በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ መደበኛው ሕይወታችን እንመለስ ይሆን? ሕይወት ከወረርሽኝ ማግስት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጣቸው ጠቃሚ ሐሳቦች

ወደ መደበኛው ሕይወታችን እንመለስ ይሆን? ሕይወት ከወረርሽኝ ማግስት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጣቸው ጠቃሚ ሐሳቦች

 “ወደ መደበኛው ሕይወት መመለስ የማይፈልግ ማን አለ?”—አንጌላ መርከል፣ የጀርመን ቻንስለር

 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም ዓለምን እያተራመሰ ባለበት በዚህ ወቅት አንተም በቻንስለሯ ሐሳብ ትስማማ ይሆናል። ሆኖም “መደበኛ” ሕይወት ሲባል ምን ማለት ነው? ሰዎች የሚናፍቁት የትኛውን ሕይወት ነው?

  •   ከወረርሽኙ በፊት የነበራቸውን ሕይወት። አንዳንዶች የቀድሞው ማኅበራዊ ሕይወት ይናፍቃቸዋል፤ ከሌሎች ጋር እንደልብ መተቃቀፍ፣ መጨባበጥ እንዲሁም ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ የሚችሉበትን ጊዜ ይናፍቃሉ። ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ a እንደገለጹት “አንዳንዶች ወደ መደበኛው ሕይወት እንደተመለሱ የሚሰማቸው ሬስቶራንቶች፣ ቲያትር ቤቶችና እንዲህ የመሳሰሉት ነገሮች በደንብ ሲከፈቱ ነው።”

  •   ቀድሞ ከነበራቸው የተሻለ ሕይወት። አንዳንዶች ለውጥ እንዲመጣና ሕይወት ከወረርሽኙ በፊት ከነበረውም የተሻለ እንዲሆን ይፈልጋሉ። በዓለም ላይ ያሉት መሠረታዊ ችግሮች መስተካከል እንዳለባቸው ይሰማቸዋል፤ እንደ ምሳሌም፣ ጊዜንና ጉልበትን የሚያሟጥጡ ሥራዎችን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታየውን የፍትሕ መጓደል እንዲሁም እየተስፋፋ የመጣውን የአእምሮ ሕመም ይጠቅሳሉ። የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም መስራች የሆኑት ክላውስ ሽዋብ እንዲህ ብለዋል፦ “ወረርሽኙ የዓለማችንን ሁኔታ መለስ ብለን ለማሰብ፣ ‘ምን ቢደረግ የተሻለ ነው’ ብለን ለማቀድና አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ልዩ አጋጣሚ ሰጥቶናል፤ ጊዜው ሳያልፍብን አጋጣሚውን ልንጠቀምበት ይገባል።”

 ሌሎች ደግሞ በወረርሽኙ የተነሳ ሕይወታቸው ምስቅልቅሉ ስለወጣ ወደ “መደበኛው” ሕይወት መመለስ የሚባለው ነገር ጨርሶ አይታያቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች ሥራቸውን፣ ቤታቸውን፣ ጤናቸውን ይባስ ብሎም የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተዋል።

 እርግጥ ነው፣ ከወረርሽኝ ማግስት ሕይወት ምን እንደሚመስል በትክክል መተንበይ የሚችል ሰው የለም። (መክብብ 9:11) ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ፣ በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ እንድንሆንና ያላሰብናቸው ነገሮች ሲከሰቱ መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ጊዜ ስለሚኖረን ሕይወት የሚናገረውን ሐሳብ ስታውቅ ትገረም ይሆናል።

ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተገቢውን አመለካከት መያዝ

 ከረጅም ዘመናት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ላይ “ቸነፈር” ወይም ተላላፊ በሽታዎች እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11፤ ማቴዎስ 24:3) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከዚህ ጥቅስ አንጻር ካየነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሲፈጸም ከምንጠብቃቸው ክንውኖች አንዱ ብቻ ነው፤ በዚህ ዘመን እንደሚፈጸሙ ትንቢት ከተነገረላቸው ሌሎች ክስተቶች መካከል ጦርነት፣ ታላላቅ የምድር ነውጦችና የምግብ እጥረትም ይገኙበታል።

