ጥንታዊ ማኅተሞች ምን ዓይነት ነበሩ?
በጥንት ዘመን፣ በሸክላ ጭቃ ላይ ወይም በሰም ላይ ምልክት ለማድረግ የሚያገለግሉ የተለያዩ ነገሮች የተቀረጹባቸው ማኅተሞች ነበሩ። ማኅተሞች በተለያየ ቅርጽ ይዘጋጁ ነበር። ለምሳሌ ሾጣጣ፣ አራት ማዕዘን ወይም ክብ ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል፤ በእንስሳት ጭንቅላት ቅርጽ የሚዘጋጁ ማኅተሞችም ነበሩ። ማኅተሞች ባለንብረትነትን ለማመልከት፣ አንድን ሰነድ ሕጋዊ ለማድረግ እንዲሁም ቦርሳ፣ በር ወይም የመቃብር መግቢያ እንዳይከፈት ለመከልከል ያገለግሉ ነበር።
ማኅተሞች ከአጥንት፣ ከኖራ፣ ከብረት፣ ከድንጋይ ወይም ከእንጨት ሊሠሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ የማኅተሙ ባለቤትና የአባቱ ስም በማኅተሙ ላይ ይቀረጽ ነበር። የባለማኅተሙ የማዕረግ ስም የሚቀረጽበት ጊዜም አለ።
አንድ ሰው አንድን ሰነድ ሕጋዊ ለማድረግ በሰነዱ ላይ የሸክላ ጭቃ፣ ሰም ወይም ቅርጽ የሚይዝ ሌላ ነገር ካደረገ በኋላ በዚያ ላይ ማኅተሙን ያሳርፍ ነበር። (ኢዮብ 38:14) ከዚያም ጭቃው ወይም ሰሙ ስለሚደርቅ ሰነዱ እንዳይቀየር ይከላከላል ተብሎ ይታሰብ ነበር።
ማኅተሞች ውክልና ለመስጠት ያገለግሉ ነበር
አንድ ሰው ከሌላ ሰው ማኅተም ሲቀበል ባለማኅተሙን የመወከል ሥልጣን ይኖረዋል። በጥንቷ ግብፅ የነበረ አንድ ፈርዖን የያዕቆብ ልጅ ለሆነው ለዕብራዊው ዮሴፍ ያደረገለት ነገር ይህን ያሳያል። ዮሴፍ በግብፅ ባሪያ ነበር። በኋላም በሐሰት ተከሶ እስር ቤት ገባ። ከጊዜ በኋላ ግን ፈርዖን ዮሴፍን ከእስር አስፈትቶ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር አደረገው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዚያም ፈርዖን የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ ላይ አውልቆ በዮሴፍ እጅ ላይ አደረገለት” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 41:42) ዮሴፍ የማኅተም ቀለበቱን መቀበሉ የተሰጠውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ሥልጣን እንዲኖረው ያደርጋል።
የጥንቷ እስራኤል ንግሥት የነበረችው ኤልዛቤል፣ ናቡቴ የተባለን ሰው ለማስገደል ስትል የባሏን ማኅተም ተጠቅማ ነበር። ኤልዛቤል በንጉሥ አክዓብ ስም ለአንዳንድ ሽማግሌዎች ደብዳቤ ጽፋ ‘ናቡቴ አምላክን ተራግሟል’ ብለው በሐሰት እንዲወነጅሉት አደረገች። ከዚያም ደብዳቤዎቹን በንጉሡ ማኅተም አተመቻቸው፤ የጠነሰሰችው ሴራም ሰመረላት።—1 ነገሥት 21:5-14
የፋርስ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንጉሣዊ ትእዛዙን ለማጽደቅ በማኅተም ቀለበቱ ተጠቅሟል።—አስቴር 3:10, 12
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ነህምያ የእስራኤል መኳንንት፣ ሌዋውያንና ካህናት በጽሑፍ በሰፈረ ቃል ኪዳን ላይ ማኅተማቸውን በማኖር ስምምነታቸውን እንደገለጹ ጽፏል።—ነህምያ 1:1፤ 9:38
ማኅተም፣ መግቢያዎች እንዳይከፈቱ ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር የሚያሳዩ ሁለት ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ነቢዩ ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ ከተወረወረ በኋላ ሰዎቹ “ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት።” ከዚያም የሜዶ ፋርስ ንጉሥ የሆነው ዳርዮስ “በዳንኤል ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዳይለወጥ፣ በራሱ የማኅተም ቀለበትና በመኳንንቱ የማኅተም ቀለበት በድንጋዩ ላይ አተመበት።”—ዳንኤል 6:17
የኢየሱስ አስከሬን መቃብር ውስጥ በተቀመጠበት ወቅት ጠላቶቹ መቃብሩን ለመዝጋት በተገጠመው ‘ድንጋይ ላይ ማኅተም በማድረግ መቃብሩን አሽገውት’ ነበር። (ማቴዎስ 27:66) በዴቪድ ሊንተን ተርነር የተዘጋጀው በማቴዎስ መጽሐፍ ላይ ትንታኔ የሚሰጥ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ማኅተም የሮም ባለሥልጣናት የሚጠቀሙበት ዓይነት ማኅተም ከሆነ ‘በድንጋዩና በመቃብሩ አፍ መጋጠሚያ ላይ የሚደረግ የሸክላ ጭቃ ወይም ሰም’ ሊሆን ይችላል።
ማኅተሞች በጥንት ዘመን ስለነበረው ሕይወት ብዙ የሚጠቁሙት ነገር ስላለ የአርኪኦሎጂና የታሪክ ባለሙያዎች ለማኅተሞች ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ። እንዲያውም ሲጀሎግራፊ ተብሎ የሚጠራው የማኅተሞች ጥናት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጥናት መስክ ሆኗል።