ለምግብ ደህንነትና ለጤናማ አመጋገብ ወሳኝ የሆኑ ሰባት ነገሮች
አመጋገብህ ለውጥ የሚያመጣው ለምንድን ነው?
ጤንነትህ በተወሰነ መጠንም ቢሆን በአመጋገብህ ላይ የተመካ ነው። የምግብህን ደህንነት ለመጠበቅና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ለመከተል ጥረት የምታደርግ ከሆነ ጤንነትህ ይሻሻላል። በተቃራኒው ደግሞ፣ ጥራቱን ያልጠበቀ ነዳጅ መኪናን እንደሚያበላሽ ሁሉ ደህንነታቸው ያልተጠበቀና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብም ለከባድ የጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። ጉዳቱ ወዲያው አይታይ ይሆናል፤ መታየቱ ግን አይቀርም።—ገላትያ 6:7
የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው “በዓለም ላይ ያለው እያንዳንዱ አገር በአንዱ ወይም በሌላው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጠቃል፤” እዚህ ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲል በቂ ምግብ አለማግኘትን ብቻ ሳይሆን ከመጠን ያለፈ ክብደትንና ውፍረትንም ያጠቃልላል። ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችንና መጠጦችን አዘውትሮ መውሰድ ለልብ ድካም፣ ለስኳር፣ ለካንሰርና ለመሳሰሉት በሽታዎች ያጋልጣል። አንድ ጥናት እንደጠቆመው በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ቢያንስ 11 ሚሊዮን ሰዎች ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገመተው ከሆነ ደግሞ የተበከለ ምግብ በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት እንዲሁም በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕመም ምክንያት ሆኗል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ አክብደን እንድንመለከተው ያበረታታናል። “የሕይወት ምንጭ” አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 36:9) ሕይወት ስጦታ ነው፤ ስለዚህ የራሳችንንም ሆነ የቤተሰባችንን አባላት ጤንነት በመንከባከብ ለዚህ ስጦታ ያለንን አድናቆት ማሳየት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ለምግብ ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ አራት ነገሮች
1. ምግብህን በጥንቃቄ አዘጋጅ።
ለምን? በተበከለ ምግብና ውኃ ውስጥ ያሉ አደገኛ ጀርሞች a ወደ ሰውነትህ ሊገቡና ሊያሳምሙህ ይችላሉ።
የጤና ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?
ምግብ ማዘጋጀት ከመጀመርህ በፊት እጅህን በሳሙናና በውኃ b ታጠብ። እጆችህን ቢያንስ ለ20 ሰከንድ በደንብ እሻቸው። የእጆችህን ጀርባ (አይበሉባ)፣ በጣቶችህ መሃል ያሉትን ቦታዎች እንዲሁም ከጥፍሮችህ ሥር ያሉትን ቦታዎች በደንብ እሻቸው። ከዚያም እጆችህን በውኃ አልቅልቀህ በደንብ አድርቃቸው።
መክተፊያዎችን፣ ድስቶችንም ሆነ ምግብ የሚቀመጥበትን ማንኛውንም ዕቃ በሳሙናና በውኃ እጠብ። በተጨማሪም የሚበስሉና በጥሬው የሚበሉ ምግቦችን በአንድ መክተፊያ አትክተፍ።
ማንኛውንም ፍራፍሬና አትክልት ሳታጥብ አትመገብ፤ በአካባቢህ ሰዎች እርሻ ለማልማት እዳሪ የሚገባበትን ውኃ እንደ መስኖ አድርገው የሚጠቀሙ ከሆነ የምትገዛቸውን ፍራፍሬዎችና አትክልት በጀርም ማጽጃ ኬሚካሎች አጽዳ።
2. የበሰሉና ያልበሰሉ ምግቦችን ለያይተህ አስቀምጥ።
ለምን? ያልበሰሉ ምግቦች ውስጥ ያሉ ጀርሞች (ለምሳሌ በጥሬ ሥጋና ከውስጡ በሚወጣው ፈሳሽ ውስጥ ያሉ ጀርሞች) ሌሎች ምግቦችን ሊበክሉ ይችላሉ።
የጤና ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?
