በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ስለተከሰተው የውኃ እጥረት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ስለተከሰተው የውኃ እጥረት ምን ይላል?

 ሁላችንም በሕይወት ለመኖር ንጹሕ ውኃ ያስፈልገናል። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በዓለም ዙሪያ የውኃ ፍጆታው እየጨመረ ከመሆኑ አንጻር ከባድ የውኃ እጥረት ያጋጥማል ብለን እንጠብቃለን” በማለት አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ጊዜም እንኳ በዓለም ዙሪያ ያሉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት ይቸገራሉ።

Strdel/AFP via Getty Images

 ሁሉም ሰው በቂ ውኃ የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ወይስ የሰው ልጆች ዕድሜያቸውን ሙሉ ከውኃ እጥረት ጋር እየታገሉ መኖር ይጠበቅባቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውኃ አቅርቦት የሚሰጠው ተስፋ

 መጽሐፍ ቅዱስ የውኃ እጥረት የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። እንዲያውም ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በተትረፈረፈ ሁኔታ ይገኛል።

 “በምድረ በዳ ውኃ ይፈልቃልና፤ በበረሃማ ሜዳም ጅረት ይፈስሳል። በሐሩር የተቃጠለው ምድር ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣ የተጠማውም ምድር የውኃ ምንጭ ይሆናል።”—ኢሳይያስ 35:6, 7

 በዚህ ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምድር የተፈጠረችበትን መንገድ በተመለከተ ምን እንደሚል ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድርና ስለ ውኃ ዑደት ምን ይላል?

 “[አምላክ] ምድርን . . . መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አልፈጠራትም]።”—ኢሳይያስ 45:18

 አምላክ ምድርን የፈጠራት ለሕይወት አመቺ እንድትሆን አድርጎ ስለሆነ ንጹሕ ውኃ በበቂ መጠን እንዲኖር የሚያስችሉ ዑደቶችን አዘጋጅቷል።

 “[አምላክ] የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል፤ ጭጋጉም ወደ ዝናብነት ይለወጣል፤ ከዚያም ደመናት ያዘንባሉ፤ በሰው ልጆችም ላይ ዶፍ ያወርዳሉ።”—ኢዮብ 36:27, 28

 በአጭር አነጋገር ይህ ጥቅስ አምላክ ውኃ መልሶ የሚተካበት ተፈጥሯዊና አስተማማኝ ሥርዓት እንዳኖረ ይገልጻል። ውኃ ከመሬትና ከባሕር ተኖ በደመና መልክ ከተጠራቀመ በኋላ ዝናብ ሆኖ ይወርዳል፤ ይህም ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት ቋሚ የሆነ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል።—መክብብ 1:7፤ አሞጽ 5:8

 “ዝናብን በወቅቱ አዘንብላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ምርቷን ትሰጣለች፤ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ።”—ዘሌዋውያን 26:4

 አምላክ በግብርና ይተዳደሩ ለነበሩት የጥንቶቹ እስራኤላውያን ቋሚ የውኃ አቅርቦት እንዲያገኙ በማድረግ ምርታቸውን ፍሬያማ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ፍሬያማ ምርት ሊገኝ የሚችለው ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ሲመጣ እንደሆነ ያውቃል።

 አምላክ በጥንቷ እስራኤል ያደረገውን ነገር በቅርቡ በመላው ምድር ላይ ያደርገዋል። (ኢሳይያስ 30:23) በአሁኑ ጊዜ ግን በአብዛኞቹ የዓለማችን ክፍሎች የውኃ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፤ የዚህ ችግር መንስኤ ደግሞ የዝናብ እጥረት ብቻ አይደለም። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያለው የውኃ እጥረት መፍትሔው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ሌላስ ምን ይላል?