 ይህን ማወቃችን ምን ይጠቅመናል? ወረርሽኙ የፈጠረው ሁኔታ ነገ ይሻሻል ይሆናል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን’ እንደሆነ ያስጠነቅቀናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህን ማወቃችን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ እንድንሆን ይረዳናል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛው እይታ እንዲኖረን ይረዳናል፤ በብዙ ችግሮች የተቀሰፈው ዓለማችን በለውጥ ሂደት ላይ እንደሆነ ይነግረናል። ታዲያ ለውጡ ወዴት ያደርሰን ይሆን?

ከወረርሽኙ ማግስት አስደሳች ሕይወት ይጠብቀናል

 መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚናገረው በዘመናችን ስለሚያጋጥሙን ከባድ ችግሮች ብቻ አይደለም፤ በቅርቡ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉም ይነግረናል። የትኛውም የሰው ልጆች መንግሥት ሊሰጠን የማይችለው ዓይነት ሕይወት እንደምናገኝ ይገልጻል፤ ይህን ሊያከናውን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ራእይ 21:4

 ይሖዋ b አምላካችን “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:5) ወረርሽኙ ያስከተላቸውን ጨምሮ የዓለማችንን ችግሮች በሙሉ ያስወግዳል። የሚከተሉትን ጥሩ ነገሮች ያደርግልናል፦

  •   በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹም ጤናማ እንሆናለን፤ ያን ጊዜ ሕመምና ሞት አይኖርም።—ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24

  •   እውነተኛ እርካታ የምናገኝበት ሥራ ይኖረናል፤ ጉልበታችንን እና ጊዜያችንን የሚያሟጥጡ እንዲሁም እንድንዝል የሚያደርጉ ሥራዎች አይኖሩም።—ኢሳይያስ 65:22, 23

  •   ሁሉም ሰው የተመቻቸ ሕይወት ይኖረዋል፤ ድህነትና ረሃብ አይኖርም።—መዝሙር 72:12, 13፤ 145:16

  •   ከሚያሠቃዩን መጥፎ ትዝታዎች እናገግማለን፤ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎችም መልሰን እናገኛቸዋለን።—ኢሳይያስ 65:17፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

 ይህን ማወቃችን ምን ይጠቅመናል? መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ . . . የሆነ ይህ ተስፋ አለን” ይላል። (ዕብራውያን 6:19) ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የተሰጠን ይህ ተስፋ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ዛሬ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም የተሻለ አቅም ይሰጠናል፤ ጭንቀታችንን ይቀንስልናል እንዲሁም ያረጋጋናል።

 ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጠው ተስፋ በእርግጥ እምነት የሚጣልበት ነው? “መጽሐፍ ቅዱስ—አስተማማኝ የእውነት ምንጭ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ከወረርሽኙ ማግስት ያለውን ሕይወት ለመልመድ የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

  •   ለሕይወት ትልቅ ቦታ ስጥ

     ጥቅስ፦ “ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ [ታቆያለች]።”—መክብብ 7:12

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? ጥበብ ያለበት ውሳኔ በማድረግ በተቻለ መጠን ለሕመም እንዳትጋለጥ ተጠንቀቅ። በአካባቢህ ያለውን የበሽታ ተጋላጭነት ገምግም። ውሳኔ ስታደርግ የጤናና የደህንነት መመሪያዎችን፣ በአካባቢህ ያለውን የበሽታ ስርጭት እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎችን ብዛት ግምት ውስጥ አስገባ።

  •   ጠንቃቃ መሆንህን አታቁም

     ጥቅስ፦ “ጥበበኛ ሰው ጠንቃቃ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ ሞኝ ግን ደንታ ቢስ ነው፤ ደግሞም ከልክ በላይ በራሱ ይመካል።”—ምሳሌ 14:16

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? ጤናህን ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድህን ቀጥል። ባለሙያዎች፣ የኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ አብሮን ሊቆይ እንደሚችል ይገምታሉ።

  •   ተአማኒነት ያለው መረጃ አግኝ

     ጥቅስ፦ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? የማንን ምክር እንደምትሰማ በጥንቃቄ ምረጥ። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የምታደርገው ምርጫ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፤ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርተህ የምታደርገው ውሳኔ ጤንነትህን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።

  •   ምንጊዜም አዎንታዊ ሁን

     ጥቅስ፦ “‘የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?’ አትበል፤ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥበብ አይደለምና።”—መክብብ 7:10

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? በዛሬው ሕይወትህ ደስተኛ ሆነህ ለማለፍ ጣር። ከወረርሽኙ በፊት ስለነበረህ ሕይወት እያሰብክ አትቆዝም፤ በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉት እገዳዎች ባሳጡህ ነገሮች ላይም አታውጠንጥን።

  •   ለሌሎች አክብሮት ይኑርህ

     ጥቅስ፦ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? ሰዎች ስለ ወረርሽኙም ሆነ ስላስከተላቸው ችግሮች የተለያየ አመለካከት አላቸው። አመለካከታቸውን አክብርላቸው፤ ሆኖም አንተ አስበህበት ያደረግከውን ጥሩ ውሳኔ አትተው። ላልተከተቡ ሰዎች፣ ለአረጋውያንና ከባድ የጤና እክሎች ላሉባቸው ሰዎች አሳቢነት አሳይ።

  •   ታገሥ

     ጥቅስ፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 13:4

     ከዚህ ጥቅስ ምን ትማራለህ? አንዳንድ ሰዎች፣ ከዚህ በፊት የተለመዱ ወደነበሩ እንቅስቃሴዎች መመለስ ያስጨንቃቸው ይሆናል፤ እንዲህ ያሉ ሰዎችን በደግነት ያዝ። በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉት እገዳዎች እየላሉ ሲሄዱ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዎችህ መመለስ ትችል ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ስታደርግ ትዕግሥተኛ ሁን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ወረርሽኙ የፈጠረውን ሁኔታ እንዲቋቋሙ እየረዳቸው ያለው እንዴት ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የያዘውን አስደሳች ተስፋ ማወቃቸው አጽናንቷቸዋል፤ ይህም ከወረርሽኙ ባሻገር ያለውን እንዲያዩ ረድቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አዘውትረው ለአምልኮ እንዲሰበሰቡ የሚሰጠውን መመሪያም ይታዘዛሉ፤ ይህም እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ማንም ሰው መገኘት ይችላል፤ በወረርሽኙ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነው።

 በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ በመገኘታቸው በጣም እንደተጠቀሙ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኮቪድ-19 የያዛት አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት የቪዲዮ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ተጋበዘች። ይህች ሴት፣ በቫይረሱ ምክንያት ከገጠማት የጤና ችግር ጋር እየታገለች ቢሆንም ስብሰባዎቹ እንድትረጋጋ እንደረዷት ይሰማታል። በኋላ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “እኔም የዚህ ቤተሰብ አባል እንደሆንኩ ይሰማኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ አእምሮዬ ሰላም ያገኛል፣ ውስጤም ይረጋጋል። በችግሬ ላይ ሳይሆን ወደፊት በማገኘው አስደሳች ሕይወት ላይ እንዳተኩር ይረዳኛል። ከአምላክ ጋር ጠንካራ ዝምድና እንድመሠርት ስለረዳችሁኝ አመሰግናችኋለሁ፤ ይህ ሕይወቴን ሙሉ ስመኘው የነበረው ነገር ነው!”

a የዩናይትድ ስቴትስ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም ዳይሬክተር።

b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18