ነቅታችሁ ጠብቁ!
2022፦ በነውጥ የተሞላ ዓመት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በ2022 ስለ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ችግር እና የሥነ ምህዳር ቀውስ የሚገልጹ ዘገባዎች የዜና አውታሮችን አጥለቅልቀው ነበር። የእነዚህን ክንውኖች እውነተኛ ትርጉም ሊነግረን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።
በ2022 የተከሰቱ ክንውኖች ያላቸው እውነተኛ ትርጉም
ባሳለፍነው ዓመት ውስጥ የተከሰቱት ክንውኖች፣ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህ ዘመን የጀመረው በ1914 ነው። በቅርቡ የተከሰቱትን ክንውኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናችን ከሚናገረው ነገር ጋር እስቲ እናወዳድር፦
“ጦርነት።”—ማቴዎስ 24:6
“2022 የጦርነት ሰቆቃ ወደ አውሮፓ የተመለሰበት ዓመት ነበር።” a
“ሩሲያ ዩክሬንን ወረረች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
“የምግብ እጥረት።”—ማቴዎስ 24:7
“2022፦ ታይቶ የማይታወቅ ረሃብ የተከሰተበት ዓመት።” b
“የዩክሬን ጦርነት የዓለምን የምግብ ቀውስ አባብሶታል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
“ቸነፈር።”—ሉቃስ 21:11
“የፖሊዮ ማገርሸት፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከሰትና የኮቪድ-19 መስፋፋት የተላላፊ በሽታዎችን አደገኝነት እና የሰው ልጆችን ደካማነት አጋልጠዋል።” c
“6 ሚሊዮን ሰዎች በኮቪድ ሕይወታቸውን አጥተዋል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
“የሚያስፈሩ ነገሮች።”—ሉቃስ 21:11
“የሙቀት ወጀብ፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳትና ጎርፍ። የ2022 የበጋ ወቅት በዓለም ዙሪያ ብዙ ውድመት ባስከተሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በቀጠፉ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው ባፈናቀሉ እንግዳ የአየር ንብረት ክስተቶች የተሞላ ነበር።” d
“ዓለማችን በከፍተኛ ሙቀት እየነደደች ነው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
“ብጥብጥ [ወይም “ረብሻ፤ ዓመፅ” ግርጌ]።”—ሉቃስ 21:9
“ዜጎች በኢኮኖሚ ቀውስ፣ በተለይ ደግሞ በዋጋ ግሽበት በመማረራቸው የተነሳ በ2022 ታይቶ በማይታወቅ መጠን የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።” e
“ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ቀጣዩ ዓመት ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?
በ2023 ምን እንደሚከሰት ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም። የምናውቀው ነገር ቢኖር በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በምድር ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ነው። (ዳንኤል 2:44) ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች መከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በማስወገድ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:9, 10
የኢየሱስ ክርስቶስን ምክር በመከተል፣ በዓለም ላይ የሚታዩ ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ‘ነቅተህ እንድትጠብቅ’ እናበረታታሃለን። (ማርቆስ 13:37) መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ስለሚሰጠው አስተማማኝ ተስፋ የበለጠ ማወቅ ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድታነጋግር እንጋብዝሃለን።
a AP News, “2022 Was Year the Horror of War Returned to Europe,” by Jill Lawless, December 8, 2022.
b World Food Programme, “A Global Food Crises.”
c JAMA Health Forum, “Living in an Age of Pandemics—From COVID-19 to Monkeypox, Polio, and Disease X,” by Lawrence O. Gostin, JD, September 22, 2022.
d Earth.Org, “What’s Behind the Record-Breaking Extreme Weather Events of Summer 2022?” by Martina Igini, October 24, 2022.
e Carnegie Endowment for International Peace, “Economic Anger Dominated Global Protests in 2022,” by Thomas Carothers and Benjamin Feldman, December 8, 2022.