በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሄሱስ ማርቲን | የሕይወት ታሪክ

“ይሖዋ በጭንቄ ቀን ደርሶልኛል”

“ይሖዋ በጭንቄ ቀን ደርሶልኛል”

በ1936 ማድሪድ ውስጥ ተወለድኩ። በእኔ ዕድሜ ያሉ ስፔናውያን ይህን ዓመት ፈጽሞ አይረሱትም። ስፔን ውስጥ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ዓመት ነው።

 የእርስ በርስ ጦርነቱ ስፔንን ለሦስት ዓመታት ያህል ያናወጣት ሲሆን በብዙዎች ላይ የማይጠፋ አካላዊና ስሜታዊ ጠባሳ ትቶ አልፏል። አባቴም ቢሆን ከዚህ አላመለጠም። አባቴ ከድሮም ጀምሮ በአምላክ ያምን ነበር፤ ሆኖም የካቶሊክ ቀሳውስት በጦርነቱ ያደረጉትን ከፍተኛ ተሳትፎ ሲመለከት በሃይማኖት ምሬት አደረበት። ስለዚህ እኔንና ወንድሜን በካቶሊክ ሃይማኖት ውስጥ ክርስትና አላስነሳንም።

ፍራንሲስኮ ፍራንኮ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር እጅና ጓንት ነበር

 በ1950 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በራችንን አንኳኩ። አባቴም ካዳመጣቸው በኋላ በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። በወቅቱ የ14 ዓመት ልጅ ስሆን፣ ከምንም በላይ የምወደው እግር ኳስ ነበር። አባቴ የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡትን አንዳንድ ጽሑፎች እንዳነብ ጋበዘኝ፤ እኔ ግን ይህን ማድረግ አልፈለግሁም። አንድ ቀን እግር ኳስ ስጫወት ቆይቼ ወደ ቤት ስመለስ እናቴን “እማዬ፣ እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪዎች ዛሬም መጥተዋል?” ብዬ ጠየቅኋት። “አዎ፣ ሳሎን ውስጥ ከአባትህ ጋር እየተወያዩ ነው” አለችኝ። ይህን ስሰማ እየሮጥኩ ወደ ደጅ ወጣሁ።

 ጥሩነቱ ግን አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን መማር አለመፈለጌ ተስፋ አላስቆረጠውም። እንዲያውም ለተማራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለው ፍቅር እያደገ ስለሄደ በ1953 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። አባቴ ይህን ማድረጉ በጣም ስላስገረመኝ ብዙ ጥያቄዎች እጠይቀው ጀመር። የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት። እሱም ማክሲሞ ማርሻ የተባለ ወጣት የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናኝ አመቻቸ። ከሁለት ዓመት በኋላ በ19 ዓመቴ፣ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ የተጠመቅሁት ከማድሪድ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በጃራማ ወንዝ ውስጥ ነው።

በፍራንኮ አምባገነናዊ አገዛዝ ወቅት መስበክ

 በ1950ዎቹ ዓመታት መስበክና ለአምልኮ መሰብሰብ ቀላል አልነበረም። ስፔንን ያስተዳድር የነበረው አምባገነኑ ፍራንሲስኮ ፍራንኮ ነው፤ እሱ ደግሞ በአገሪቱ ከካቶሊክ ሃይማኖት ውጭ ሌላ እምነት እንዳይኖር ለማድረግ ቆርጦ ነበር። በመሆኑም ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክሮችን ያድኑ ጀመር። የምንሰበሰበው በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር፤ ጎረቤቶች ካዩን ለፖሊስ ሪፖርት ሊያደርጉን ስለሚችሉ ይህን የምናደርገው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። በጣም ተጠንቅቀን ከቤት ወደ ቤትም እናገለግል ነበር፤ አለፍ አለፍ እያልን ሁለት ወይ ሦስት ቤቶች ካንኳኳን በኋላ ቶሎ ብለን ወደ ሌላ አካባቢ እንሄዳለን። ብዙዎች ለመልእክታችን ቀና ምላሽ ሰጥተዋል፤ ሆኖም በሥራችን ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎችም ነበሩ።

ወንድም ፍራንዝ በድብቅ ባደረግነው ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር እያቀረበ

