ከታሪክ ማኅደራችን
ኑሮ ከባድ ቢሆንም ይሖዋን ማገልገል
በበርካታ አገሮች የኑሮ መወደድ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ የብዙዎችን ሕይወት ከባድ አድርጎታል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች የኑሮ ጉዳይ ከልክ በላይ አያስጨንቃቸውም፤ ይሖዋ አገልጋዮቹን ‘ፈጽሞ እንደማይተው’ የገባው ቃል ያረጋጋቸዋል። (ዕብራውያን 13:5) ይሖዋም በተደጋጋሚ ይህን ቃሉን እንደሚጠብቅ አሳይቷል። በፊሊፒንስ የታየው ሁኔታ ይህን ያረጋግጣል፤ ብዙዎቹ የዚህች አገር ነዋሪዎች አሁንም ከድህነት አልተላቀቁም። በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ዓመታት ግን ሁኔታው ከዚህም የከፋ ነበር።
ቪኪ a የተባለች እህት ያንን ጊዜ ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “የምበላው ስለሌለኝ የማለቅስበት ጊዜ ነበር። አንዳንዴ ከሩዝ፣ ከጨውና ከውኃ በስተቀር ምንም አይኖረንም።” ፍሎረንሲዮ የተባለ አንድ ወንድም ሥራ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “ያለኝ ሦስት ሸሚዝና ሦስት ሱሪ ብቻ ነበር። በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እያፈራረቅሁ የምለብሰው እነዚህኑ ነው።” ታዲያ የይሖዋ ሕዝቦች ያን የችግር ጊዜ እንዴት አለፉት? በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ከፊታችን ከባድ ጊዜ የሚጠብቀን እኛስ ከእነሱ ምሳሌ ምን እንማራለን?
በይሖዋ ታምነዋል
በፊሊፒንስ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው እርግጠኞች ነበሩ። (ዕብራውያን 13:6) ደግሞም ተንከባክቧቸዋል፤ አንዳንዴ እንዲህ ያደረገላቸው ጨርሶ ባልጠበቋቸው መንገዶች ነው። ለምሳሌ እህት ሴሲል እንዲህ ብላለች፦ “የነበረችንን አንዲት እፍኝ ሩዝ ለቁርስ ሠራናት፤ አራት አባላት ያሉት ቤተሰባችን ከዚያ በኋላ የሚበላው አልነበረም። ስለዚህ ይሖዋ በዚያ ዕለት የሚያስፈልገንን እንዲሰጠን ጸለይን። ገና ቁርሳችንን እንኳ በልተን ሳንጨርስ አንድ ወንድም አምስት ኪሎ ሩዝ ይዞልን መጣ። ይሖዋ ላደረገልን ለዚህ ነገር ከተሰማን አመስጋኝነትና ከደስታችን የተነሳ አለቀስን። እንዲህ የመሰሉ ብዙ ገጠመኞች ነበሩን።”
ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ አድርገዋል። (ምሳሌ 2:6, 7) ለምሳሌ ያን ጊዜ አዲስ ተጠማቂ የነበረችው አርሴሊታ በወቅቱ አላገባችም ነበር፤ ኑሮ በጣም ስለከበዳት የልቧን ግልጥልጥ አድርጋ ለይሖዋ ነገረችው። ከዚያም በምሳሌ 10:4 ላይ አሰላሰለች። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ሥራ የፈቱ እጆች ያደኸያሉ፤ ትጉ እጆች ግን ብልጽግና ያስገኛሉ።” ይህን ጥቅስ ተግባራዊ በማድረግ ጓሮዋን ለማልማት ወሰነች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ጥረቴን ባርኮልኛል። እንዲያውም ያገኘሁት ምርት ቀለቤን ከመቻል ባለፈ የትራንስፖርት ወጪዬን ለመሸፈን አስችሎኛል።”
መሰብሰባቸውን ቸል አላሉም
ወንድሞች መሬት የሚገዙበትና የስብሰባ አዳራሽ የሚገነቡበት ገንዘብ አልነበራቸውም። ይህ ግን እንድንሰበሰብና እርስ በርሳችን እንድንበረታታ የተሰጠንን መመሪያ ችላ እንዲሉ አላደረጋቸውም። (ዕብራውያን 10:24, 25) ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን የሚችሉትን አድርገዋል። ለምሳሌ ዲቦራ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እኔና አብራኝ የምታገለግለው አቅኚ እህት ለስብሰባ የምትሆን ትንሽ ጎጆ ሠራን። የዘንባባ ቅጠል በመጠቀም ጣሪያውን ከደንነው፤ እንዲሁም በኮኮናት ዛፍ ቅጠል ግድግዳውን ሠራን። የዘንባባ ግንድ አጋድመን ደግሞ መቀመጫ አደረግነው። በዚህ ሁኔታ ስድስት ሆነን እንሰበሰብ ነበር።”
ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ወንድሞች የሚሰበሰቡት በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር። ቨርጂኒያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቤታችን ትንሽ ስትሆን የተሠራችው ከሳርና ከቀርከሃ ነበር። ሁልጊዜ ቅዳሜ ቅዳሜ በማግስቱ ለሚደረገው ስብሰባ ቦታውን ለማዘጋጀት የቤታችንን ዕቃዎች ጥግ ጥግ እናስይዝ ነበር።” ስብሰባ የሚደረግበት ሌላኛው ቤት ደግሞ ጣሪያው ያፈስ ነበር። ወንድም ኖኤል እንዲህ ብሏል፦ “ሲዘንብ ጠፈጠፉ እንዳያበሰብሰን ባልዲ እንደቅን ነበር። ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን ጋር ለአምልኮ ስንሰበሰብ ግን እነዚህ ምቾት የሚነሱ ነገሮች መኖራቸው እንኳ ብዙም ትዝ አይለንም።”
