የምትወስደውን የአልኮል መጠጥ መጠን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰዎች ውጥረት ሲገጥማቸው፣ ብቸኝነት ሲሰማቸው ወይም እንዲሁ ሲደብራቸው ከበፊቱ የበለጠ ይጠጣሉ። የምትወስደው የአልኮል መጠጥ መጠን እየጨመረ ነው? ከሆነ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀምህ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ወይም የአልኮል መጠጥ ሱስ እንዳይዝህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን እስቲ እንመልከት።
የአልኮል መጠጥ በልኩ መውሰድ ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ . . . ሰዎች አትሁን።”—ምሳሌ 23:20
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ በልኩ መጠጣትን አያወግዝም። (መክብብ 9:7) ያም ቢሆን በልክ በመጠጣት፣ ከልክ በላይ በመጠጣትና በስካር መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያስቀምጣል። (ሉቃስ 21:34፤ ኤፌሶን 5:18፤ ቲቶ 2:3) አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳ ከልክ በላይ መጠጣቱ ውሳኔ የማድረግ ችሎታውን ሊያዛባው እንዲሁም ጤንነቱንና ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት ሊነካበት ይችላል።—ምሳሌ 23:29, 30
በብዙ አገሮች ባለሥልጣናት፣ ከአልኮል መጠጥ አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ከልኩ አለፈ የሚባለው የቱ ጋር ሲደርስ እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ደረጃ ያወጣሉ፤ ይህን ደረጃ የሚያወጡት አንድ ሰው በቀን የሚጠጣውን መጠንና በሳምንት የሚጠጣባቸውን ቀናት ብዛት በማስላት ነው። a ይሁንና የአልኮል መጠጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከሰው ሰው ይለያያል፤ በተጨማሪም ጨርሶ አለመጠጣት የተሻለ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መሥፈርት መሠረት
“ምንም አለመጠጣት ከሚመከርባቸው ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
በምታሽከረክርበት ወይም ማሽኖችን በምታንቀሳቅስበት ወቅት።
አንዲት ሴት ነፍሰ ጡር ስትሆን ወይም ስታጠባ።
አንዳንድ መድኃኒቶችን በምትወስድበት ወቅት።
አንዳንድ የጤና እክሎች ካሉብህ።
በመጠጥ አወሳሰድ ረገድ ራስን የመግዛት ችግር ካለብህ።”
የምትወስደው የአልኮል መጠጥ መጠን ከልክ እንዳለፈ የሚጠቁሙ ምልክቶች
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “መንገዳችንን እንመርምር፤ ደግሞም እንፈትን።”—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:40
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የመጠጥ አወሳሰድ ልማድህን በየጊዜው የምትገመግምና አስፈላጊ ሲሆን ማስተካከያ የምታደርግ ከሆነ መጠጥ ከሚያስከትላቸው ጎጂ ተጽዕኖዎች ራስህን ትጠብቃለህ። ቀጥሎ የተዘረዘሩት ምልክቶች፣ ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ራስህን መቆጣጠር እየተቸገርክ እንደሆነ ሊጠቁሙ ይችላሉ።
ደስ የሚልህ መጠጥ ስትጠጣ ብቻ ነው። ዘና ለማለት ወይም ከሌሎች ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ መጠጣት እንዳለብህ ይሰማሃል። ችግሮችህን ለመርሳት ወደ መጠጥ ዘወር ትላለህ።
ከበፊቱ የበለጠ መጠጣት ጀምረሃል። ከበፊቱ የበለጠ በተደጋጋሚ ትጠጣለህ። ጠንከር ያሉ መጠጦችን መውሰድ ጀምረሃል፤ በተጨማሪም ሞቅ እንዲልህ ከበፊቱ የበለጠ መጠጣት ያስፈልግሃል።
የመጠጥ አወሳሰድ ልማድህ፣ በቤት ወይም በሥራ ቦታ ችግር እየፈጠረብህ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ለመጠጥ የምታወጣው ወጪ በጀትህን እያቃወሰው መጥቷል።
ከጠጣህ በኋላ ደህንነትህን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ለማድረግ ትነሳለህ፤ ለምሳሌ መኪና ታሽከረክራለህ፣ ትዋኛለህ ወይም ማሽኖችን ታንቀሳቅሳለህ።
ሌሎች የመጠጥ አወሳሰድ ልማድህ እያሳሰባቸው እንደመጣ ነግረውሃል። እንዲህ ዓይነት አስተያየት ሲሰጥህ ለማስተባበል ትሞክራለህ። እንደምትጠጣ ወይም ምን ያህል መጠጥ እንደምትወስድ ከሌሎች ለመደበቅ ትጥራለህ።
የመጠጥ ልማድህን ማቆም ተቸግረሃል። የምትጠጣውን መጠን ለመቀነስ ወይም ጨርሶ መጠጣትህን ለማቆም ብትሞክርም አልተሳካልህም።
የምትወስደውን የአልኮል መጠጥ መጠን ለመቆጣጠር የሚረዱ አምስት ነገሮች
