ወረርሽኙ የሚፈጥረውን ሥነ ልቦናዊ ጫና መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው ስጋት እያዛለህ ነው? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በዓለም ዙሪያ፣ ሰዎች ወረርሽኙ ባሳደረው ጫና የተነሳ ለበርካታ ወራት በአኗኗራቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። የዓለም የጤና ድርጅት የአውሮፓ ቀጠና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሃንስ ክሉገ “የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመግታት [ብዙዎች] ትልቅ መሥዋዕትነት መክፈል ጠይቆባቸዋል” ብለዋል። አክለውም “እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች አንድን ሰው ወደ መሰላቸት ወይም ተነሳሽነት ወደ ማጣት ሊመሩት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ እየዛለ እንደሆነ የሚጠቁም ምልክት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ወረርሽኙ የሚያሳድረው ሥነ ልቦናዊ ጫና እያዛለህ ከሆነ አይዞህ፣ ተስፋ አትቁረጥ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብዙዎች ይህ ሁኔታ ያሳደረባቸውን ውጥረት እንዲቋቋሙ እየረዳቸው ነው። አንተንም ሊረዳህ ይችላል።
ወረርሽኙ ምን ዓይነት ሥነ ልቦናዊ ጫና ያሳድራል?
ወረርሽኙ የፈጠረው ስጋትና ቀውስ ረዘም ላለ ጊዜ መዝለቁ በብዙዎች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና እያሳደረ ነው። ወረርሽኙ የሚያሳድረው ሥነ ልቦናዊ ጫና ከሰው ሰው ቢለያይም የተለመዱ ከሚባሉት ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
ተነሳሽነት ማጣት
የአመጋገብ ልማድ ወይም የእንቅልፍ ሥርዓት መዛባት
ብስጩ መሆን
ቀደም ሲል በቀላሉ እናከናውናቸው የነበሩ ነገሮችን መሥራት መፍራት
ትኩረትን መሰብሰብ መቸገር
ተስፋ መቁረጥ
ወረርሽኙ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና በቀላሉ መታየት የሌለበት ለምንድን ነው?
ይህ ስሜት፣ የእኛንም ሆነ የሌሎችን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ስሜቱን ካልተዋጋነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የደህንነት መመሪያዎችን ለመከተል ያለን ተነሳሽነት ቀስ በቀስ ሊጠፋ ይችላል። ቫይረሱ መስፋፋቱንና የሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ቢቀጥልም እኛ ግን ስለ ቫይረሱ ግድየለሽ እየሆንን ልንሄድ እንችላለን። በወረርሽኙ ምክንያት በተጣሉት እገዳዎች ከመሰላቸታችን የተነሳ ነፃነት ወደ መፈለግ ልንሄድ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ የእኛንም ሆነ የሌሎችን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
ይህ አስጨናቂ ጊዜ፣ ብዙዎች “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓል። (ምሳሌ 24:10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን ወረርሽኝ ጨምሮ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳን ምክር ይዟል።
ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ሥነ ልቦናዊ ጫና እንድትቋቋም የሚረዱህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች የትኞቹ ናቸው?
አካላዊ ርቀትህን ጠብቅ፤ ማኅበራዊ ግንኙነትህን ግን አታቋርጥ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እውነተኛ ወዳጆች ያበረታቱናል። (1 ተሰሎንቄ 5:11) በተቃራኒው ግን ለረጅም ጊዜ ራሳችንን ማግለል ጤንነታችንን ሊያቃውሰው ይችላል።—ምሳሌ 18:1
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በቪዲዮ፣ በስልክ ወይም በኢ-ሜይልና በጽሑፍ መልእክቶች አማካኝነት ከጓደኞችህ ጋር ለመገናኘት ጥረት አድርግ። ሲከፋህ የጓደኞችህን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል፤ እነሱ ያሉበትን ሁኔታም በየጊዜው ጠይቅ። ወረርሽኙ ያስከተለውን ጫና ለመቋቋም የረዷችሁን ጠቃሚ ሐሳቦች ተነጋገሩ። አጋጣሚ ፈልገህ ለጓደኞችህ ጥሩ ነገር አድርግ፤ ይህ ለአንተም ሆነ መልካም ነገር ለምታደርግለት ሰው ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።
አሁን ያለህበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:16
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጊዜህን በአስተዋይነት መጠቀምህ ጥሩ ጥሩ እንድታስብና ከልክ በላይ እንዳትጨነቅ ይረዳሃል።—ሉቃስ 12:25
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አሁን ማድረግ በማትችላቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ አሁን ባለህበት ሁኔታ ልታደርግ ስለምትችላቸው ነገሮች አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ አሁን ያለህበት ሁኔታ ጊዜ ያላገኘህላቸውን አንዳንድ ሥራዎች እንድታከናውን ወይም ተሰጥኦዎችህን እንድታሻሽል አጋጣሚ ይሰጥሃል? ከቤተሰብህ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ አጋጣሚ አግኝተሃል?