በቅንዓት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል
ድህነት እነዚህ ክርስቲያኖች ለአገልግሎት የነበራቸው ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ አላደረገም። በኔግሮስ ደሴት የምትኖረው ሊንዲና እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “ቤተሰባችን ሰፊ ነበር፤ ሥራ ያለው ግን አባቴ ብቻ ነው። ስለዚህ ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ የምናጣበት ጊዜ አለ። እናም በአብዛኛው ወደ ክልላችን የምንሄደው በእግራችን ነበር። ተሰባስበን ስለምንሄድ ግን ደስ ይለናል። ይሖዋም በጥረታችን እንደሚደሰት እርግጠኞች ነበርን።”
ርቀው ወደሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች ለስብከት መሄድ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ምክንያቱም በአብዛኛው ወደነዚህ አካባቢዎች የሚሄድ መጓጓዣ አልነበረም። በሉዞን ደሴት የምትኖረው ኤስተር እንዲህ ብላለች፦ “ከ6 እስከ 12 የምንሆን ወንድሞችና እህቶች ተሰባስበን በማለዳ እንወጣለን፤ ምክንያቱም ብዙ ኪሎ ሜትሮች በእግር መጓዝ ይኖርብናል። ሙሉ ቀን ስናገለግል እንውላለን። ዛፍ ጥላ ሥር ሆነን የቋጠርነውን ምግብ እንመገባለን። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ግን ምግብ ይዘው ለመምጣት አቅማቸው አይፈቅድላቸውም፤ ሆኖም አይቀሩም። እኛም ‘ምንም አታስቡ፤ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ምግብ አለን’ እንላቸው ነበር።”
ይሖዋ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ያገለገሉትን እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ባርኳቸዋል። ለምሳሌ በ1970 በፊሊፒንስ የነበሩት አስፋፊዎች ቁጥር 54,789 ነበር። በ1989 ይህ ቁጥር በእጥፍ ገደማ አድጎ 102,487 ደረሰ። በ2023 ደግሞ በፊሊፒንስ የሚኖሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነዋሪዎች ቁጥር 253,876 ደርሷል።
“ድህነት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር አላቀዘቀዘውም”
በዚህ ከባድ የድህነት ወቅትም እንኳ ወንድሞችና እህቶች በመንፈሳዊ ማደጋቸውን ቀጥለዋል። ወንድም አንቶንዮ “ድህነት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር አላቀዘቀዘውም” ብሏል። እህት ፌይ አባድ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ባጋጠመን ወቅት ይሖዋን የሙጥኝ ብለናል፤ ይህም ቀላል ሕይወት መምራት የሚያስገኘውን ደስታ እንድናጣጥም አስችሎናል። ልጆቻችንም በይሖዋ መታመንን ተምረዋል።”
በሳማር ደሴት የምትኖረው ሉሲላ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን የምታገለግል ከሆነ ድህነት ያን ያህል ከባድ ችግር አይደለም። የአምላክን ፈቃድ ስናስቀድም ባለን መርካትና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ እንችላለን። እኔ በበኩሌ ጥናቶቼ ይሖዋን ሲያውቁና አብረውኝ በአቅኚነት ሲያገለግሉ ለመመልከት በቅቻለሁ።”
እኛም ከፊታችን አስቸጋሪ ጊዜያት ይጠብቁናል፤ በመሆኑም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለውን የወንድም ሩዶልፎን ሐሳብ በልባችን መያዛችን ይጠቅመናል። ሩዶልፎ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አስቸጋሪ የነበሩትን የ1970ዎቹንና የ1980ዎቹን ዓመታት በማለፌ የይሖዋን እጅ ለማየት አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ገንዘብ ባይኖረኝም እንዳጣሁ ተሰምቶኝ አያውቅም። ይሖዋ ጥሩ አድርጎ ተንከባክቦኛል። ያሳለፍኩትን ሕይወት ሳስብ የሚቆጨኝ ነገር የለም፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም ደግሞ ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት’ ለማግኘት በጉጉት እጠባበቃለሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:19
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።