በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

በከባድ ጊዜ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ቀጥለዋል

በከባድ ጊዜ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ቀጥለዋል

 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ውጥንቅጡ ወጥቶ ነበር። በሌላ በኩል ግን የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች የነበሩ በርካታ ሰዎች ነፃ የተለቀቁት በዚሁ ወቅት ነው። ያም ሆኖ ለእነዚህ ሰዎች ሕይወት ከባድ ነበር። እንደ ሌሎች በርካታ ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ከምግብ፣ ከልብስ፣ ከመጠለያና ከሌሎች መሠረታዊ ነገሮች እጦት ጋር መታገል ነበረባቸው። እህት ካረን ሃርቱንግ እንዲህ ብላለች፦ “የመኖሪያ ቤት እጦቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ሰዎች ዘመዶቻቸውን ማስጠጋት ወይም የቤታቸውን የተወሰነ ክፍል ከፍለው ማከራየት አስፈልጓቸዋል።” ለሰባት ዓመት ተኩል ያህል በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የቆየችው እህት ጌርትሩድ ፖይትጺንገር በቁሳቁስ ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ ለመኖርና ወንበር ላይ ለመተኛት ተገዳለች። a

 በጦርነት በታመሱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞችን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ምን እርምጃ ተወስዷል? እኛስ ከጦርነቱ በኋላ በነበረው ከባድ ጊዜ ከኖሩት ሰዎች ምን ትምህርት እናገኛለን?

የወንድሞችን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት

 የይሖዋ ድርጅት በአውሮፓ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች እርዳታ ለመስጠት ፈጣን እርምጃ ወስዷል። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉት ናታን ኖር እና ሚልተን ሄንሸል ወንድሞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለመገምገም አካባቢውን ጎበኙ። ከኅዳር እስከ ታኅሣሥ 1945 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ቤልጅየም፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ እና ፊንላንድ ተጓዙ። ወንድም ኖር “ጦርነቱ በአህጉሩ ላይ ያስከተለውን ውድመት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓይናችን ተመልክተናል” በማለት ሪፖርት አድርጓል።

ታኅሣሥ 21, 1945 ናታን ኖር በሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች ንግግር ሲያቀርብ

 ወንድም ኖር በወቅቱ ወደ ጀርመን ለመግባት ፈቃድ አላገኘም። በመሆኑም በጀርመን ያለው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የነበረው ኤሪክ ፍሮስት ወንድም ኖርን ለማግኘት ወደ ሌላ አገር ተጓዘ። b ወንድም ኤሪክ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል፦ “ወንድም ኖር ጠቃሚ ምክሮችን የሰጠን ሲሆን የምግብና የልብስ እርዳታ እንደምናገኝም ቃል ገባልን። ብዙም ሳይቆይ ዱቄት፣ ስብ፣ ሲናር እና ሌሎች ምግቦችን የያዘ ትልቅ ጭነት ወደ ጀርመን ገባ። በተጨማሪም በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞች እንደ ሙሉ ልብስ፣ የውስጥ ሱሪና ጫማ ያሉ ቁሳቁሶችን የያዙ ትላልቅ ሣጥኖችን ላኩልን።” ወንድሞችና እህቶች እነዚህ እርዳታዎች ሲሰጧቸው ከአመስጋኝነታቸው የተነሳ አለቀሱ። ደግሞም በአንድ ሪፖርት ላይ እንደገለጸው “ይህ እርዳታ፣ አንዴ ተደርጎ የቆመ አይደለም። የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙ ጭነቶች ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ወደ ጀርመን መላካቸውን ቀጥለዋል!” c

በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አውሮፓ በእርዳታ የሚላኩትን ልብሶች ሲያስተካክሉ

በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮራቸውን ቀጥለዋል

 ወንድሞች የኑሮ ሁኔታቸው መሻሻል ከጀመረ በኋላም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮራቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ረገድ የረዳቸው ምንድን ነው?

