በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

Sean Gladwell/Moment via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

የዓለም ወታደራዊ ወጪ 2 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የዓለም ወታደራዊ ወጪ 2 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በ2022 የዓለም ወታደራዊ ወጪ 2.24 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል፤ ይህ እስከ ዛሬ ያልተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ለዚህ በዋነኝነት ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ ነው። የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም ሚያዝያ 2023 ባወጣው ሪፖርት ላይ የሚከተሉትን ግኝቶች ይፋ አድርጓል፦

  •   የአውሮፓ ወታደራዊ ወጪ “[በ2022] 13 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፤ ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ ወዲህ በአውሮፓ ይህን ያህል ከፍተኛ ወጪ የተመዘገበበት ዓመት የለም።”

  •   በ2022 ሩሲያ “[ለወታደራዊ ወጪ] ፈሰስ በምታደርገው ገንዘብ ላይ 9.2 በመቶ ገደማ ጭማሪ አድርጋለች፤ በመሆኑም ከፍተኛ ፈሰስ ከሚያደርጉ የዓለም አገራት ዝርዝር ውስጥ ከአምስተኛ ደረጃ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተዛውራለች።”

  •   ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ካላቸው የዓለም አገራት መካከል በ2022ም ቀዳሚውን ቦታ እንደያዘች ናት፤ “ከዓለም ወታደራዊ ወጪ 39 በመቶውን ይዛለች።”

 ከዚህ ሪፖርት አዘጋጆች አንዱ የሆኑት ዶክተር ናን ቲያን እንዲህ ብለዋል፦ “በቅርብ ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ወጪ መጨመሩ፣ የምንኖርበት ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስጋት እያጠላበት እንደሄደ ይጠቁማል።”

 በዛሬው ጊዜ ባሉ የዓለም ኃያላን መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተንብዮአል፤ ለሰላም ብቸኛው መፍትሔ ምን እንደሆነም ይናገራል።

ወታደራዊ ግጭቶች እንደሚጨምሩ በትንቢት ተነግሯል

  •   መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንኖርበትን ዘመን “የፍጻሜ ዘመን” ብሎ ይጠራዋል።—ዳንኤል 8:19

  •   የዳንኤል መጽሐፍ ስለዚህ ዘመን በተናገረው ትንቢት ላይ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እርስ በርሳቸው እንደሚቀናቀኑ ተንብዮአል። በትንቢቱ መሠረት እነዚህ ኃያላን መንግሥታት ‘ይጋፋሉ’፤ ይህም የበላይነቱን ቦታ ለመያዝ በመካከላቸው ሽኩቻ እንደሚኖር ይጠቁማል። ይህ ወታደራዊ ሽኩቻ ብዙ ‘ውድ ሀብት’ ወይም መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል።—ዳንኤል 11:40, 42, 43

 ይህን አስገራሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ፍጻሜውን ያገኘ ትንቢት—ዳንኤል ምዕራፍ 11 የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

እውነተኛ ሰላም የሚመጣው እንዴት ነው?

  •   አምላክ የሰው ልጆች የመሠረቷቸውን መስተዳድሮች ከቦታቸው እንደሚያነሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በምትካቸው ደግሞ “ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።”—ዳንኤል 2:44

  •   በቅርቡ ይሖዋ a አምላክ ከሰው ልጆች አቅም በላይ የሆነውን ነገር ያደርጋል፤ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ያመጣል። እንዴት? እሱ በሰማይ ያቋቋመው መንግሥት የጦር መሣሪያዎችንና ጦርነትን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል።—መዝሙር 46:8, 9

 የአምላክ መንግሥት ስለሚያከናውነው ነገር ይበልጥ ለማወቅ “በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ ‘ሰላም ይበዛል’” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18