 በአንድ ወቅት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ከአንድ የካቶሊክ ቄስ ጋር ተገናኘን። ወደ ቤቱ የመጣንበትን ዓላማ ስንነግረው “ማን ፈቅዶላችሁ ነው ይህን የምታደርጉት? በፖሊስ ላስይዛችሁ እንደምችል አታውቁም?” አለን። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን እንደሚችል የምናውቅ መሆኑን ገለጽኩለት። ከዚያም እንዲህ አልኩት፦ “የኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶችም ሊያሳስሩት ሞክረው ነበር። ታዲያ ተከታዮቹስ ተመሳሳይ ዕጣ ቢደርስባቸው ምን ይገርማል?” ቄሱ የሰጠሁት ምላሽ ስላበሳጨው ወደ ውስጥ ገብቶ ለፖሊሶች መደወል ጀመረ። እኔም ጊዜ ሳላጠፋ ሕንፃውን ለቅቄ አመለጥኩ።

 በስፔን የነበርነው በመቶዎች የምንቆጠር አስፋፊዎች እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ለመልእክቱ ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች አግኝተናል። የካቲት 1956 ገና በ19 ዓመቴ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። a በአቅኚነት የምናገለግለው አብዛኞቻችን ወጣትና ተሞክሮ የሌለን ነበርን። ሆኖም በወቅቱ ለነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ሚስዮናውያን ምስጋና ይግባቸውና የሚያስፈልገንን ሥልጠናና ማበረታቻ አግኝተናል። እኔና አንድ ሌላ ወጣት አቅኚ በአሊካንቴ ከተማ እንድናገለግል ተመደብን፤ በዚህች ከተማ የስብከቱ ሥራ ገና ሀ ተብሎ መጀመሩ ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ ብዙ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና በመቶዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎች ማበርከት ችለናል።

 ሥራችን የሰዎችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። በአሊካንቴ ለጥቂት ወራት እንደሰበክን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋልን፤ መጽሐፍ ቅዱሶቻችንም ተወረሱብን። ለ33 ቀናት አስረው ካቆዩን በኋላ ማድሪድ ወስደው ለቀቁን። ይህ ሁኔታ ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ማሳያ ነበር።

የጭንቅ ጊዜ

 ሃያ አንድ ዓመት ሲሆነኝ በውትድርና እንዳገለግል ተመለመልኩ። በናዶር ወደሚገኘው የወታደር ጦር ሰፈር ሄጄ ሪፖርት ማድረግ ነበረብኝ፤ በሰሜናዊ ሞሮኮ የምትገኘው ይህች ከተማ በስፔን ሞግዚትነት ሥር ነበረች። በዚያም በዋናው ሌተናል ፊት ቀርቤ አቋሜን በግልጽ አስረዳሁ። ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠትም ሆነ የደንብ ልብሱን ለመልበስ ፈቃደኛ አለመሆኔን ነገርኳቸው። ወታደራዊው ፖሊስ በመሊላ ወደሚገኘው ሮስትሮጎርዶ ወህኒ ቤት ወሰደኝ፤ እዚያ ሆኜ፣ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የምቀርብበትን ጊዜ መጠባበቅ ጀመርኩ።

በመሊላ የሚገኘው ሮስትሮጎርዶ ወህኒ ቤት

 ፍርድ ቤት ከመቅረቤ በፊት ግን በሞሮኮ ያለው ወታደራዊ አዛዥ ‘ትንሽ ቢያቀምሱኝ’ ሐሳቤን እንደምቀይር ተሰማው። ስለዚህ ሙልጭ አድርገው ሰደቡኝ፤ ከዚያም ለ20 ደቂቃ ያህል በፈረስ ጅራፍ ገረፉኝ፤ በድብደባው ብዛት ራሴን ልስት ምንም አልቀረኝ። አዛዡ ግን ይህም ስላልበቃው በወታደር ጫማው ጭንቅላቴን ይረግጠኝ ጀመር፤ ድብደባውን ያቆመው ደሜ መፍሰስ ሲጀምር ነው። ከዚያም ወደ ቢሮው ተወሰድኩ፤ አዛዡ “የለቀቅሁህ እንዳይመስልህ! ገና በየቀኑ አሳርህን ነው የምናበላህ!” ሲል ጮኸብኝ። በኋላም ጠባቂዎቹን ምድር ቤት ውስጥ እንዲዘጉብኝ አዘዛቸው። ክፍሉ ቀዝቃዛና ጨለማ ነው፤ ምንም ተስፋ ያለኝ አይመስልም ነበር።

