በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያስተምር የባሕል ድርጅት

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያስተምር የባሕል ድርጅት

 ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በኋላ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለዋል) እንግዳ ተቀባይ ለሆነው የሜክሲኮ ሕዝብ ለመስበክ የተደራጀ ጥረት ማድረግ የጀመሩት በ1917 ነው። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ ጎርፈዋል። ይሁንና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሜክሲኮ መንግሥት ከምንሰብክባቸውና ስብሰባዎቻችንን ከምናካሂድባቸው ቦታዎች ጋር በተያያዘ ችግር መፍጠር ጀመረ።

 በወቅቱ የሜክሲኮ ሕግ ማንኛውም የአምልኮ እንቅስቃሴ መከናወን ያለበት የመንግሥት ንብረት በሆኑ ሕንፃዎች ውስጥ እንደሆነ ይደነግግ ነበር። ይህ ሕግ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮብን ነበር፤ ምክንያቱም የክልል ስብሰባዎቻችን የሚደረጉት በትላልቅ አዳራሾች ውስጥ፣ ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሚደረጉት በይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር፤ በተጨማሪም የምንሰብከው በመንገድ ላይና ከቤት ወደ ቤት ነው።

 ይህን ሕግ ለመታዘዝ ስንል በ1943 ሕዝብን የሚያስተምር አትራፊ ያልሆነ ሲቪልና የባሕል ማኅበር ተብለን ተመዘገብን። ይህ ምዝገባ፣ መብትና እውቅና የሰጠን እንደ ሃይማኖት ሳይሆን እንደ ባሕል ድርጅት አድርጎ ነው። በዚህም የተነሳ እንቅስቃሴዎቻችን የመንግሥት ንብረት በሆኑ ሕንፃዎች ውስጥ የተገደቡ እንዳይሆኑ ፈቃድ አገኘን።

 ከእንቅስቃሴዎቻችን መካከል ባሕላዊና ትምህርታዊ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች ይገኙ ነበር። በመሆኑም መንግሥት ለሲቪልና ለባሕል ድርጅቶች ያወጣቸውን ሕጋዊ መሥፈርቶች ሙሉ በሙሉ አሟላን። (ሮም 13:1) እርግጥ ዋናው ፍላጎታችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ሰዎችን መርዳት ነበር። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አዲሱን ዝግጅት እየባረከው እንደሆነ ማስተዋል ቻልን። ይህ ዝግጅት ለአስደናቂ እድገት መሠረት እንደጣለ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በዓይናቸው አይተዋል።

በስብከቱ ሥራችን በምንጠቀምበት አቀራረብ ላይ ማስተካከያ አደረግን

 ሜክሲኮ ውስጥ ዋነኛው ሥራችን ምንጊዜም ቢሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው። ያም ቢሆን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ከስብከቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ እንደ ሁኔታው በአቀራረባችን ላይ ማስተካከያ አደረግን። (1 ቆሮንቶስ 9:20-23) ለምሳሌ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ለአቴንስ ሰዎች ሲሰብክ ከቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ አልጠቀሰም። (የሐዋርያት ሥራ 17:22-31) እኛም በተመሳሳይ በምንሰብክበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ አንይዝም እንዲሁም ከሰዎች ጋር ስንወያይ ጥቅሶችን አንጠቀምም ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ የሚካፈሉት መጽሐፍ ቅዱስ ሳይዙ ነበር፣ 1945

 ኢሳቤል እንዲህ ብላለች፦ “ራሳችንን ስናስተዋውቅ የባሕልና የትምህርት ማኅበር ወኪሎች እንደሆንን እንናገር ነበር። ብዙውን ጊዜ የምጠቀመው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን በቀጥታ የማይጠቅሱ ንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕሶችን ነበር።” ሆኖም የምናነጋግራቸው ሰዎች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፍላጎት ካሳዩስ? እንደዚያ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንነግራቸዋለን። ኦሮራ “መጽሐፍ ቅዱስ ይዘን ስለማንወጣ ብዙ ጥቅሶችን በቃላችን እንይዝ ነበር” ብላለች። በተጨማሪም የምናነጋግራቸው ሰዎች በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ስናስረዳቸው ጥሩ ምላሽ ይሰጡ ነበር።

ከቤት ወደ ቤት የምናከውነው ሥራ በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ

 ሥራችን ሕጋዊ እውቅና እንዳለው፣ ለሚጠይቀን ሁሉ ማብራሪያ ለመስጠት ተዘጋጅተን ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:7) መንግሥት የሰጠን የመታወቂያ ካርድ በጣም ጠቅሞናል። a ማሪያ “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፊርማ ያረፈበት የመታወቂያ ካርድ ከቦርሳችን አይለይም ነበር” ብላለች። ሳሙኤል ደግሞ “ባለሥልጣናቱ አስቁመው ምን እያደረግን እንደሆነ ሲጠይቁን ካርዳችንን እናሳያቸው ነበር” ብሏል።

