በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

የኒው ዚላንድ የይሖዋ ምሥክሮች—ሰላማዊ እና ታማኝ ክርስቲያኖች

የኒው ዚላንድ የይሖዋ ምሥክሮች—ሰላማዊ እና ታማኝ ክርስቲያኖች

 ጥቅምት 21, 1940 የኒው ዚላንድ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ማኅበረሰቡን የሚያውክ አደገኛ ድርጅት እንደሆነ አወጀ። ይህ የመንግሥት አዋጅ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ብዙ ችግር ቢያስከትልባቸውም አቋማቸውን አላላሉም። ለምሳሌ ፖሊሶች ሊመጡባቸውና ሊያስሯቸው እንደሚችሉ ቢያውቁም እንኳ ለአምልኮ መሰብሰባቸውን ቀጥለዋል።

 እህት ሜሪ፣ አንዲ ክላርክ የሚባል የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ባል ነበራት፤ አንዲ ሁኔታው አደገኛ ቢሆንም ባለቤቱ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንደቆረጠች አስተዋለ። በመሆኑም ሜሪ ስብሰባ ላይ በመገኘቷ ምክንያት ልትታሰር ትችላለች የሚል ስጋት አደረበት። አንዲ ከዚያ ቀደም በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልማድ ባይኖረውም ከሜሪ ጋር አብሮ ወደ ስብሰባ መሄድ ጀመረ፤ “አንቺን ካሰሩሽ እኔንም አብረው ይሰሩኝ” ብሏት ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ አንዲ ከባለቤቱ ጋር በቋሚነት ወደ ስብሰባ መሄዱን ቀጠለ። ከጊዜ በኋላ እሱም ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በኒው ዚላንድ የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ቢደርስባቸውም የሜሪ ዓይነት ቁርጠኝነት አሳይተዋል።

ቢታሰሩም ውጤታማ ነበሩ

 አንድ ቀን ጆን መሪ የተባሉ የ78 ዓመት ወንድም ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየት ላይ ሳሉ ፖሊሶች አስቆሟቸው። ፍርድ ቤቱ ወንድም ጆን ማኅበረሰቡን በሚያውክ ድርጅት እንቅስቃሴ እንደተካፈሉ በመግለጽ ፈረደባቸው። ሌሎች በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም ፍርድ ቤት ቀርበዋል፤ አንዳንዶቹ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ እስከ ሦስት ወር የሚደርስ እስራት ተበይኖባቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የታሰሩት በተደጋጋሚ ነው።

 የይሖዋ ምሥክሮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናቸው የተነሳ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም። (ኢሳይያስ 2:4) ሆኖም በጦርነቱ ወቅት ብዙዎች የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቦ ስለነበር ወንድሞቻችን ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። ሰማንያ ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የውትድርና ሥልጠና ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በጦርነቱ ወቅት በጉልበት ሥራ ካምፖች እንዲቆዩ ተደርገዋል። በካምፖቹ ውስጥ ግፍ ቢደርስባቸውም እንዲሁም ክረምቱ እጅግ ቀዝቃዛ ቢሆንም ወንድሞቻችን በደስታ ይሖዋን ማምለካቸውን ቀጥለዋል።

 በካምፖቹ ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወዲያውኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉበት ቋሚ ፕሮግራም አወጡ። በጉባኤ መልክ የተደራጁ ሲሆን አዘውትረው ስብሰባ የሚያደርጉበትና ለሌሎች እስረኞች የሚሰብኩበት ዝግጅት ነበራቸው። እንዲያውም በአንዳንዶቹ ካምፖች ውስጥ ጠባቂዎች በተገኙበት ትላልቅ ስብሰባዎችን እንዲያካሂዱ ተፈቅዶላቸው ነበር። አንዳንድ እስረኞች እዚያው ካምፑ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተምረው እዚያው ተጠምቀዋል።

በእስር ላይ የነበሩት ወንድሞች ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አዘጋጅተው ነበር