በ1954 ዩርገን ራንድል (ከፊት በስተ ግራ) ኦስትሪያ በሚገኘው ስፒታል አን ደር ድሮ በተባለው ጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር

 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ነበራቸው። (ኤፌሶን 5:15, 16) በጦርነቱ ወቅት ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ማግኘትና መንፈሳዊ ፕሮግራሞቻቸውን ቋሚ ማድረግ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ግን እንደ ቀድሞው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ማድረግና በስብከቱ ሥራ መካፈል ቻሉ። በኦስትሪያ የሚኖረው ዩርገን ራንድል እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ኢንፎርማንት d የተባለው ጽሑፍና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾቻችን፣ ቋሚ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖረን ያበረታቱን ነበር።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረታችን ያረፈው በይሖዋ፣ በኢየሱስ፣ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እና በአገልግሎት ላይ ብቻ ነበር። እንደ ቴሌቪዥን ያሉ ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮች አልነበሩም።”

 እህት ኡልሪከ ክሮሎፕ እንዲህ ብላለች፦ “አንድን መንፈሳዊ ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀት ሳጠና ምን ያህል ደስታ ይሰማኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ባለቤቴ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ሆኖኛል። አዲስ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እንደደረሰን ሁሉን ነገር ትቶ ያጠናው ነበር።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካረን እንዲህ ብላለች፦ “በጦርነቱ ወቅት ቁሳዊ ንብረት ምን ያህል በፍጥነት ሊጠፋ እንደሚችል ተመልክተናል። መንፈሳዊውን ምግብ ግን እንደ ልብ ማግኘት ባንችልም ተቋርጦብን አያውቅም። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ክሷቸዋል።”

ኡልሪከ ክሮሎፕ

 ወደ አገልግሎታቸው ተመለሱ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ጦርነቱ የይሖዋ ሕዝቦች በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ እንደ ልባቸው እንዳይካፈሉ አግዷቸው ነበር። ፍሪድሄልም የተባለ ወንድም፣ ከጦርነቱ በኋላ “ሁላችንም ወዲያውኑ ወደ አገልግሎታችን ተመለስን” በማለት ተናግሯል። ኡልሪከ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ለባለቤቴ ቤተሰቦች የመንግሥቱን መልእክት ለመጀመሪያ ጊዜ የነገራቸው ወንድም የማጎሪያ ካምፕ ዩኒፎርሙን እንኳ ገና አላወለቀም ነበር! መስበክ የጀመረው ልክ ከካምፑ እንደወጣ ነው።” ዩርገን እንዲህ ብሏል፦ “ከጦርነቱ በኋላ ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል፣ በቅንዓት ተሞልቶ ነበር። ብዙ ወጣት ወንድሞችና እህቶች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገቡ።”

 “የቦምብ ፍንዳታ በተከሰተባቸው ከተሞች፣ የኑሮ ሁኔታው በጣም አስከፊ ነበር” በማለት ኡልሪከ ተናግራለች። ብዙ ሰዎች የሚኖሩት በፈራረሱ ቤቶች ውስጥ ነበር! ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ሰዎች አግኝተው ሊሰብኩላቸው የቻሉት እንዴት ነው? ቤተሰቦቿ ከጦርነቱ በኋላ ወደ እውነት የመጡት ኡልሪከ “የምንሄደው የመብራት ጭላንጭል ወይም ከቤቶቹ የሚወጣውን ጭስ እየፈለግን ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

 እርስ በርስ ተበረታተዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:11) በጦርነቱ ወቅት ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል። ከጦርነቱ በኋላ ግን የደረሰባቸውን መከራ እያሰቡ ከመብሰልሰል ይልቅ እርስ በርስ ለመበረታታት ጥረት አድርገዋል። በእርግጥም ‘ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታቸው’ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ያዕቆብ 1:2, 3) በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “ለተወሰነ ጊዜ ያህል በማጎሪያ ካምፖች የቆየው የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን የይሖዋን እጅ ስላዩባቸው በርካታ አጋጣሚዎች የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን ይነግረን ነበር። እነዚህ ተሞክሮዎች እምነታችንን በእጅጉ አጠናክረውታል።”

 ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ወንድሞች፣ ይሖዋ “በካምፕ ውስጥ ሳሉ የረዳቸውና ጸሎታቸውን የመለሰላቸው እንዴት እንደሆነ” መለስ ብለው በማስታወስ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ዝምድና አጠናክረው እንደቀጠሉ ዮሐንስ ተናግሯል። በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከእስር ነፃ የወጡት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ እንደማንበብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደመገኘትና በመስክ አገልግሎት እንደመካፈል ያሉ ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችን ይዘው ቀጥለዋል። በ1946 በኑረምበርግ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኘችው ኤሊዛቤት የእነዚህን ወንድሞችና እህቶች ሁኔታ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ሲታዩ ከሲታና ደካማ ነበሩ። ተሞክሯቸውን ሲነግሩን ግን ‘በመንፈስ ይቃጠሉ ነበር።’”​—ሮም 12:11

ካረን ሃርቱንግ

 ከእምነት ባልንጀሮቻቸው አልራቁም። (ሮም 1:11, 12) በጦርነቱ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ስደት ይደርስባቸው ስለነበር እርስ በርስ በነፃነት መገናኘት አይችሉም ነበር። ካረን እንደተናገረችው “የባለሥልጣናቱን ትኩረት በመሳብ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ስለሚፈሩ እርስ በርስ የሚገናኙት አልፎ አልፎ ነበር።” ጦርነቱ ሲያበቃ ግን ይህ ሁሉ ነገር ተቀየረ። ፍሪድሄልም እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት አብረው ነበር። ሁሌም ለስብሰባዎችና ለአገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣሉ።”

 በጀርመን የሚኖር ዲትሪክ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ጦርነቱ እንዳበቃ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “መኪና ያላቸው ወንድሞች ጥቂት ነበሩ። ስለዚህ ወደ ስብሰባ የምንሄደው በእግራችን ነበር፤ ደግሞም በዛ ብለን ነበር የምንሄደው። በዚህ መልኩ አዘውትረን አብረን መሆናችን በመካከላችን ያለውን ቅርርብ አጠናክሮታል። ልክ እንደ ቤተሰብ አቀራርቦናል።”

የምናገኘው ትምህርት

 በዛሬው ጊዜ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነት፣ በስደትና በኑሮ ውድነት ምክንያት ችግሮችን እየተጋፈጡ ይገኛሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሆኖም ከልክ በላይ ልንጨነቅ አይገባም። ለምን? በናዚ አገዛዝ ሥር በጀርመን የነበሩ ታማኝ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተዉት ምሳሌ አምላካችን አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት እኛን መደገፉን እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ይሰጡናል። እንግዲያው እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን አስተሳሰብ ለመያዝ ጥረት እናድርግ፦ “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”​—ዕብራውያን 13:6

a የእህት ፖይትጺንገርን የሕይወት ታሪክ ለማንበብ “በጀርመን ከጦርነቱ በኋላ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም” የሚለውን ርዕስ በእንግሊዝኛ ተመልከት።

b የወንድም ፍሮስትን የሕይወት ታሪክ ለማንበብ “በአምላክ በማመን ከአንባገነናዊ ሥርዓት ነፃ መውጣት” የሚለውን ርዕስ በእንግሊዝኛ ተመልከት።

c ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ስለተደረገው የእርዳታ አገልግሎት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ምርጣቸውን ሰጥተዋል” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! በተባለው መጽሐፍ ገጽ 211, 218 እና 219 ላይ የሚገኙትን ሣጥኖች ተመልከት።

d በአሁኑ ጊዜ ጉባኤዎች የሚጠቀሙት ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ የተባለውን ጽሑፍ ነው