 የመታወቂያ ካርዳችን የሚደርስብንን ተቃውሞ ለመቋቋም ረድቶናል። ለምሳሌ ያህል፣ በሃሊስኮ ግዛት ያገለግል የነበረው ሄሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በ1974 በአንድ ቄስ የሚመሩ ዓመፀኞች እኔንና አንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስትን ሥራችንን ለማስቆም በማሰብ ወደ ባለሥልጣናት ወሰዱን። የመታወቂያ ካርዳችንን ለባለሥልጣናቱ ስናሳያቸው ሁሉም ተረጋጉ። የሕግ ከለላ ካገኘን በኋላ በአካባቢው ያሉ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መርዳታችንን ቀጠልን። በዛሬው ጊዜ በዚያ ከተማ ብዙ ጉባኤዎች ይገኛሉ።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና መሠረተ ትምህርት

 ትምህርትን የሚያበረታታ ሲቪል ማኅበር እንደመሆናችን መጠን ሕዝቡን ማንበብና መጻፍ በነፃ እናስተምር ነበር። b ኤርየል እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ዝግጅት የተጀመረው በትክክለኛው ጊዜ ነው። በወቅቱ ብዙ ሰዎች የመማር ዕድል አላገኙም ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። በመሆኑም ማንበብና መጻፍ እናስተምራቸው ጀመር፤ ብዙም ሳይቆይ ብዙዎች ከእኛ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ።”

 ሩት እንዲህ ብላለች፦ “አንዴ ፊደል መቁጠር ከተማሩ በኋላ የሚያስቆማቸው ምንም ነገር አልነበረም። ማንበብና መጻፍ መቻላቸው ውስጣዊ እርካታና ደስታ ሰጥቷቸዋል። እኛም ያደረጉትን መንፈሳዊ እድገት በገዛ ዓይናችን መመልከት ችለናል።”

 የይሖዋ ምሥክሮች ሲቪልና የባሕል ማኅበር እንደሆኑ ተደርገው ይታወቁ የነበረው ከ1943 እስከ 1993 ባሉት ዓመታት ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ127,000 የሚበልጡ ሰዎች ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ፣ ከ37,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የማንበብና የመጻፍ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ረድተናል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ከመሠረተ ትምህርት ጋር በተያያዘ ላከናወንነው ሥራ አመስግነውናል። (ሮም 13:3) ለምሳሌ ‘ለአሥርተ ዓመታት በትጋት ሰዎችን ማንበብና መጻፍ በማስተማራችን እንዲሁም በሜክሲኮ ግዛት አልፎ ተርፎም በመላ አገሪቱ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ በመርዳታችን’ በ2010 ልዩ እውቅና ሰጥተውናል።

አንድ ላይ መሰብሰብ

 የባሕል ማኅበር ሆነን በመመዝገባችን የተነሳ ስብሰባ የምናደርግባቸው ቦታዎች የትምህርት ቤት ክፍሎች ይመስላሉ፤ የሚታወቁትም የባሕል ትምህርት አዳራሽ ተብለው ነበር። ስብሰባዎቻችንን የምናደርገውም ሆነ መሠረተ ትምህርት የምናስተምረው በዚያ ነው።

 ኤንጅል እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ የምንሰበሰበው በወንድሞች ቤቶች ውስጥ ነበር፤ አብዛኞቹ ቤተሰቦች በቁሳዊ ድሆች ነበሩ። በጣም አደንቃቸዋለሁ። በቤቱ አንደኛው ክፍል ውስጥ ስብሰባ እንድናደርግ ሲሉ ሌላኛው ክፍል ውስጥ ተጨናንቀው ይኖሩ ነበር።”

 እንዲህ ያለ መሥዋዕት መክፈላቸው ጠቅሞናል። ኤንጅል ስለ ጉባኤ ስብሰባዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዴ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ስለሚሆን ብዙዎቻችን ደጅ ለመቆም እንገደድ ነበር። መልስ መመለስ ስንፈልግ ደግሞ በመስኮት ብቅ እንላለን። ያም ቢሆን ስብሰባዎቹ በጣም አስደሳች ነበሩ።”

 ችግር ውስጥ እንዳንገባ ስንል በስብሰባዎች ላይ ጮክ ብለን አንጸልይም ወይም አንዘምርም ነበር። ኤድሙንዶ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን የሕዝብ ንግግር ብለን የምንጠራው የባሕል ንግግር ሲቀርብ ተናጋሪው አድማጮቹ ባሕላቸውን እንዲያደንቁና የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት ተግባራዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን ጎላ አድርጎ ይጠቅሳል።” ውሎ አድሮ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ስም እንኳ መጠቀም አቆምን። ታዲያ ተናጋሪዎች ጥቅስ የሚጠቅሱት እንዴት ነው? ማኑኤል እንዲህ ብሏል፦ “ራእይ ምዕራፍ 21 ቁጥር 3 እና 4 ከማለት ይልቅ ‘66ኛው መጽሐፍ፣ 21፣ 3 እና 4’ አንል ነበር።” ሞይሰስ የተባለ ወንድም ደግሞ “ጥቅስ ለማግኘት ስንል እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ስንተኛ ተራ ቁጥር ላይ እንደሚገኝ ማወቅ ነበረብን” ብሏል።

