ነቅታችሁ ጠብቁ!
የዩክሬን ጦርነት የዓለምን የምግብ ቀውስ አባብሶታል
ግንቦት 19, 2022 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ከ75 ከሚበልጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንድ ሪፖርት ደርሶት ነበር፤ ሪፖርቱ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ቀድሞውንም ተባብሶ የነበረው ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት፣ በዩክሬን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ረሃብ ሊያመራ” እንደሚችል ይገልጻል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል፦ “ዓለማችን ቀድሞውንም በቋፍ ላይ ነበር፤ ጦርነቱ ደግሞ ብዙዎች በረሃብ አለንጋ እንዲገረፉ ሊያደርግ ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን እንዲህ ያለ የምግብ እጥረት እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል፤ ሆኖም ተስፋ ሰጪ የሆነ ሐሳብም ይዟል።
መጽሐፍ ቅዱስ የምግብ እጥረት እንደሚከሰት አስቀድሞ ተንብዮአል
ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:7
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ስለ አራት ምሳሌያዊ ፈረሰኞች ይናገራል። ከአራቱ ፈረሰኞች አንዱ ጦርነትን ያመለክታል። እሱን ተከትሎ የሚመጣው ፈረሰኛ ደግሞ ረሃብን ይወክላል። ይህ ፈረሰኛ በሚጋልብበት ወቅት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ስለሚኖር የምግብ ዋጋ በጣም ይወደዳል። “እነሆ ጥቁር ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሚዛን በእጁ ይዞ ነበር፤ . . . ድምፅ ሰማሁ፤ ይህ ድምፅ፣ ‘ግማሽ ኪሎ ያኽል ስንዴ የአንድ ቀን ደመወዝ፣ ለአንድ ኪሎ ተኩል ያኽል ገብስ ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን . . .’ ሲል ሰማሁ።”—ራእይ 6:5, 6 የታረመው የ1980 ትርጉም
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምግብ እጥረት የተናገራቸው እነዚህ ትንቢቶች በዘመናችን እየተፈጸሙ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዘመን ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” እና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተገለጹት አራት ፈረሰኞች ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ትፈልጋለህ? ከ1914 ወዲህ የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል የሚለውን ቪዲዮ እንድትመለከትና “አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል። ለምሳሌ፣ ከምግብ ዋጋ መወደድ ወይም ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንደምንችል አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ይሰጣል። “በአነስተኛ ገቢ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?” በሚለው ርዕስ ላይ ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችል ነጥቦች ታገኛለህ።
መጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣም ተስፋ ይሰጣል። ወደፊት ‘በምድር ላይ እህል እንደሚትረፈረፍ’ እና ሁሉም ሰው በቂ ምግብ እንደሚያገኝ ይናገራል። (መዝሙር 72:16) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን ተስፋ እንዲሁም በዚህ ተስፋ እምነት ልትጥል የምትችለው ለምን እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? “የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?” የሚለውን ርዕስ እንድታነብብ እንጋብዝሃለን።