ነቅታችሁ ጠብቁ!
ክርስቲያኖች እና ጦርነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የዩክሬኑ ጦርነት በግልጽ እንዳሳየው ብዙ የክርስትና እምነት መሪዎች ጦርነት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል። በሁለቱም በኩል ያሉ ቀሳውስት ጦርነቱን የደገፉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ እንመልከት፦
“አገራችሁን ዩክሬንን ከወራሪው ኃይል ለመታደግ እየተፋለማችሁ ያላችሁ ጀግና ተዋጊዎቻችን፣ ሁላችሁም ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል . . . በሐሳብ፣ በጸሎትና በሞራል ምንጊዜም ከጎናችሁ ነን።”—የኪየቩ ሜትሮፖሊታን ኤፒፋነስ አንደኛ እንደተናገሩት፣ ዘገባው የጀሩሳሌም ፖስት ነው፣ መጋቢት 16, 2022
“ሞስኮ ዩክሬን ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪ፣ እሁድ ዕለት ለሩሲያ ወታደሮች ቡራኬ ሰጥተዋል፤ ወታደሮቹ ‘በሩሲያውያን የጀግንነት ደንብ’ ለአገራቸው እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።”—ሮይተርስ፣ ሚያዝያ 3, 2022
ይሁንና ክርስቲያኖች በጦርነት ሊካፈሉ ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች በጦርነት እንደማይካፈሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።
“ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።”—ማቴዎስ 26:52
ጦርነትን የሚደግፍ ወይም ጦር ሜዳ ሄዶ የሚዋጋ ሰው የኢየሱስን ትእዛዝ አክብሯል ሊባል ይችላል?
“እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35
ጦርነትን የሚደግፍ ሰው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወይም ተከታዮቹ ተለይተው እንደሚታወቁበት የገለጸውን ዓይነት ፍቅር እያሳየ ነው ሊባል ይችላል?
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ክርስትና ጦርነትን ይደግፋል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
ክርስቲያኖችና ጦርነት በዘመናችን
በዘመናችን በጦርነት ጨርሶ የማይካፈሉ ክርስቲያኖች በእርግጥ አሉ? አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብሎ ስለሚጠራው አሁን ስላለንበት ዘመን የሚገልጽ አንድ ትንቢት ይህን ይጠቁማል፤ ትንቢቱ ከሁሉም አገራት የተውጣጡ ሰዎች ‘ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት እንደማይማሩ’ ይናገራል። በዚህ መንገድ የኢየሱስን ትምህርቶች ይታዘዛሉ።—ኢሳይያስ 2:2, 4 የግርጌ ማስታወሻ
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ ላይ “አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ምንድን ነው?” በሚል ዋና ርዕስ ሥር የወጡትን ርዕሶች አንብብ።
‘የሰላም አምላክ’ የሆነው ይሖዋ a በሰማይ ያቋቋመውን መንግሥት ተጠቅሞ በቅርቡ ሰዎችን “ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—ፊልጵስዩስ 4:9፤ መዝሙር 72:14
እንዴት የሚለውን ለማየት “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18