በሜክሲኮ ካሳለፍነው ታሪክ የምናገኘው ትምህርት

 በጥቅሉ ሲታይ ድርጅታችን በሜክሲኮ ሥራውን የሚያከናውንበት መንገድ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከነበረው የተለየ አልነበረም። በሥራችን ላይ ገደብ ቢኖርም የይሖዋ በረከት አልተለየንም። ሲቪል ማኅበር ሆነን በ1943 ስንመዘገብ በሜክሲኮ 1,565 አስፋፊዎች ነበሩ። እንደ ሃይማኖታዊ ድርጅት ተቆጥረን ሕጋዊ እውቅና ያገኘነው በ1993 ነው። በዚያ ዓመት የነበረው አማካይ የአስፋፊዎች ቁጥር 366,177 ነው። እነዚህ አስፋፊዎች ያከናወኑት ሥራ ተጨማሪ እድገት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። በ2021 ደግሞ በሜክሲኮ የነበረው አማካይ የአስፋፊዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሮ 864,633 ደረሰ። ከዚህ ታሪካዊ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

 እንቅፋት ሲያጋጥም ማስተካከያ ማድረግ፦ ሜክሲኮ ውስጥ በሥራችን ላይ ማስተካከያ በመደረጉ ለ50 ዓመታት ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ችለናል። ማሪዮ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ‘በሌሎች አገራት ውስጥ ያሉት ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች የሌሉን ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። ይሁንና ማንም ሰው ከድርጅቱ በምናገኘው መመሪያ ላይ ጥያቄ ሲያነሳ ሰምቼ አላውቅም። ምንጊዜም ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚመራ ጠንካራ እምነት ነበረን። በመሆኑም ለመታዘዝ ዝግጁ ነበርን።”

 በይሖዋ ሥራ ላይ ማተኮር፦ ጓዳሉፔ እንዲህ ብሏል፦ “ትኩረታችን ያረፈው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ከመሆኑ የተነሳ ስለ ሌላ ነገር የምናስብበት ጊዜም አልነበረንም። ይሖዋን ማገልገል በራሱ ደስታ ያስገኝልን ነበር። ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ይህ ነው።”

 ከእምነት አጋሮቻችን ጋር መቀራረብ። አኒታ እንዲህ ብላለች፦ “የመንግሥቱን መዝሙሮች እንደመዘመር ያሉ በባሕል ትምህርት አዳራሽ ውስጥ ማድረግ የማንችላቸውን ነገሮች ቤታችን እናደርጋለን። አንድነት ነበረን፤ እንዲሁም በየጊዜው እንገባበዛለን። በግብዣዎቻችን ላይ ምንጊዜም ትልቁን ቦታ የሚይዘው መንፈሳዊ ጭውውት ነበር።”

 ፍሎረንቲኖ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “ያንን ዘመን መለስ ብዬ ሳስብ ሁሉም ነገር የሆነው በዓላማ እንደሆነና ጥቅም እንዳስገኘልን ይሰማኛል። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት በተቃውሞ ውስጥም ጭምር የይሖዋ አመራር እንዳልተለየን እርግጠኛ ነኝ።”

a እንዲህ ያሉ ካርዶችን የተጠቀምነው ለመታወቂያነት ብቻ ነበር። ቅዱሳን መጻሕፍት ክርስቲያኖች ለጎረቤቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር ሲሉ በግለሰብ ደረጃ ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው አይገልጹም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ እንዲህ ያሉ ሰነዶችን ወይም ፈቃዶችን ለማግኘት ጥረት አያደርጉም።

b ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በ1940ዎቹ እና በ1950ዎቹ ዓመታት ግማሽ ገደማ የሚሆነው የሜክሲኮ ሕዝብ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር።

በ1952 ስፓንኛ “መጠበቂያ ግንብ” የያዙ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባ አዳራሻቸው ፊት ቆመው። ሕንፃው ላይ የተለጠፈው ምልክት በስፓንኛ “የባሕል ትምህርት አዳራሽ” ይላል።

በሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ፊት የቆሙ የይሖዋ ምሥክሮች። የተለጠፈው ምልክት በስፓንኛ “የመጠበቂያ ግንብ ሲቪል ማኅበር” ይላል፣ 1947

ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በኢዳልጎ፣ ሜክሲኮ ገጠራማ አካባቢ ስፓንኛ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሲያበረክቱ፣ 1959

የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ መንግሥት የሰጣቸውን የመታወቂያ ካርድ እንደ አስፈላጊነቱ ይጠቀሙበት ነበር

በ2010 የሜክሲኮ የትምህርት ሚኒስትር ዜጎችን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ጥረት በማድረጋቸው ለይሖዋ ምሥክሮች ሽልማት አበርክቶላቸዋል

የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ባሕል ድርጅት ተደርገው ስለተመዘገቡ ትላልቅ ስብሰባዎችን ማካሄድ ችለዋል፤ ለምሳሌ በ1969 ዓለም አቀፍ የባሕል ስብሰባ አድርገዋል