በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

fcafotodigital/E+ via Getty Images

ከእንስሳት ተዋጽኦዎች የጸዳ የአመጋገብ ሥርዓት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ከእንስሳት ተዋጽኦዎች የጸዳ የአመጋገብ ሥርዓት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ከእንስሳት ተዋጽኦዎች የጸዳ የአመጋገብ ሥርዓት (ቪጋኒዝም) በዓለም ዙሪያ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው።

  •   “ከእንስሳት ተዋጽኦዎች የጸዳ የአመጋገብ ሥርዓት ለምግብ፣ ለልብስም ሆነ ለሌላ ዓላማ ሲባል በእንስሳት ላይ የሚፈጸምን ጭካኔ በተቻለ መጠን ለማስቀረት አልሞ የሚንቀሳቀስ ፍልስፍናና የአኗኗር ዘይቤ ነው።”—ዘ ቪጋን ሶሳይቲ

 አንዳንዶች ለእንስሳት በመቆርቆር ብቻ ሳይሆን ለአካባቢ ደህንነት በማሰብ፣ ለጤንነታቸው ሲሉ ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት እንዲህ ያለውን የአመጋገብ ሥርዓት ይከተላሉ።

  •   “ከሌሎች የአመጋገብ ሥርዓቶች በተለየ ቪጋኒዝም የኑሮ መርሕ፣ ሥነ ምግባራዊ ውሳኔ ወይም አንድ ሰው በዓለም ላይ ለውጥ ለማምጣት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችልበት ዘዴ ተደርጎ ይታያል።”—ብሪታኒካ አካደሚክ

 ይህ የአመጋገብ ሥርዓት በእርግጥ ለፕላኔታችን ችግሮች መፍትሔ ያስገኛል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ፈጣሪያችን ለሰዎችና ለእንስሳት ያለው አመለካከት

 መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ a የሰው ልጆችን ከእንስሳት አስበልጦ እንደሚመለከታቸው እንዲሁም በእነሱ ላይ ሥልጣን እንደሰጣቸው ይጠቁማል። (ዘፍጥረት 1:27, 28) በኋላም አምላክ፣ ሰዎች እንስሳትን ለምግብነት እንዲጠቀሙ ፈቀደላቸው። (ዘፍጥረት 9:3) ያም ቢሆን አምላክ በእንስሳት ላይ የሚፈጸምን የጭካኔ ድርጊት አይደግፍም።—ዘፍጥረት 9:3

 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሥጋ መብላት ወይም አለመብላት ለእያንዳንዱ ሰው የተተወ ምርጫ ነው። b በዚህ ረገድ የምናደርገው ምርጫ አምላክ ለእኛ ባለው አመለካከት ላይ ለውጥ አያመጣም። (1 ቆሮንቶስ 8:8) ማንም ሰው ሌሎችን በአመጋገብ ምርጫቸው የተነሳ ሊተች አይገባም።—ሮም 14:3

በዓለማችን ላይ ለውጥ የሚመጣበት መንገድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የምንከተለው የአኗኗር ዘይቤ በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ሊያስወግድ እንደማይችል ይጠቁማል። የአብዛኞቹ ችግሮች መንስኤ በዓለም ላይ ያለው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ነው፤ ይህ ሥርዓት ደግሞ በሰው አቅም ሊለወጥ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

  •   “የተጣመመ ነገር ሊቃና አይችልም።”—መክብብ 1:15

 ፈጣሪያችን በዛሬው ጊዜ እያጋጠሙን ያሉትን ችግሮች ያስወግዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም አምላክ የሚወስደውን እርምጃ ይገልጻል።

  •   “እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤ ባሕሩም ከእንግዲህ ወዲህ የለም።”—ራእይ 21:1

 አምላክ ‘የቀድሞውን ሰማይ’ ማለትም ሰብዓዊ መንግሥታትን ‘በአዲስ ሰማይ’ ማለትም እሱ ባቋቋመው ሰማያዊ መንግሥት ይተካቸዋል። ይህ መንግሥት ‘የቀድሞውን ምድር’ ወይም ክፉዎችን አስወግዶ ‘በአዲስ ምድር’ ወይም ለሥልጣኑ በፈቃደኝነት በሚገዙ ሰዎች ላይ ይገዛል።

 የሰው ልጆች ከእንስሳትም ሆነ ከአካባቢያቸው ጋር ፍጹም በሆነ መንገድ ተስማምተው መኖር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚማሩት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 11:6-9

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18

b መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም ራቁ’ የሚል ትእዛዝ ይሰጠናል። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) ይህም ሲባል ደም ልንጠጣም ሆነ ደሙ ያልፈሰሰን እንስሳ ሥጋ ልንበላ እንዲሁም ደም የተጨመረባቸውን ምግቦች ልንመገብ አይገባም ማለት ነው።