የተለመደ ፕሮግራምህን ጠብቅ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሁሉም ነገር . . . በሥርዓት ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 14:40
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በጥቅሉ ሲታይ፣ የተለመደ ዕለታዊ ፕሮግራማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ይበልጥ የተረጋጉና ደስተኛ ናቸው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አሁን ላለህበት ሁኔታ የሚስማማ ፕሮግራም አውጣ። የትምህርት ቤት ሥራዎችህን፣ መደበኛ ሥራህን፣ ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችህን የምታከናውንበት እንዲሁም መንፈሳዊ ነገሮችን የምታከናውንበት ጊዜ መድብ። ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም ፕሮግራምህ ውስጥ አካትት፤ ለምሳሌ ከቤተሰብህ ጋር የምትሆንበት፣ ወጣ ብለህ የምትንሸራሸርበትና ስፖርት የምትሠራበት ጊዜ መድብ። በየጊዜው ፕሮግራምህን ገምግም፤ አስፈላጊ ከሆነ ማስተካከያ አድርግበት።
ወቅቱ ሲለዋወጥ እንደ ሁኔታው ማስተካከያ አድርግ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።”—ምሳሌ 22:3
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁኔታው እንደምትኖርበት አካባቢ ሊለያይ ቢችልም የወቅቶች መለዋወጥ ንጹሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን እንደልብ ማግኘት የምትችልበት አጋጣሚ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነትህ አስፈላጊ ናቸው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የክረምቱ ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ ከተቻለ ሳሎንህ ወይም የምትሠራበት አካባቢ በቂ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ ማስተካከያ አድርግ። አየሩ ቀዝቃዛ ቢሆንም ከቤት ውጭ የሚከናወኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ዕቅድ አውጣ። የሚቻል ከሆነ፣ ከቤት ውጭ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት እንድትችል የክረምት ልብስ አዘጋጅ።
በጋ ሲገባ ደግሞ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከቤት ውጭ ያሳልፋሉ፤ ስለዚህ ደህንነትህን ለመጠበቅ ጥንቃቄ አድርግ። የምትሄድበትን ቦታና እዚያ ቦታ ሰው የማይበዛበትን ጊዜ ምረጥ።
የኮቪድ የደህንነት መመሪያዎችን ማክበርህን ቀጥል
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሞኝ . . . ደንታ ቢስ ነው፤ ደግሞም ከልክ በላይ በራሱ ይመካል።”—ምሳሌ 14:16
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኮቪድ-19 ገዳይ በሽታ ነው፤ ከተዘናጋን በቫይረሱ ልንጠቃ እንችላለን።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ወረርሽኙን በተመለከተ በአካባቢህ የሚሰጡትን መመሪያዎች በየጊዜው ተከታተል፤ ከመመሪያዎቹ አንጻር በቂ ጥንቃቄ እያደረግህ መሆን አለመሆንህን ገምግም። የምታደርገው ነገር አንተን፣ ቤተሰብህንም ሆነ ሌሎችን የሚነካው እንዴት እንደሆነ አስብ።
ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8
ይህ ምክር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ ማንኛውንም ከባድ ሁኔታ እንድትወጣ ይረዳሃል።—ኢሳይያስ 41:13
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በየቀኑ የተወሰነ ክፍል አንብብ። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ስብሰባቸውን ማካሄድ የሚችሉበት ዝግጅት አድርገዋል፤ ስብሰባው ላይ መገኘት የምትፈልግ ከሆነ ለምን እነሱን አታነጋግራቸውም? ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸውን፣ ዓመታዊውን የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ እንዲሁም ሌሎች ዓመታዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ በቪዲዮ ኮንፈረንስ እየተጠቀሙ ነው።
ወረርሽኙ የሚያሳድረውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመቋቋም የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
ኢሳይያስ 30:15፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”
ይህ ምን ማለት ነው? አምላክ በሚሰጠን ምክር መተማመናችን በአስቸጋሪ ጊዜ ተረጋግተን እንድንኖር ይረዳናል።
ምሳሌ 15:15፦ “ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤ ደስተኛ ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”
ይህ ምን ማለት ነው? በጥሩ ነገሮች ላይ ማተኮር በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ ደስተኛ እንድንሆን ይረዳናል።
ምሳሌ 14:15፦ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”
ይህ ምን ማለት ነው? የጤና አጠባበቅ መመሪያዎችን አክብር፤ የሚጣሉት እገዳዎች አስፈላጊ አይደሉም ብለህ ለመደምደም አትቸኩል።
ኢሳይያስ 33:24፦ “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”
ይህ ምን ማለት ነው? አምላክ በሽታን ሁሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቶልናል።