በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

WBBR የተባለው የሬዲዮ ጣቢያ፣ 1924

ከታሪክ ማኅደራችን

ምሥራቹን ለብዙኃን ማሰራጨት

ምሥራቹን ለብዙኃን ማሰራጨት

 የካቲት 24, 1924 እሁድ ምሽት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች a ያቋቋሙት WBBR የተባለው አዲስ የሬዲዮ ጣቢያ ስርጭቱን ጀመረ። የመጀመሪያው ስርጭት ምን ይመስል ነበር? ስርጭቱ እነማን ጆሮ ደርሷል? የይሖዋ ምሥክሮች ‘የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር ለመስበክ’ አለ የተባለውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀማቸውን የቀጠሉትስ እንዴት ነው?​—ማቴዎስ 24:14

በWBBR የቴክኒክ ቁጥጥር ላይ እየሠራ ያለ ባለሙያ

“ስርጭቱን ጀመርን”

 ማታ 2:30 ላይ የጀመረው የመጀመሪያው ስርጭት ለሁለት ሰዓት ያህል አየር ላይ ቆይቷል። ፕሮግራሙ የተሰራጨው በስታተን አይላንድ፣ ኒው ዮርክ ከተገነባው አዲስ ስቱዲዮ ነበር። ዋና የስርጭት ባለሙያ የነበረው ወንድም ራልፍ ሌፍለር በስቱዲዮው ውስጥ “ውጥረት ሰፍኖ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “ስርጭታችን ሰዎች ጆሮ ይደርስ ይሆን?” የሚል ስጋት አድሮበት ነበር። ሆኖም “ሁሉም ነገር ይሳካል የሚል ተስፋ ይዘን ስርጭቱን ጀመርን” በማለት ተናግሯል።

 ያንን ታሪካዊ ስርጭት ያስተዋወቀው የጣቢያው ኃላፊ የነበረው ወንድም ቪክተር ሽሚት ነበር። ወንድም ቪክተር ተሰጥኦ ያላቸውን የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችና ዘማሪዎች በማስተዋወቅ ፕሮግራሙን ጀመረ፤ እነዚህ ሙዚቀኞች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። በቅድሚያ አንድ ወንድም በፒያኖ ክላሲካል ሙዚቃ ተጫወተ። በኋላም ኮራ ዌልማን ኢየሱስ ስለጠፋችው በግ በሰጠው ምሳሌ ላይ የተመሠረተ “ዘጠና ዘጠኙ” የተባለ መዝሙር ዘመረች። (ሉቃስ 15:4-7) ቀጥሎ ሌሎች መዝሙሮች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ የዘመረው “የንስሐ ልመና” የተባለው መዝሙር ይገኝበታል፤ ይህ መዝሙር ስለጠፋው ወይም ስለኮበለለው ልጅ በሚናገው ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው።​—ሉቃስ 15:11-25

WBBR ስርጭቱን በጀመረበት ቀን የሚተላለፉትን ፕሮግራሞች የሚያሳይ ዝርዝር

 በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በበላይነት ይከታተል የነበረው ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ፣ የሬዲዮ ጣቢያው “ለመሲሑ መንግሥት ጉዳዮች” እንዲውል የውሰና ንግግር አቀረበ። በንግግሩ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ሬዲዮ በዚህ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል መፍቀዱ ይህ መሣሪያ ስለ ታላላቅ ትንቢቶቹ ለሰዎች ለማስተማር እንዲያገለግል መፈለጉን ያሳያል።”

“አንዲት ፊደል እንኳ አላመለጠችኝም”

 የመጀመሪያው ስርጭት በሰሜን ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጆሮ ደርሷል። ከ320 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በሚገኘው በሞሪስቪል፣ ቬርሞንት ያለ አንድ አድማጭ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል፦ “ስርጭቱ በደንብ እየተላለፈ እንደሆነ ሳሳውቃችሁ በጣም ደስ ይለኛል። . . . በተለይ የራዘርፎርድ ድምፅ ጥርት ብሎ ነው የሚሰማው። . . . አንዲት ፊደል እንኳ አላመለጠችኝም።” በሞንቲቼሎ፣ ፍሎሪዳ ያለ አድማጭም እንኳ ስርጭቱን ማዳመጥ ችሏል! የአዲሱ የሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት ስኬታማ የነበረ ሲሆን ብዙ የአድናቆት ደብዳቤዎች ይጎርፉ ጀመር።

በWBBR ስቱዲዮ ጆሴፍ ራዘርፎርድ ማይክሮፎኑ ጋ ቆሞ። የፕሮግራሙ አስተዋዋቂ ቪክተር ሽሚት ነው

 ጣቢያው በተለይ በሰሜን ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ አድማጮች ለ33 ዓመት ያህል b የመንግሥቱን መልእክት ሲያሰራጭ ቆይቷል። አንዳንዴ ግን WBBR ከሌሎች ጣቢያዎች ጋር በመቀናጀት በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳና በሌሎች አገሮች ላሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አድማጮች ስርጭቱን ማዳረስ ችሏል። እንዲያውም የ1975 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል፦ “የስርጭቱ ተደራሽነት ከፍተኛ ጣሪያ ላይ በደረሰበት በ1933፣ መልእክቱን ወደ ስድስት አኅጉራት ለማሰራጨት የሚያገለግሉ 408 ጣቢያዎች የነበሩ ሲሆን 23,783 የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ማሰራጨት ተችሏል። . . . በእነዚያ ጊዜያት አንድ ሰው የሬዲዮ ጣቢያውን በመቀያየር በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ጊዜ ላይ የሚያሰራጯቸውን የመጠበቂያ ግንብ ስርጭቶች ማዳመጥ ይችል ነበር። ጣቢያዎቹን የሚከታተሉ ሰዎች ሁሉ፣ አምላክን የሚያስከብሩ እውነቶችን የማዳመጥ አጋጣሚ ነበራቸው።”

