ነቅታችሁ ጠብቁ!
የዓለም ዋንጫ በእርግጥ ሕዝቦችን ያቀራርባል?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 18, 2022 እየተካሄደ ያለውን የፊፋ የዓለም ዋንጫ አምስት ቢሊዮን ሰዎች ይከታተሉታል ተብሎ ይገመታል። ሰዎች እንዲህ ያሉ ስፖርታዊ ውድድሮችን አብሮ መመልከት እንደሚያቀራርብ ይሰማቸዋል፤ እነዚህ ውድድሮች ከዚህም የበለጠ ፋይዳ እንዳላቸው የሚያስቡም አሉ።
“ስፖርት ዓለምን የመቀየር ኃይል አለው። ሰዎችን ለበጎ የማነሳሳት ኃይል አለው። የስፖርትን ያህል ሰዎችን አንድ የማድረግ ኃይል ያለው ሌላ ነገር የለም።”—ኔልሰን ማንዴላ፣ የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት
“እግር ኳስ . . . በተስፋ አንድ ያደርጋል፣ በደስታ አንድ ያደርጋል፣ በጋለ ስሜት አንድ ያደርጋል፣ በፍቅር አንድ ያደርጋል፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ይፈጥራል።”—ጃኒ ኢንፋንቲኖ፣ የፊፋ a ፕሬዚዳንት
ታዲያ የዓለም ዋንጫም ሆነ ሌላ ማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዲህ ያለውን የተቀደሰ ዓላማ ሊያሳካ ይችላል? ሰላምና አንድነት ይመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለን?
በእርግጥ አንድ ያደርጋል?
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከእግር ኳስነትም ያለፈ ትርጉም ነበረው። አወዛጋቢ የሆኑ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል፤ ከሰብዓዊ መብት፣ ከዘረኝነትና ኢፍትሐዊ ከሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የተነሱትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ብዙዎች እንደ ዓለም ዋንጫ ባሉ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ይዝናናሉ። ይሁንና ሰዎች እንደሚመኙት እነዚህ ውድድሮች የሚያስገኙት አንድነት ዘላቂ አይደለም። እንዲያውም ከፋፋይ የሆኑ ባሕርያትና ድርጊቶች ጎልተው የሚታዩት እንዲህ ባሉ ውድድሮች ላይ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ በሚጠራው በዚህ ዘመን እነዚህ ባሕርያት የተለመዱ እንደሚሆኑ በትንቢት ተነግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ለአንድነት እውነተኛ ተስፋ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንደሚሰፍን የሚገልጽ እውነተኛ ተስፋ ይዟል። ‘የአምላክ መንግሥት’ በመባል የሚታወቀው ሰማይ ላይ ያለ መስተዳድር፣ የምድርን ነዋሪዎች አንድ እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 4:43፤ ማቴዎስ 6:10
የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዓለም በሙሉ ሰላምን ያሰፍናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦
“ጻድቅ ይለመልማል፤ . . . ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7
“እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ . . . ይታደጋልና። ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:12, 14
የኢየሱስ ትምህርቶች ዛሬም እንኳ በ239 አገራት የሚኖሩ ሚሊዮኖችን አንድ አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች ጥላቻን ድል መንሳት ችለዋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች አንብብ።
a ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አስተዳደር አካል (Fédération Internationale de Football Association)