በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

በተከፋፈለ አገር ውስጥ በአንድነት መኖር

በተከፋፈለ አገር ውስጥ በአንድነት መኖር

 ከ1948 እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ a የተባለ የፖለቲካ ሥርዓት ትከተል ነበር። በእነዚህ ዓመታት ብዙዎች ከእነሱ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይይዙ ነበር። በአፓርታይድ ሥርዓት ሥር በነበረው ክፍፍል መሠረት “ክልስ” (ከሌላ ዘር ጋር የተዳቀለ) በሚለው ፈርጅ ተመድቦ የነበረ ካሊ የተባለ ግለሰብ “ነጭ ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ እርስ በርሳቸው የተከፋፈሉ ነበሩ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

 በደቡብ አፍሪካ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያየ ዘር ያላቸው ናቸው። ታዲያ የአፓርታይድ ሥርዓትን ያሳለፉት እንዴት ነበር? ደግሞስ እነሱ ያሳለፉት ታሪክ ለእኛ ምን ትምህርት ይዞልናል?

ክፍፍሉ ያስከተለውን አደጋ መጋፈጥ

 በደቡብ አፍሪካ የተጣለውን የክፍፍል ሥርዓት የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ያደራጁ ነበር። የመንግሥትን ፖሊሲዎች ከተቃወሙት መካከል አብዛኞቹ ታስረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ተገድለዋል። ይህም ተቃዋሚዎቹን ይበልጥ አስቆጣቸው። በሌላ በኩል ግን የይሖዋ ምሥክሮች የአገሪቱን ሕግ ይታዘዙ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ በተቃውሞ ሰልፎችም ሆነ መንግሥትን ለመገልበጥ በሚደረጉ ጥረቶች አልተሳተፉም። በዚህ መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ‘ለበላይ ባለሥልጣናት እንደሚገዙ’ አሳይተዋል።—ሮም 13:1, 2

 የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን እንዲያላሉና አንዱን ወገን እንዲይዙ በተደጋጋሚ ጫና ተደርጎባቸዋል። ሆኖም ወገን ቢይዙ ኖሮ፣ ዓመፅ የተሞላባቸውን ፖለቲካዊ ግጭቶች ለመደገፍ አልፎ ተርፎም መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን ለመዋጋት ሊገደዱ ይችሉ ነበር። ቴምሲ የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “በ1976 በተቀሰቀሰው ግጭት ብዙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሕዝባዊ ዓመፆችን እንዲቀላቀሉ ተገደው ነበር። በዓመፁ የሚካፈሉ ተማሪዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ቡድኑን የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን ይፈልጋሉ። አንድ ሰው ፈቃደኛ ካልሆነ ቤቱን ሊያቃጥሉበት ብሎም እስኪሞት ድረስ ሊደበድቡት ይችላሉ።” የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆነ አንድ ሰው ቴዎፊለስ ለተባለ የይሖዋ ምሥክር “ነጮቹን ድል ካደረግን በኋላ፣ ቀጥሎ ወደ አንተ መምጣታችን አይቀርም፤ ምክንያቱም ለአገርህ አልተዋጋህም” ብሎት ነበር።

በተከፋፈለ አገር ውስጥ በአንድነት መሰብሰብ

 በደቡብ አፍሪካ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአፓርታይድ ሥርዓት የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ቢያስከትልባቸውም ለአምልኮ በአንድነት መሰብሰባቸውን አላቆሙም። (ዕብራውያን 10:24, 25) የፖለቲካ ሥርዓቱ ብዙዎችን ለድህነት ዳርጎ ስለነበር አንዳንድ ጉባኤዎች የስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት አቅሙ አልነበራቸውም። b ኤንቨር የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለብዙ ዓመታት፣ ጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኙ የስብሰባ ቦታዎችን ማግኘት አልቻልንም ነበር። ስለዚህ አባቴ፣ ወንድሞች ቤታችንን ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዲጠቀሙ ሐሳብ አቀረበ። በሳምንት ሁለቴ ቤታችንን ወደ ስብሰባ አዳራሽነት እንቀይረዋለን። ቤታችን ውስጥ ከ100 በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ጊዜ ነበር። ስብሰባዎቹ ካለቁ በኋላ፣ ለተሰብሳቢዎቹ ሻይ ቡና ማቅረብ ያስደስተናል።”

ሚያዝያ 1950 ጥቁር እና ነጭ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ ተሰብስበው

በ1980 በጆሃንስበርግ ባለው ራንድ ስታዲየም የተካሄደ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች የተገኙበት ስብሰባ

 ወንድሞች የአፓርታይድ ሥርዓት የፈጠረባቸውን እንቅፋት ለመወጣት አስደናቂ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ አንድ ነጭ ወንድም ሊምፖፖ በተባለ ግዛት ጥቁሮች ብቻ በሚኖሩበት አካባቢ በሚካሄድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ንግግር ተሰጥቶት ነበር፤ ሆኖም ወደዚያ እንዲገባ አልተፈቀደለትም። ይሁንና ጥቁሮች ብቻ ከሚኖሩበት ከዚህ አካባቢ አጠገብ አንድ እርሻ የነበረ ሲሆን የዚህ እርሻ ባለቤት ደግሞ ነጭ ነው፤ ስለዚህ ወንድም ወደዚህ ሰው ሄዶ ከእሱ ጋር ስምምነት አደረገ። በወረዳ ስብሰባው ላይ ተሰብሳቢዎቹ ከዚህ ገበሬ አጥር ውጭ በጥቁሮቹ በኩል ሆነው፣ ተናጋሪው ደግሞ በእርሻው በኩል ሆኖ ንግግር ሊሰጥ ቻለ።