ከገበያ የገዛሃቸውን ነገሮች ወደ ቤት ስትወስድም ሆነ ቤት ውስጥ ስታስቀምጥ ያልበሰሉ ምግቦችን (በተለይ ሥጋን) ከበሰሉ ምግቦች ለይተህ አስቀምጥ።
ሥጋ ከከተፍክ በኋላ ሌላ ነገር ከመክተፍህ በፊት እጅህን በሚገባ ታጠብ፤ የተጠቀምክበትን ቢላና መክተፊያም በደንብ እጠብ።
3. በእሳት መብሰል ያለባቸውን ምግቦች በሚገባ አብስል።
ለምን? ጎጂ ጀርሞችን መግደል የሚቻለው በከፍተኛ ሙቀት ብቻ ነው።
የጤና ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?
ምግብ ስታበስል በደንብ ከመብሰሉ በፊት አታውጣው። የምታበስለው ምግብ (የሥጋን ውስጠኛ ክፍል ጨምሮ) 70 ዲግሪ ሴልሸስ የሙቀት መጠን ላይ ከደረሰ በኋላ ቢያንስ ለ30 ሰከንድ እሳት ላይ ሊቆይ ይገባል።
ሾርባ ወይም ወጥ ስትሠራ በደንብ እንዲንተከተክ አድርግ።
ቀድሞ የበሰለን ምግብ ከመመገብህ በፊት ትኩስ እስኪሆንና እንፋሎት እስኪያወጣ ድረስ አሙቀው።
4. ምግብህን በተገቢው የሙቀት መጠን ላይ አስቀምጥ።
ለምን? ከ5 እስከ 60 ዲግሪ ሴልሸስ ባለ የሙቀት መጠን ላይ የተቀመጠ ምግብ በ20 ደቂቃ ብቻ በውስጡ ያሉት ባክቴሪያዎች በእጥፍ ሊጨምሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ጥሬ ሥጋ በተገቢው የሙቀት መጠን ላይ ካልተቀመጠ በውስጡ ያሉት አንዳንድ ባክቴሪያዎች የሚያመነጯቸው መርዞች ሥጋው በእሳት ከበሰለ በኋላም እንኳ ላይጠፉ ይችላሉ።
የጤና ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?
ምግብ፣ ወይ ቀዝቃዛ ወይ ትኩስ ሆኖ መቀመጥ አለበት እንጂ ለብ ብሎ መቀመጥ የለበትም፤ ይህም በምግቡ ውስጥ ያሉት ጀርሞች የሚባዙበትን ፍጥነት ለመግታት ወይም ጨርሶ እንዳይባዙ ለማድረግ ይረዳል።
ምግብህን ማቀዝቀዣ ውስጥ ሳታስገባ ከሁለት ሰዓት በላይ ማቆየት አይኖርብህም፤ የክፍሉ ሙቀት ከ32 ዲግሪ ሴልሸስ በላይ ከሆነ ደግሞ ምግቡ ከአንድ ሰዓት በላይ ውጭ መቆየት የለበትም።
ምግብ ካበሰልክ በኋላ እስክታቀርበው ድረስ ትኩስ ሆኖ እንዲቆይ አድርግ።
ለጤናማ አመጋገብ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ነገሮች
1. በየቀኑ ፍራፍሬዎችና አትክልት ተመገብ።
ፍራፍሬዎችና አትክልት እንደ ቫይታሚን፣ ማዕድንና ሌሎች ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ይዘዋል። የዓለም የጤና ድርጅት፣ በየቀኑ ቢያንስ 400 ግራም ፍራፍሬና አትክልት መመገብ ለሰውነታችን አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው መጠን እንደ ድንች ያሉ ሥራ ሥሮችን አይጨምርም።
2. ቅባትና ዘይት አታብዛ።
በዘይት የተጠበሱ እንዲሁም የታሸጉ ወይም ፋብሪካ ውስጥ የተመረቱ ጣፋጭ ምግቦችን ማብዛት ጠቃሚ እንዳልሆነ የዓለም የጤና ድርጅት ይመክራል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ምግቦች ብዙውን ጊዜ ጤናማ ያልሆነ የቅባት ዓይነት አላቸው። ከተቻለ ምግብ ስታበስል የማይረጉ የአትክልት ዘይቶችን ተጠቀም። እንዲህ ያሉት ዘይቶች ከሚረጉ ዘይቶች የተሻለ ጤናማ ናቸው።
3. ጨውና ስኳር አታብዛ።