የቤት ወደ ቤት አገልግሎት ከሬዲዮ የበለጠ ውጤታማ ሆነ

 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች WBBR የተባለውን የሬዲዮ ጣቢያ መጠቀም በጀመሩበት ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የነበሩት የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር በአማካይ 1,064 ገደማ ነበር። የሬዲዮ ስርጭቶቹ መኖር በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ የነበረውን ቡድን በእጅጉ ረድቶታል። ሆኖም በ1957 የአስፋፊዎች ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ 187,762፣ በመላው ዓለም ደግሞ 653,273 ደርሶ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በሚሰጠው ሥልጠና ምክንያት እነዚያ ቀናተኛ ወንድሞችና እህቶች ከቤት ወደ ቤት በሚሰጠው ምሥክርነትም ሆነ በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ይበልጥ ውጤታማ እየሆኑ ነበር።

 ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች እንዲህ ያሉትን አዎንታዊ ለውጦች ሲያዩ የሬዲዮ ስርጭቶች በየቤቱ ከሚሰጠው ምሥክርነት አንጻር ያላቸውን ውጤታማነት ለመገምገም ተነሳሱ። ውጤቱ ምን ሆነ? በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሥር ያለውንና ማኅበሩ የሚጠቀምበትን ብቸኛውን የሬዲዮ ጣቢያ ማለትም WBBRን ለመሸጥ ተወሰነ። ጣቢያው ሚያዝያ 15, 1957 ተሸጠ። ከአንድ ቀን በፊት በተላለፈው ልዩ የስንብት ፕሮግራም ላይ ናታን ኖር ጣቢያው የሚሸጠው ለምን እንደሆነ ጥያቄ ቀረበለት። እሱም የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እንዲጨምር ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት እንደሆነ ገለጸ። “የWBBR ስርጭቶች ብዙዎችን እንደጠቀሙ አይካድም” በማለት ተናገረ። አክሎም “ሆኖም WBBR በሚሰራጭባቸው አካባቢዎች ያለው እድገት በዓለም ዙሪያ ይህ ስርጭት በማይደርስባቸው አካባቢዎች ካለው እድገት ያን ያህል የተለየ አይደለም” አለ። በመሆኑም ወንድሞች ከሬዲዮ ስርጭት ይልቅ ከቤት ወደ ቤት በመስበክ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተገነዘቡ። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች የመገናኛ ብዙኃንን መጠቀማቸውን በዚያው አላቆሙም። ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ይህን ዘዴ በአዲስ መልክ ጥቅም ላይ ማዋል ጀመሩ።

በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን የምናሰራጭባቸው ዘዴዎች

 ጥቅምት 6, 2014 በይሖዋ ድርጅት ታሪክ ውስጥ አስደናቂ እመርታ የታየበት ነው፤ በዚያ ዕለት JW ብሮድካስቲንግ የተባለው የኢንተርኔት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥራ ጀመረ። አሁን የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች ሰዎች የድረ ገጽ ማሰሻዎችን፣ JW ላይብረሪ የተባለውን አፕሊኬሽን፣ የቪዲዮ ማሰራጫ መሣሪያዎችን ወይም የሳተላይት ዲሾችን በመጠቀም ወርሃዊ ብሮድካስቶችን ማየት ይችላሉ። c በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ግን የይሖዋ ሕዝቦች የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶችን በሚገባ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። እንዴት?

የJW ብሮድካስቲንግ የመጀመሪያ ስርጭት፣ ጥቅምት 2014

 ባለፉት ዓመታት የይሖዋ ድርጅት የይሖዋ ምሥክሮች ንብረት ያልሆኑ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በመጠቀም ኢንተርኔት እንደ ልብ በሌለባቸው አካባቢዎች ሳምንታዊ ስብሰባዎችንና የክልል ስብሰባዎችን ማስተላለፍ ችለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች እነዚህን ስርጭቶች ተከታትለዋል፤ ከእነዚህ መካከል ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች ይገኙበታል። ለምሳሌ ከ2021 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ የሬዲዮ ጣቢያ ኃላፊዎች፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ለስብሰባዎቻችን ያላቸውን አድናቆት እንደገለጹ በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አሳውቀዋል። እንዲያውም በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በታንዛኒያ የሚገኙ አንዳንድ አድማጮች መጽሐፍ ቅዱስን በግል ለመማር ጥያቄ አቅርበዋል።

 የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን መልእክት በዓለም ዙሪያ ለማድረስ የሚጠቀሙባቸው ዋነኛ ዘዴዎች ግን ከቤት ወደ ቤት የሚሰጠው ምሥክርነት፣ የጽሑፍ ጋሪዎች እና jw.org የተባለው ድረ ገጽ ናቸው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ1,080 በሚበልጡ ቋንቋዎች በነፃ ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪም ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘትና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን የት እንደሚካሄዱ ማወቅ ይችላሉ። ዕድሜ ለእነዚህ ጥረቶችና ዝግጅቶች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ማሰራጨት ችለዋል! በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ምሥራቹ “በመላው ምድር” እየተሰበከ ነው።​—ማቴዎስ 24:14

a በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም መጠቀም ጀመሩ።

b ለተወሰነ ጊዜ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች አውስትራሊያ እና ካናዳን ጨምሮ በሌሎች አገሮችም የሬዲዮ ጣቢያዎች ነበሯቸው።