለት ይሆን?
የአሜሪካ የማኅበረሰብ ጤና ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ዶክተር ቪቬክ ሙርቲ “ብቸኝነትና የመገለል ስሜት ለጤናችን እና ለደህንነታችን ጠንቅ እየሆኑ ነው” ብለዋል። ከዚያ ግን አክለው “መፍትሔ ልናገኝለት እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል። መፍትሔው ምንድን ነው? “በትንሹ መጀመር ቢያስፈልግም በየቀኑ በምናደርጋቸው ነገሮች ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችንን ማጠናከር ነው” ሲሉ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል። a
ከሌሎች ጋር አለመሆን ብቻውን ለብቸኝነት ስሜት አይዳርግም። አንዳንዶች በሰዎች ተከበውም እንኳ ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። መንስኤው ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኝነትን ለመቋቋም ይረዳናል። ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችንን ለማጠናከር የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮች ይዟል።
ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች
የመግባባት ችሎታ አዳብር። ይህም የራስህን ስሜት መናገርን ብቻ ሳይሆን ጥሩ አድማጭ መሆንንም ይጨምራል። የሌሎች ሰዎች ጉዳይ ግድ እንደሚሰጥህ የምታሳይ ከሆነ ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4
የጓደኛ ምርጫህን አስፋ። በዕድሜ የሚበልጡህን ወይም የሚያንሱህን ጨምሮ የተለየ ባሕል፣ አስተዳደግ ወይም ብሔር ያላቸውን ሰዎች ጓደኛ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።”—2 ቆሮንቶስ 6:13
ጥሩ ጓደኛ ማግኘትና ጓደኝነቱን ማስቀጠል ስለምትችልበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ጓደኛ የማግኘት ፍላጎታችንን ማሟላት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
a የብቸኝነትና የመገለል ወረርሽኝ፦ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን፣ ማኅበራዊ ትስስርና ማኅበረሰብ ለጤና በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ላይ የሰጡት ሐሳብ፣ 2023