አዋቂዎች በቀን ውስጥ ከአንድ የሻይ ማንኪያ በላይ ጨው መውሰድ እንደሌለባቸው የዓለም የጤና ድርጅት ይመክራል። በተጨማሪም በቀን ውስጥ ከ60 ሚሊ ሊትር (12 የሻይ ማንኪያ) በላይ ስኳር መውሰድ እንደማይመከር የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። c በፋብሪካ በሚመረቱ ብዙ ምግቦችና መጠጦች ውስጥ በዋነኝነት የሚገባው ስኳር ነው። ለምሳሌ 355 ሚሊ ሊትር መጠን ባለው ለስላሳ መጠጥ ውስጥ እስከ 50 ሚሊ ሊትር (10 የሻይ ማንኪያ) የሚደርስ ስኳር አለ። ለስላሳ መጠጦች ብዙ ካሎሪ ቢኖራቸውም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ግን የሏቸውም።
መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ከአመጋገብ ልማድህ ጋር በተያያዘ ጠንቃቃ ከሆንክና አስፈላጊውን ማስተካከያ ካደረግህ አምላክ ለሰጠህ ሕይወትና ጤንነት አድናቆት እንዳለህ ታሳያለህ።
የተለመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶች
የተሳሳተ አመለካከት፦ አንድን ምግብ ስናየው፣ ስናሸተው ወይም ስንቀምሰው ደህና ከሆነ ልንመገበው እንችላለን።
እውነታው፦ አንድ ሊትር ውኃ ተበክሎ ጉም የሚመስልበት ደረጃ ላይ የሚደርሰው በውስጡ ከ10 ቢሊዮን በላይ ባክቴሪያዎች ሲኖሩ ነው፤ ሆኖም ይህን ያህል መጠን ባለው ውኃ ውስጥ ከ15 እስከ 20 አደገኛ ባክቴሪያዎች ቢኖሩ እንኳ ልንታመም እንችላለን። የምትበላውና የምትጠጣው ነገር ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ምግቡን ስታዘጋጅ፣ ስታቀርብም ሆነ ስታስቀምጥ ተገቢ የሙቀት መጠንን በተመለከተ የተሰጡ መመሪያዎችን ተከተል።
የተሳሳተ አመለካከት፦ ዝንቦች ምግብ አይበክሉም።
እውነታው፦ ዝንቦች የሚመገቡትም ሆነ የሚራቡት እንደ እዳሪ ባሉ ቆሻሻዎች ላይ ነው፤ በመሆኑም ብዙውን ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሽታ አምጪ ጀርሞችን በእግራቸው ይሸከማሉ። የበሰለ ምግብ በዝንቦች እንዳይበከል ሙሉ በሙሉ መሸፈን ይኖርበታል።
የተሳሳተ አመለካከት፦ “ለረጅም ጊዜ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት አልነበረኝም፤ አሁን ለውጥ ባደርግም ያን ያህል አይጠቅመኝም።”
እውነታው፦ ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት ከሆነ አመጋገብህን ለማስተካከል አሁኑኑ እርምጃ መውሰድህ ያለዕድሜ የመሞት አጋጣሚህ እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ጤናማ አመጋገብ ይዘህ በቀጠልክ መጠን ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞች ታገኛለህ።
a ጀርሞች በዓይን ሊታዩ የማይችሉ ጥቃቅን ተሕዋስያን ናቸው። ከእነዚህ መካከል ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶችና ፓራሳይቶች ይገኙበታል። አንዳንድ በዓይን የማይታዩ ተሕዋስያን ጠቃሚ ናቸው፤ ጎጂዎቹ ተሕዋስያን ግን እንድትታመም ሊያደርጉህ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርጉህ ይችላሉ።
b በውኃ ብቻ ከመታጠብ ይልቅ ሳሙና መጠቀም የበለጠ ጀርሞችን የማስወገድ ኃይል አለው።
c እዚህ ላይ ስኳር የተባለው፣ ከፍተኛ ጣፋጭነት ያላቸው ወይም በፋብሪካ የሚመረቱ የስኳር ዓይነቶችን ያጠቃልላል፤ ከእነዚህ መካከል ማር እና የፍራፍሬ ጭማቂዎች ይገኙበታል። በተፈጥሮ በፍራፍሬዎች፣ በአትክልትና በወተት ውስጥ የሚገኘው ስኳር እዚህ ውስጥ አይካተትም።