በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

Surasak Suwanmake/Moment via Getty Images

ነቅታችሁ ጠብቁ!

በ2023 የበጋ ወራት በዓለም ዙሪያ እየታየ ያለው ከፍተኛ ሙቀት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በ2023 የበጋ ወራት በዓለም ዙሪያ እየታየ ያለው ከፍተኛ ሙቀት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቀው ከፍተኛ የሙቀት መጠን እና ከዚያ ጋር ተያይዞ በሚመጣው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት ለችግር ተዳርገዋል። እስቲ የሚከተሉትን ሪፖርቶች ተመልከት፦

  •   “በዓለማችን ላይ ባለፉት 174 ዓመታት ውስጥ በሰኔ ወር ላይ ከተመዘገበው የሙቀት መጠን ሁሉ ከፍተኛው የተመዘገበው በዚህ ዓመት የሰኔ ወር ላይ ነው።”—ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር፣ የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ዲፓርትመንት፣ ሐምሌ 13, 2023

  •   “በጣሊያን፣ በስፔን፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና በፖላንድ ከፍተኛ ሙቀት እየተመዘገበ ሲሆን በሲሲሊ እና በሳርዲኒያ ደሴቶች ደግሞ የሙቀት መጠኑ ጨምሮ እስከ 48 ዲግሪ ሴልሸስ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፤ ይህ እስካሁን ድረስ በአውሮፓ የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሊሆን ይችላል።”—የአውሮፓ የሕዋ ጥናት ኤጀንሲ፣ ሐምሌ 13, 2023

  •   “የፕላኔታችን ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ ዝናቡ ይበልጥ ኃይለኛ፣ ተደጋጋሚና ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል፤ ይህም ከበፊቱ የበለጠ አውዳሚ ጎርፍ ያስከትላል።”—ስቴፋን ኡለንብሩክ፣ በዓለም የሜትዮሮሎጂ ድርጅት የሥነ ውኃ እና የበረዶ ሽፋን ጥናት ዳይሬክተር፣ ሐምሌ 17, 2023

 እንዲህ ስላሉ ከባድ የአየር ሁኔታዎች የሚገልጹ ሪፖርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሄዳቸው ያሳስብሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ምን እንደሚል እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

ከባድ የአየር ሁኔታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ናቸው?

 አዎ። በዓለም ዙሪያ እየተመዘገበ ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ጨምሮ ሌሎች ከባድ የአየር ሁኔታዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን እንደሚከሰቱ ከተናገራቸው ትንቢቶች ጋር የሚስማሙ ናቸው። ለምሳሌ ኢየሱስ “የሚያስፈሩ ነገሮች” ወይም “ለየት ያሉ ክስተቶች” እንደሚኖሩ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደው የዓለም የሙቀት መጠን የተነሳ ብዙዎች የሰው ልጆች ምድርን ሊያጠፏት ይችላሉ ብለው ይሰጋሉ።

ምድር ሰው ሊኖርባት የማይችል ቦታ ትሆን ይሆን?

 በፍጹም። አምላክ ምድርን የፈጠራት የዘላለም መኖሪያችን እንድትሆን ነው፤ የሰው ልጆች እንዲያጠፏት አይፈቅድም። (መዝሙር 115:16፤ መክብብ 1:4) እንዲያውም “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [እንደሚያጠፋ]” ቃል ገብቷል።—ራእይ 11:18

 ምድር አውዳሚ በሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እንዳትጠፋ አምላክ ጥበቃ ሊያደርግላት እንደሚችል፣ ደግሞም እንደሚያደርግላት መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።

  •   “[አምላክ] አውሎ ነፋሱ እንዲቆም ያደርጋል፤ የባሕሩም ሞገዶች ጸጥ ይላሉ።” (መዝሙር 107:29) አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል አለው። በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆችን ለሥቃይ ለዳረጓቸው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታዎች መንስኤ የሆኑትን አካባቢያዊ ችግሮች ለማስተካከል አቅሙ አለው።

  •   “ምድርን እጅግ ፍሬያማ በማድረግና በማበልጸግ ትንከባከባታለህ።” (መዝሙር 65:9) በአምላክ በረከት ምድር ገነት ትሆናለች።

 አምላክ ምድርን እንደሚያድሳት ስለሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ምድርን የሚታደጋት ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።