 ቀደም ሲል የተጠቀሱት የሜሪና የአንዲ የመጨረሻ ልጅ የሆነው ብሩስ የእስር ቆይታውን መንፈሳዊ ትምህርት እንደሚያገኝበት አጋጣሚ አድርጎ ተመልክቶታል። በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ያ አጋጣሚ ለእኔ ትምህርት ቤት እንደመግባት ነበር፤ ምክንያቱም ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር ጥልቅ ውይይት በማድረግ የእነሱን እውቀት በሙሉ መቅሰም የምችልበት አጋጣሚ ነበረኝ።”

 በ1944 መንግሥት በካምፖቹ ውስጥ ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዳንዶቹን መልቀቅ ፈልጎ ነበር። ሆኖም ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ በዚህ ሐሳብ አልተስማሙም፤ ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮቹ ከተለቀቁ ስለ እምነታቸው ለሌሎች መናገራቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኞች ነበሩ። በሪፖርታቸው ላይ እንዲህ ብለው ነበር፦ “በእስር መቆየታቸው አክራሪነታቸውን በተወሰነ መጠን ለመግታት ቢያስችልም ሰዎቹን በፍጹም ሊቀይራቸው አይችልም።”

በማኅበረሰቡ ላይ አደጋ አይፈጥሩም

 እገዳው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በስፋት እንዲወራ ስላደረገ አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። ከጊዜ በኋላም ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበረሰቡ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንደማይፈጥሩ ተገነዘቡ። የይሖዋ ምሥክሮች በማንም ላይ ጉዳት የማያደርሱ ሰላማዊ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ተረዱ። በዚህም የተነሳ በኒው ዚላንድ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በ1939 ከነበረበት ከ320 ተነስቶ በ1945 ወደ 536 ከፍ ብሏል!

 አንዳንድ ምክንያታዊ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ኢፍትሐዊ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ለምሳሌ አንድ ዳኛ፣ በመስበኩ ምክንያት ክስ በተመሠረተበት አንድ ወንድም ላይ የቀረበውን ማስረጃ ከሰሙ በኋላ ክሱን ውድቅ አደረጉት። እንዲህ ብለዋል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማሰራጨት እንደ ወንጀል መቆጠሩን አእምሮዬ ጨርሶ ሊቀበለው አይችልም፤ ይህ ካለኝ የሕግ እውቀት ጋር ይጋጫል።”

 ጦርነቱ አብቅቶ እገዳው ሲነሳ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ለማስተማር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠው ነበር። በ1945 ቅርንጫፍ ቢሮው በኒው ዚላንድ ለሚገኙት ለሁሉም ጉባኤዎች የላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዳችሁ ሁሉንም ሰው ስታነጋግሩ ዘዴኛ፣ ወዳጃዊና ደግ ሁኑ። ውዝግብ ወይም ጭቅጭቅ ውስጥ ከመግባት ተቆጠቡ። የምናነጋግራቸው ሰዎች እምነታቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱትና በቁም ነገር እንደሚመሩበት አትዘንጉ። . . . ብዙዎቹ ሰዎች የጌታ ‘በጎች’ ናቸው፤ ወደ ይሖዋና ወደ መንግሥቱ ልንመራቸው ይገባል።”

 በዛሬው ጊዜም ኒው ዚላንድ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለጎብኚዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መናገራቸውን ቀጥለዋል። እንዲያውም አንድ ቀን በቱራንጊ የሚኖሩ 4 የይሖዋ ምሥክሮች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ17 አገሮች የመጡ 67 ጎብኚዎችን አነጋግረው ነበር።

 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የኒው ዚላንድ ነዋሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰላማዊና ታማኝ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ተገንዝበዋል። በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። በምድራችን ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው በዚህ አገር ውስጥ በ2019 ይሖዋን በደስታ የሚያገለግሉ ከ14,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።

እገዳው በ1940 ከተጣለ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተካሄደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባ

ኖርዝ አይላንድ፣ ኒው ዚላንድ ውስጥ ባለው ካምፕ ውስጥ ያሉ አንድ ሰው ብቻ የሚይዙ ክፍሎች

የሃውቱ ካምፕ፣ ኖርዝ አይላንድ፣ ኒው ዚላንድ

በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ 1949