በዘር በተከፋፈሉ ክልሎች ማገልገል

 በአፓርታይድ ሥርዓት ሥር የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች የየራሳቸው መኖሪያ አካባቢ ይመደብላቸው ነበር። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ጉባኤ ክልል ውስጥ የሚኖሩት ተመሳሳይ ዘር ያላቸው ሰዎች ናቸው። የአፓርታይድ ሥርዓት የይሖዋ ምሥክሮች፣ አስፋፊዎችን ለመስክ አገልግሎት በሚያደራጁበት መንገድ ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ለምሳሌ ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ ክልሎች ላይ ማገልገል የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች ነበሩት። በወቅቱ በነበረው የዘር ክፍፍል መሠረት “ሕንዳዊ” በሚለው ፈርጅ የተመደበ ክሪሽ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ነጭ ያልሆኑ ሰዎች ሊያድሩባቸው የሚችሉ ቦታዎችን ማግኘት ከባድ ነበር። ስለዚህ መኪናችን ውስጥ ወይም ዛፍ ሥር እናድራለን። ጠዋት ላይ በነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ውስጥ ወዳሉ መታጠቢያ ቤቶች ሄደን እንታጠባለን። አንዳንዴ ግን እነዚህ መታጠቢያ ቤቶችም እንኳ ‘ለነጮች ብቻ’ የሚል ምልክት ይለጠፍባቸዋል። ያም ሆኖ አስፋፊዎች አገልግሎቱን ይደግፉ የነበረ ሲሆን በገጠራማ አካባቢዎች ላሉ ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች መስበክ ያስደስታቸው ነበር።”

በ1981 የተለያየ ዘር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ገጠራማ አካባቢ ሲሰብኩ

 እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የይሖዋ ሕዝቦች በቁጥር ማደጋቸውን ቀጠሉ። በ1948 የአፓርታይድ ሥርዓት ሲጸድቅ በደቡብ አፍሪካ 4,831 አስፋፊዎች ነበሩ። በ1994 ይህ ሥርዓት ባበቃበት ወቅት ግን የአስፋፊዎች ቁጥር 58,729 ደርሶ ነበር። ይህ ቁጥር ማደጉን የቀጠለ ሲሆን በ2021 በደቡብ አፍሪካ 100,112 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

በጥላቻ ተከቦ በፍቅር አንድ መሆን

 በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት ሥር የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች ተለያይተው እንዲኖሩ ይገደዱ ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ ተጽዕኖ ነፃ አልነበሩም። ያም ቢሆን የተለያየ ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህን የሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በማስተማርና በመከተል ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) በጥላቻ ቢከበቡም በፍቅር አንድ ሆነው ነበር።—ዮሐንስ 13:34, 35

 በ1993 የይሖዋ ምሥክሮች በደቡብ አፍሪካ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች የተገኙበት ትልቅ ስብሰባ አድርገው ነበር። አንድ ከፍተኛ ቦታ ያለው የፖለቲካ መሪ የደቡብ አፍሪካ የይሖዋ ምሥክሮች አየር መንገድ ሄደው ከዓለም ዙሪያ ለመጡ ልዑካን ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርጉላቸውና ሲያቅፏቸው ተመለከተ። ከዚያም “የእናንተ ዓይነት አንድነት ቢኖረን ኖሮ ችግሮቻችንን ገና ድሮ መፍታት በቻልን ነበር” በማለት ተናገረ።

በ1955 ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጣው ሚልተን ሄንሸል የተለያየ ዘር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በተገኙበት ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርብ

በ1986 በደቡብ አፍሪካ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጥቁርና ነጭ ወንድሞች አብረው ሲሠሩ

በእውነት ውስጥ ለረጅም ዓመታት የቆዩት ቶማስ ስኮሳና (በስተ ግራ) እና አልፍሬድ ስቲንበርግ በ1985 በትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተው

በ1985 የተለያየ ዘር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ምግብ ሲያቀርቡ

በ2011 በጆሃንስበርግ ኤፍኤንቢ ስታዲየም በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከተለያየ ዘር የተውጣጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ተሰብስበው

a አፓርታይድ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች ተለያይተው እንዲኖሩ የሚያስገድድ ሥርዓት ነበር። ይህ ሥርዓት የአንድን ሰው ዘር መሠረት በማድረግ ግለሰቡ ምን ዓይነት ትምህርት መማር፣ ምን ዓይነት ሥራ መሥራት፣ የት መኖርና ማንን ማግባት እንደሚችል ይወስናል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በ2007 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “አፓርታይድ ምን ነበር?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b ከ1999 ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የተሰበሰቡ መዋጮዎች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች የስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባትና ለማደስ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።