በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

Pawel Gluza/500Px Plus/Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

የዱር እንስሳት ቁጥር በ50 ዓመት ውስጥ 73 በመቶ አሽቆለቆለ—⁠መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የዱር እንስሳት ቁጥር በ50 ዓመት ውስጥ 73 በመቶ አሽቆለቆለ—⁠መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ጥቅምት 9, 2024 የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ የተባለው ድርጅት የሰው ልጆች እንቅስቃሴ በዱር እንስሳት ሕይወት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ አስደንጋጭ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። ሪፖርቱ እንደገለጸው “ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ማለትም ከ1970 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የዱር እንስሳት አማካይ ቁጥር 73 በመቶ ቀንሷል።” ሪፖርቱ አክሎም እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚከናወነው ነገር በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ዕጣ ይወስነዋል ቢባል ምንም ማጋነን አይሆንም።”

 ብዙዎች እንዲህ ያሉ ሪፖርቶችን ሲሰሙ ቢደናገጡ አያስገርምም። ውብ የሆነችውን ፕላኔታችንን እንወዳታለን፤ በላይዋ ላይ የሚኖሩ የዱር እንስሳት ሲሠቃዩ ማየትም አንፈልግም። እንዲህ የሚሰማን አምላክ እንስሳትን እንድንንከባከብ አድርጎ ስለፈጠረን ነው።​—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ምሳሌ 12:10

 ከዚህ አንጻር እንዲህ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብህ ይሆናል፦ ‘የዱር እንስሳትን ከመጥፋት ልንታደጋቸው እንችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?’

አስደሳች ተስፋ

 እኛ የቻልነውን ሁሉ ጥረት ብናደርግም ልናመጣ የምንችለው ለውጥ ውስን ነው። የፕላኔታችንን የዱር እንስሳት ሊታደጋቸው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 11:18 ላይ፣ አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [እንደሚያጠፋ]” ይናገራል። ይህ ጥቅስ ሁለት ነገሮችን ያስገነዝበናል፦

  1.  1. አምላክ ሰዎች ምድርን ሙሉ በሙሉ እንዲያበላሿት ወይም እንዲያጠፏት አይፈቅድላቸውም፤ እንደዚያ ከማድረጋቸው በፊት ጣልቃ ገብቶ ያስቆማቸዋል።

  2.  2. አምላክ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። ይህን በምን እናውቃለን? የሰው ዘር በታሪክ ዘመናት ውስጥ የአሁኑን ያህል የዱር እንስሳትን ለማጥፋት ተቃርቦ አያውቅም።

 አምላክ ይህን ችግር ለማስወገድ ምን እርምጃ ይወስዳል? በሰማይ ባቋቋመው መስተዳድር ወይም መንግሥት አማካኝነት መላዋን ምድር ይገዛል። (ማቴዎስ 6:10) ይህ መንግሥት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የዱር እንስሳትን ለመንከባከብና ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርትና ሥልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል።​—ኢሳይያስ 11:9