1. ዕቅድ አውጣ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በሳምንቱ ውስጥ የምትጠጣባቸውን ቀናት ወስን። በእነዚህ ቀናት ምን ያህል እንደምትጠጣ ገደብ አብጅ። በሳምንቱ ውስጥ የማትጠጣባቸው ቢያንስ ሁለት ቀናት ወስን።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ የአልኮል መጠጥ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጥ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት “አልፎ አልፎ ሙሉ በሙሉ ከአልኮል መጠጥ መታቀብ የአልኮል መጠጥ ጥገኝነትን ለመቀነስ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው” በማለት ተናግሯል።
2. ዕቅድህን ወደ ተግባር ለውጥ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የጀመራችሁትን ሥራ ዳር አድርሱት።”—2 ቆሮንቶስ 8:11
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ መደበኛ የመጠጥ መጠን የሚባለው ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርግ፤ ይህም የምትጠጣውን መጠን በትክክል ለመለካትና ለመቁጠር ይረዳሃል። የምትወዳቸውን አልኮል የሌላቸው መጠጦች በቅርብ አስቀምጥ።
በዩናይትድ ስቴትስ በአልኮል መጠጥ ሱሰኝነት ላይ የሚሠራው ብሔራዊ ተቋም እንደተናገረው “ከአልኮል መጠጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በመቀነስ ረገድ ትናንሽ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።”
3. በውሳኔህ ጽና።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “‘አዎ’ ካላችሁ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ካላችሁ አይደለም ይሁን።”—ያዕቆብ 5:12
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ አንድ ሰው ከዕቅድህ ውጭ እንድትጠጣ ሲጋብዝህ በትሕትና ሆኖም በቁርጠኝነት እንቢ ለማለት ዝግጁ ሁን።
በዩናይትድ ስቴትስ በአልኮል መጠጥ ሱሰኝነት ላይ የሚሠራው ብሔራዊ ተቋም እንደተናገረው “እንዲህ ላሉት ግብዣዎች ወዲያውኑ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠትህ በአቋምህ እንድትጸና ይረዳሃል።”
4. ውሳኔህ በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል።”—መክብብ 7:8
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የምትጠጣውን አልኮል መጠን መቀነስ የምትፈልግባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ጻፍ። ጥሩ እንቅልፍ መተኛት፣ ጤንነቴን ማሻሻል፣ ገንዘቤን በተሻለ መንገድ መጠቀም እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚሉት ያሉ ምክንያቶችን ማካተት ትችላለህ። ስላደረግከው ውሳኔ ለሌሎች ስታወራ ባጋጠመህ ተፈታታኝ ሁኔታ ላይ ሳይሆን በምታገኘው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርግ።
5. አምላክ እንዲረዳህ ጠይቀው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የአልኮል መጠጥ አወሳሰድ ልማድህ ካሳሰበህ አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ። ኃይል እንዲሰጥህና ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር እንዲረዳህ ለምነው። b በተጨማሪም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የያዘ ምክር ለመማር ጊዜ መድብ። በአምላክ እርዳታ የአልኮል መጠጥ ልማድህን መቆጣጠር ትችላለህ።
a ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ክፍል ባወጣው ደረጃ መሠረት ከልክ ያለፈ የመጠጥ አወሳሰድ የሚባለው “ለሴቶች በቀን 4 ወይም ከዚያ በላይ መጠጣት ወይም በሳምንት 8 ወይም ከዚያ በላይ መጠጣት፣ ለወንዶች ደግሞ በቀን 5 ወይም ከዚያ በላይ መጠጣት ወይም በሳምንት 15 ወይም ከዚያ በላይ መጠጣት ነው።” መደበኛ ተብሎ የሚወሰነው የመጠጥ መጠን ከአገር አገር ሊለያይ ይችላል፤ በመሆኑም በአካባቢህ ያለው የጤና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ልከኛ ነው የሚለው የመጠጥ አወሳሰድ ምን ያህል እንደሆነ አጣራ።
b የመጠጥ ልማድህን መቆጣጠር ካቃተህ የባለሙያ እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልግህም ይችላል።