የውኃ እጥረት የሚወገደው እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት የውኃ እጥረትን ጨምሮ ፕላኔታችንን እያመሱ ያሉትን ችግሮች በሙሉ እንደሚያስወግድ ይናገራል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛ በሰማይ ያለ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15) የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታት ፈጽሞ ማድረግ የማይችሉትን ነገር ያደርጋል፤ ለውኃ እጥረት መንስኤ የሆኑትን ችግሮች ከሥር መሠረታቸው ያስወግዳል።

 ችግሩ፦ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውኃ ዑደት በእጅጉ እንዲዛባ አድርጓል። ይህም ከባድ ድርቅ እንዲሁም በኃይለኛ ዝናብ ወይም በባሕር ጠለል መጨመር ምክንያት የሚከሰት አውዳሚ ጎርፍ እያስከተለ ነው።

 መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት የምድርን ተፈጥሯዊ ሥርዓቶች በማስተካከል ፕላኔታችን ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም ያደርጋል። አምላክ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:5) ደረቅ መሬቶች በቂ ንጹሕ ውኃ ስለሚያገኙ በአሁኑ ጊዜ ማንም የማይኖርባቸው አካባቢዎችም እንኳ ሕይወት ላላቸው ነገሮች ምቹ ይሆናሉ። (ኢሳይያስ 41:17-20) ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት የምድርን ተፈጥሯዊ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ያውላል።

 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አስፈሪ የሆነን አውሎ ነፋስ ጸጥ በማሰኘት አምላክ ምን ያህል ኃይል እንደሰጠው በጥቂቱም ቢሆን አሳይቷል። (ማርቆስ 4:39, 41) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ ምድርን ሲገዛ የተፈጥሮ አደጋዎች አይኖሩም። ሰዎች የትኛውም ዓይነት አደጋ ይከሰታል ብለው ስለማይሰጉ እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት ይኖራቸዋል።

 ችግሩ፦ ጊዜያዊ ጥቅማቸው ብቻ የሚያሳስባቸው ስግብግብ የንግድ ድርጅቶች ወንዞችን፣ ሐይቆችንና የከርሰ ምድር ውኃን በመበከል የንጹሕ ውኃ እጥረት እንዲባባስ አድርገዋል።

 መፍትሔው፦ አምላክ ምድርን በማጽዳት ወንዞቿ፣ ሐይቆቿ፣ ባሕሮቿና አፈሯ እንደቀድሞው ጤናማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ምድር ገነት ትሆናለች። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ውብ በሆኑ ቃላት ይገልጸዋል፦ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤ በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1

 ለአካባቢያቸውም ሆነ ለሌሎች ምንም ግድ የሌላቸው ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል? አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [እንደሚያጠፋ]” ቃል ገብቷል።—ራእይ 11:18፤ ምሳሌ 2:21, 22

 ችግሩ፦ ሰዎች የውኃ አቅርቦቱን በአግባቡ እየተጠቀሙ ስላልሆነ አቅርቦቱ መተካት በማይችልበት ፍጥነት እያለቀ ነው።

 መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ፍላጎት ሳይሆን የአምላክ ፈቃድ ‘በምድር ላይ እንዲፈጸም’ ያደርጋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ምድር ላይ ላሉ ተገዢዎቹ ከሁሉ የላቀ ትምህርት ይሰጣል። ኢሳይያስ 11:9 እንደሚለው “[ምድር] በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።” a በዚያን ጊዜ የሚኖሩት ሰዎች እንዲህ ያለ የላቀ እውቀት ስለሚያገኙ እንዲሁም ለአምላክም ሆነ ለሁሉም ፍጥረታቱ ጥልቅ ፍቅር ስላላቸው ውብ የሆነችውን ፕላኔታችንንና የተፈጥሮ ሀብቷን በእንክብካቤ ይይዛሉ።

  •    የአምላክ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ወደፊት ምን ያከናውናል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

  •    ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጠው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ ያለውን ዘገባ አንተው ራስህ አንብብ።

  •    አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ይበልጥ ለማወቅ አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።