ነቅታችሁ ጠብቁ!
የስደተኞች ቀውስ—በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዩክሬንን ለቀው እየተሰደዱ ነው
የካቲት 24, 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ወረራ ጀመረች። በዚህ የተነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ እየሸሹ ስለሆነ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል። a
“በየቦታው ከባድ ፍንዳታ አለ። ሁኔታው ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። አካባቢውን ለቀው የሚወጡ ሰዎችን የሚያጓጉዙ ባቡሮች እንዳሉ ስንሰማ እኛም ለመውጣት ወሰንን። በጀርባችን ከምትታዘል ትንሽ ቦርሳ በስተቀር ምንም መያዝ አልቻልንም። መያዝ የቻልነው አስፈላጊ ሰነዶችን፣ መድኃኒቶችን፣ ውኃና ትንሽ የሚቀመስ ነገር ብቻ ነው። ሁሉን ነገር ትተን ወደ ባቡር ጣቢያው ስንሄድ በአካባቢያችን በየቦታው ቦምብ ይፈነዳ ነበር።”—በካርኪቭ፣ ዩክሬን ትኖር የነበረችው ናታሊያ
“እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ጦርነት ይቀሰቀሳል ብለን አላመንም ነበር። በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው ፍንዳታ መስኮቶቹን ያንገጫግጫቸው ነበር። በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ይዤ ለመውጣት ወሰንኩ። ጠዋት 2:00 ላይ ከቤት ወጥቼ ወደ ለቪፍ የሚወስደውን ባቡር ተሳፈርኩ፤ ከዚያም ወደ ፖላንድ የሚወስደውን አውቶቡስ ይዤ ተጓዝኩ።”—በካርኪቭ፣ ዩክሬን ትኖር የነበረችው ናዲያ
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ይህ የስደተኞች ቀውስ እንዲከሰት ዋነኛ መንስኤ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?
በዩክሬን የስደተኞች ቀውስ የተከሰተው ሩሲያ ወታደራዊ ወረራ በማካሄዷ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ቀውስ መከሰት መሠረታዊ መንስኤ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ይጠቁማል፦
ሰብዓዊ መንግሥታት የሰው ልጆችን ፍላጎቶች ማሟላት አልቻሉም። መንግሥታት ሥልጣናቸውን የሚጠቀሙበት ሰዎችን ለማንገላታትና ለመጨቆን ነው።—መክብብ 4:1፤ 8:9
“የዚህ ዓለም ገዢ” ሰይጣን ዲያብሎስ በሰው ዘር ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” ይላል።—ዮሐንስ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 5:19
የሰው ዘር በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የተለያዩ ችግሮች የተፈራረቁበት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ ሲገልጽ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]” በማለት ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚህም ሌላ ያለንበት ጊዜ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የምግብ እጥረትና ቸነፈር የሚከሰትበት ዘመን እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ሰዎችን ለስደት ይዳርጋሉ።—ሉቃስ 21:10, 11
ስደተኞች ምን የሚያጽናና ተስፋ አላቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ፣ b ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ስደተኞች የሚራራ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (ዘዳግም 10:18) ይሖዋ፣ የአምላክ መንግሥት ተብሎ በሚጠራው በሰማይ ባለው መስተዳድሩ አማካኝነት ስደተኞች ያሉባቸውን ችግሮች በሙሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል፤ ይህ የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን አስወግዶ ምድርን ይገዛል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት ሰይጣን ዲያብሎስን ያጠፋል። (ሮም 16:20) ይህ መንግሥት ዓለም አቀፍ መስተዳድር ነው፤ በድንበርና በወሰን የተከፋፈለ አይደለም። የሰው ዘር በሙሉ አንድ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ ይሆናል። የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚያስተዳድርበት ወቅት ከአካባቢው የሚፈናቀል ሰው አይኖርም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይዟል፦ “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም፤ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”—ሚክያስ 4:4
በዛሬው ጊዜ ላለው የስደተኞች ቀውስ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። ይሖዋ ሰዎችን ለስደት የዳረጓቸውን ችግሮች በሙሉ በመንግሥቱ አማካኝነት ያስወግዳል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
ጦርነት። “[ይሖዋ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9) አምላክ ግጭቶችን የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “በምድር ላይ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
ጭቆናና ግፍ። “[ይሖዋ] ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል።” (መዝሙር 72:14) ሰዎች ሥር የሰደዱ መጥፎ አመለካከቶችን እንዴት መለወጥ እንደሚችሉ ለመረዳት “የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ” በሚል ጭብጥ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።
ድህነት። “[ይሖዋ] እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ . . . ይታደጋል።” (መዝሙር 72:12) አምላክ ለድህነት ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች እንዴት እንደሚያስወግድ ለማወቅ “ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
የምግብ እጥረት። “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል።” (መዝሙር 72:16) አምላክ ማንም ሰው ለረሃብ የማይዳረግበት ጊዜ እንደሚመጣ የሰጠውን ዋስትና ለማወቅ “ረሃብ የማይኖርበት ዓለም” (እንግሊዝኛ) የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ለስደተኞች የሚሆን ምን ጠቃሚ ምክር ይዟል?
መጽሐፍ ቅዱስ ለስደተኞች አስተማማኝ ተስፋ በመስጠት ብቻ አይወሰንም፤ በዛሬው ጊዜ የሚደርሱባቸውን ችግሮች መወጣት እንዲችሉ የሚረዳ ጠቃሚ ምክርም ይዟል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15
ምን ማለት ነው? ምን ችግሮች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉና እነዚህን ችግሮች ለመወጣት ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ተሰደህ በሄድክበት አካባቢ ያሉ ወንጀለኞች ለአካባቢው እንግዳ መሆንህን አይተው የጥቃት ሰለባ እንዳያደርጉህ ተጠንቀቅ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8
ምን ማለት ነው? ቁሳዊ ነገሮች ላይ አታተኩር። መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ረክተህ የምትኖር ከሆነ ደስተኛ ትሆናለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12
ምን ማለት ነው? ታጋሽና ደግ ሁን። እነዚህን ባሕርያት ማሳየትህ በተሰደድክበት አካባቢ ባሉ ሰዎች ዘንድ አክብሮትና ተቀባይነት እንድታገኝ ይረዳሃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።”—ሮም 12:17
ምን ማለት ነው? ግፍ ሲፈጸምብህ ተበሳጭተህ አጸፋ ለመመለስ አትሞክር። እንዲህ ማድረግህ ችግሩን ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13
ምን ማለት ነው? በሕይወትህ ውስጥ ለአምላክ ቀዳሚውን ቦታ በመስጠት አዘውትረህ ጸልይ። ያሉብህን ችግሮች እንድትቋቋም ይረዳሃል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ምን ማለት ነው? ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አምላክ ውስጣዊ ሰላም እንዲሰጥህና እንዲያረጋጋህ ጸልይ። “ፊልጵስዩስ 4:6, 7—‘ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ’” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
a በወረራው ማግስት፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ይህን ቀውስ በአስጊነቱ የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ ሰጥቶታል። በ12 ቀናት ውስጥ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከዩክሬን ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል፤ ሌሎች አንድ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ እዚያው ዩክሬን ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተፈናቅለዋል።
b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።