በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላላቅ የምድር ነውጦች—የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ይላል?

ታላላቅ የምድር ነውጦች—የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ይላል?

 በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ። አብዛኞቹ ነውጦች ቀላል ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን ከባድ ናቸው፤ እነሱም መጠነ ሰፊ ውድመት እንዲሁም መከራና ሞት ያስከትላሉ። አንዳንድ ጊዜ የምድር ነውጦቹ ሱናሚ ያስነሳሉ፤ ሱናሚዎቹም በባሕር ዳርቻዎች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርሱ ከመሆኑም ሌላ የበርካቶችን ሕይወት ይቀጥፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ታላላቅ የምድር ነውጦች እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 መጽሐፍ ቅዱስ የምድር ነውጦች እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል?

 ኢየሱስ የምድር ነውጦች እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ ተመዝግቦ ይገኛል።

 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል።”—ማቴዎስ 24:7

 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምድር ነውጥ ይከሰታል፤ በተጨማሪም የምግብ እጥረት ይኖራል።”—ማርቆስ 13:8

 “ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል።”—ሉቃስ 21:11

 ኢየሱስ ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና ቸነፈር በሚከሰትበት ዘመን “ታላላቅ የምድር ነውጦች” “በተለያየ ስፍራ” እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል። እነዚህ ክንውኖች በተመሳሳይ ጊዜ የሚከሰቱት “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ወይም ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በተባለው ዘመን ውስጥ ነው። (ማቴዎስ 24:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ የጀመሩት በ1914 ሲሆን እስካሁን አላበቁም።

 በዛሬው ጊዜ የሚከሰቱት የምድር ነውጦች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ናቸው?

 አዎ። ኢየሱስ ስለ ምድር ነውጦችና ስለተለያዩ ክንውኖች የተናገረው ትንቢት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ እንደሆነ በግልጽ ማየት እንችላለን። ከ1914 ወዲህ ከ1,950 የሚበልጡ ትላልቅ የምድር ነውጦች ተከስተዋል፤ በእነዚህም ነውጦች የተነሳ በድምሩ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። a እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ከዚህ ክፍለ ዘመን ብቻ እንመልከት።

 2004—የሕንድ ውቅያኖስ። በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 9.1 የተመዘገበ የምድር ነውጥ ሱናሚ አስነስቶ ነበር። በዚህም የተነሳ በበርካታ አገሮች ውስጥ የሚገኙ 225,000 ገደማ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

 2008—ቻይና። በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 7.9 የተመዘገበው የምድር ነውጥ ከተሞችንና መንደሮችን አውድሟል፤ በተጨማሪም 90,000 ሰዎችን እንደገደለ፣ በ375,000 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዳደረሰ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቤት አልባ እንዳደረገ ይገመታል።

 2010—ሄይቲ። በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 7.0 የተመዘገበ የምድር ነውጥና እሱን ተከትለው የተከሰቱት ከባድ ርዕደ መሬቶች ከ300,000 በላይ ሰዎችን ገድለዋል፤ እንዲሁም ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ቤት አልባ አድርገዋል።

 2011—ጃፓን። በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 9.0 የተመዘገበ የምድር ነውጥና እሱን ተከትሎ የተከሰቱት ሱናሚዎች 18,500 ገደማ ሰዎችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቅለዋል። በተጨማሪም የፉኩሺማ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጉዳት ስለደረሰበት የኑክሌር አደጋ ተከስቷል። አደጋው ከደረሰ አሥር ዓመት ቢያልፍም በኃይል ማመንጫው አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ 40,000 ገደማ ሰዎች ባለው አደገኛ ጨረር ምክንያት ወደ ቤታቸው መመለስ አልቻሉም።

 ስለ ምድር ነውጦች የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

 ስለ ምድር ነውጦች የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በቅርቡ ምን እንደሚከሰት ይጠቁመናል። ኢየሱስ “እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስታዩ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች ሁኑ” ብሏል።—ሉቃስ 21:31

 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ላይ ያለ እውን መስተዳድር እንደሆነና ንጉሡም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምር ስለዚህ መንግሥት መናገሩ ነበር።—ማቴዎስ 6:10

 የአምላክ መንግሥት ምድርን ሲያስተዳድር አምላክ እንደ ምድር ነውጦች ያሉ በሰው ልጆች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ያስቀራል። (ኢሳይያስ 32:18) በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ የምድር ነውጦች በሰዎች ላይ ያስከተሉትን አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት ያስተካክላል። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:3, 4) ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የአምላክ መንግሥት ወደፊት ምን ያከናውናል?” የሚለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

a አኃዛዊ መረጃዎቹ የተወሰዱት በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጂኦፊዚካል መረጃ ተቋም ሥር ካለው ግሎባል ሲግኒፊካንት ኧርዝኩዌክ ዳታቤዝ ነው።