በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

ዓለም አቀፍ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ

ዓለም አቀፍ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ

 በብራዚል የሚኖረው አጎስቲኖ እንዲህ ብሏል፦ “ያደግኩት ገጠር ውስጥ ነው፤ ቤተሰቦቼ የሚተዳደሩት በግብርና ነበር። በጣም ድሆች ነበርን። ሥራ ሠርቼ ቤተሰቦቼን ለመደጎም ስል ትምህርቴን ማቋረጥ ነበረብኝ።” አጎስቲኖ ማንበብና መጻፍ የተማረው 33 ዓመት ሲሞላው ነው። “ማንበብና መጻፍ መማሬ ለራሴ ያለኝ አክብሮት እንዲጨምር አድርጓል” በማለት ተናግሯል።

 የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ ማንበብና መጻፍ ካስተማሯቸው ከሩብ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች መካከል አጎስቲኖ አንዱ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እንደዚህ ዓይነት ትምህርት የሚሰጡት ለምንድን ነው? ይህን ትምህርት የተከታተሉ ሰዎች ምን ጥቅም አግኝተዋል?

መሃይምነት የመማር አቅምን ይቀንሳል

 በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች በ115 አገሮች ይሰብኩ ነበር። ሚስዮናውያን የተለያዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች ለመስበክ ሲሉ ተተርጉመው የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ያጫውቱ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአካባቢው ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ያበረክቱ ነበር። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተው ነበር፤ ያም ቢሆን አንዳንዶቹ ማንበብና መጻፍ አለመቻላቸው መጽሐፍ ቅዱስን መማር አዳጋች እንዲሆንባቸው አድርጓል።

 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ማንበብ አለመቻላቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጎ ነበር። (ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:2, 3) ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን መወጣትም ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። ለምሳሌ ማንበብ የማይችሉ ወላጆች ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ከፍተኛ ትግል ይጠይቅባቸዋል። (ዘዳግም 6:6, 7) በተጨማሪም ማንበብ የማይችሉ አዲስ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ሌሎችን የማስተማር ችሎታቸው የተገደበ ይሆናል።

የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ማካሄድ

 የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይመሩ የነበሩት ናታን ኖር እና ሚልተን ሄንሸል በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ የስብከት ሥራውን ለማደራጀት ወደተለያዩ አገሮች ይጓዙ ነበር። እነዚህ ወንድሞች መሃይምነት በተስፋፋባቸው አገሮች ውስጥ ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በጉባኤዎች ውስጥ መሠረተ ትምህርት እንዲሰጥ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሐሳብ አቀረቡ።

በቺንጎላ፣ ዛምቢያ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ በሲንያንጃ ቋንቋ የተዘጋጀ ንባብ ማስተማሪያ ሲወጣ፣ 1954

 ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ትምህርቱ የሚካሄድበትን መንገድ በተመለከተ ለጉባኤዎች መመሪያ ሰጡ። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ መንግሥት ያዘጋጀው የመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብር ስለነበር እሱን ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ መጻሕፍትንና ሌሎች የትምህርት መሣሪያዎችን ከመንግሥት ተቀብሎ ወደ ጉባኤዎች ልኳል። በሌሎች አገሮች ግን ወንድሞች የራሳቸውን የመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብር መቅረጽ አስፈልጓቸዋል።

 ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው ትምህርቱን መከታተል ይችል ነበር። የትምህርቱ ዓላማ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ ማድረግ ነበር፤ ለዚህ ሲባል በአንድ ጉባኤ ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች መሠረተ ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነበር።

ሰዎችን በእጅጉ የረዳ መርሃ ግብር

 ሰዎች ከዚህ የመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብር የተጠቀሙት እንዴት ነው? በሜክሲኮ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማነበው ነገር ስለሚገባኝ ልቤ ይነካል። ማንበብ መቻሌ ከጎረቤቶቼ ጋር በነፃነት እንድነጋገር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለብዙ ሰዎች ማካፈል እንድችል ረድቶኛል።”

 የመሠረተ ትምህርት ዘመቻው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንዲረዱ ከማስቻል ባለፈ ሌሎች ጥቅሞችንም አስገኝቷል። በቡሩንዲ የሚኖር አይዛክ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ማንበብና መጻፍ መቻሌ የግንባታ ሙያ ለመማር አስችሎኛል። አሁን የምተዳደረው በግንባታ ሥራ ነው፤ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እቆጣጠራለሁ።”

በሊሎንግዌ፣ ማላዊ በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የቺቼዋ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ፣ 2014

 በፔሩ የምትኖረው ሄሱሳ ማንበብና መጻፍ የተማረችው በ49 ዓመቷ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የቤት እመቤት እንደመሆኔ መጠን ገበያ የቀረቡትን ሸቀጦች ዓይነትና ዋጋ ማንበብ ያስፈልገኛል። ቀደም ሲል እንዲህ ማድረግ ይከብደኝ ነበር። ለመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብሩ ምስጋና ይግባውና አሁን ለቤተሰቤ የሚያስፈልጉ ነገሮችን መሸመት ቀላል ሆኖልኛል።”

 ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አገሮች ባለሥልጣናት፣ የይሖዋ ምሥክሮች መሠረተ ትምህርትን ለማስፋፋት ጥረት በማድረጋቸው አመስግነዋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም የመሠረተ ትምህርት መርሃ ግብር አላቸው፤ የማስተማሪያ ዘዴዎቻቸው ደግሞ ከዓመት ዓመት እየተሻሻሉ መጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች በቀለም ትምህርት ብዙ ያልገፉ ሰዎችን ለመርዳት እንዲሁም ሰዎችን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ሲሉ 224 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ብሮሹሮችን በ720 ቋንቋዎች አሳትመዋል። a

a ለምሳሌ ያህል፣ ማንበብና መጻፍ መማር የተባለው ብሮሹር በ123 ቋንቋዎች፣ አምላክን ስማ የተባለው ብሮሹር ደግሞ በ610 ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል።