በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነቅታችሁ ጠብቁ!

የትምህርት ቤት ተኩስ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የትምህርት ቤት ተኩስ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ግንቦት 24, 2022 ቴክሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በምትገኘው ዩቫልዲ የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ዘግናኝ የሆነ ነገር አጋጠመ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “መሣሪያ የታጠቀ አንድ ሰው፣ ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በከፈተው ተኩስ 19 ልጆችና ሁለት መምህራን ተገድለዋል።”

 የሚያሳዝነው እንዲህ ያሉ ዘግናኝ ክስተቶች በጣም የተለመዱ እየሆኑ ነው። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ስለተፈጸሙ ክስተቶች ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “ባለፈው ዓመት ብቻ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 249 ጊዜ ተኩስ ተከፍቷል፤ ከ1970 ወዲህ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ዓመት የለም።”

 እንዲህ ያሉ የጭካኔ ድርጊቶች የበዙት ለምንድን ነው? እነዚህ አረመኔያዊ ድርጊቶች የሚፈጥሩትን ስሜት ለመቋቋም ምን ይረዳናል? ግፍና የኃይል ጥቃቶች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል።

አረመኔያዊ ጥቃቶች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?

 ብዙዎችን የሚያሳስብ አንድ ጥያቄ አለ፦ ‘አምላክ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሚፈጸሙ ያሉ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚደርሱ አረመኔያዊ ጥቃቶችን የማያስቆመው ለምንድን ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ለማወቅ “ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገሮች ይደርሱባቸዋል—ለምን?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

እንዲህ ያሉ የክፋት ድርጊቶች የሚፈጥሩብንን ስሜት ለመቋቋም ምን ይረዳናል?

  •    “ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።”—ሮም 15:4

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መመሪያዎች በዚህ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሙንን ነገሮች ለመቋቋም ይረዱናል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ዓመፅ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚለውን ንቁ! መጽሔት አንብብ።

 ወላጅ ከሆንክ ልጆችህን አስጨናቂ ከሆኑ የዜና ዘገባዎች ለመጠበቅ የሚረዱ ሐሳቦች ማግኘት ትፈልጋለህ? “የሚያስጨንቁ የዜና ዘገባዎችና ልጆቻችሁ” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ግፍና ጭካኔ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

  •    “ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:14

  •    “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ። አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።”—ሚክያስ 4:3

 አምላክ ከሰው ልጆች አቅም በላይ የሆነውን ነገር ያደርጋል። በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት የጦር መሣሪያዎችን ጠራርጎ ያጠፋል፤ የኃይል ጥቃቶችንም ሙሉ በሙሉ ያስቀራል። የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን ለማወቅ “በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ ‘ሰላም ይበዛል’” የሚለውን ርዕስ እንድታነብብ እንጋብዝሃለን።