 ጭንቅላቴ በደም እንደተጨማለቀ የእስር ቤቱ ወለል ላይ ወድቄ የነበረበትን ያን ጊዜ መቼም ቢሆን አልረሳውም። ከአንዲት ስስ ብርድ ልብስ ሌላ የምለብሰው ነገር አልነበረኝም። አልፎ አልፎ አይጦች ውር ውር ይላሉ። ማድረግ የምችለው ብቸኛ ነገር ይሖዋ ጥንካሬና ጽናት እንዲሰጠኝ መጸለይ ነበር። በጨለማ በተዋጠው በዚያ ቀዝቃዛ እስር ቤት ውስጥ ሆኜ ደጋግሜ ጸለይኩ። b

 በቀጣዩ ቀንም ሌላው ኃላፊ እንደገና ደበደበኝ። ዋናው አዛዥ የልቡ እስኪደርስ መደብደቤን ለማረጋገጥ ቆሞ እያየ ነበር። እውነቱን ለመናገር በዚህ ጊዜ ‘ከዚህ በላይስ መቋቋም አልችልም’ ብዬ ማሰብ ጀምሬ ነበር። በዚያ ምሽት የእስር ቤቱ ክፍል ውስጥ ሆኜ ይሖዋ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት።

 በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው አዛዥ ቢሮ እንደገና ተጠራሁ። ‘አሁንስ አለቀለኝ!’ ብዬ አሰብኩ። ወደ አዛዡ ቢሮ የሄድኩት እየጸለይኩ ነው። የወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ጸሐፊ የሆነው ዶን ኢስቴቫን c ቢሮ ውስጥ እየጠበቀኝ ነበር። የመጣው ወታደራዊ ችሎት ፊት የምቀርብበትን ሂደት ለማስጀመር ነው።

 ዶን ኢስቴቫን ጭንቅላቴ ላይ የተጠመጠመውን ፋሻ ሲያይ “ምን ሆነህ ነው?” አለኝ። የባሰ ነገር እንዳይመጣ ስለሰጋሁ ለመናገር አመነታሁ፤ እንደምንም ብዬ ግን እውነቱን ነገርኩት። የደረሰብኝን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ወታደራዊ ችሎት ፊት እንዳትቀርብ ልረዳህ አልችልም። ከአሁን በኋላ ግን ማንም ሰው እንደማይነካህ ቃል እገባልሃለሁ።”

 እንዳለውም ከዚያ በኋላ በእስር ባሳለፍኩት ጊዜ አንድም ሰው ንክች አላደረገኝም። ዳኛው ኢስቴቫን እኔን ለማነጋገር ለምን በዚያች ቀን እንደመጣ የማውቀው ነገር የለም። ሆኖም ጸሎቴ አስደናቂ በሆነ መንገድ መልስ እንዳገኘ እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ በጭንቄ ቀን ደርሶልኛል፤ ልሸከመው ከምችለው በላይ እንድፈተን እንዳልፈቀደም በግልጽ ተመልክቻለሁ። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ስለዚህ ወታደራዊ ችሎት ፊት የቀረብኩት በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ተማምኜ ነው።

በኦካንያ ማረሚያ ቤት

 ፍርድ ቤቱ የ19 ዓመት እስራት በየነብኝ፤ በኋላ ላይ ደግሞ “ዓመፀኛ ነው” በሚል ሦስት ዓመት ተጨመረብኝ። ሞሮኮ ውስጥ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ከታሰርኩ በኋላ ከማድሪድ ብዙም ወደማይርቀው ወደ ኦካንያ ማረሚያ ቤት ተዛወርኩ፤ የቀረውን የእስር ጊዜዬን በዚያ እንድጨርስ ታስቦ ነበር። ወደ ኦካንያ መዛወሬን ከይሖዋ እንደመጣ በረከት ነው የቆጠርኩት። ከሮስትሮጎርዶ ጋር ሲነጻጸር ይሄ ገነት የመግባት ያህል ነው። የታሰርኩበት ክፍል አልጋ፣ ፍራሽና አንሶላ አለው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የማረሚያ ቤቱ የሒሳብ ሹም አደረጉኝ። ያም ቢሆን ግን ለረጅም ጊዜ በመታሰሬ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር መገናኘት አለመቻሌ ትልቅ ፈተና ሆነብኝ።

 ወላጆቼ በየጊዜው እየመጡ ቢጠይቁኝም የሌሎች ማበረታቻ በጣም ያስፈልገኝ ነበር። ወላጆቼ፣ ሌሎች ወንድሞችም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ መግለጻቸውን ነገሩኝ። ይህን ስሰማ ‘ይሖዋ፣ እባክህ ቢያንስ አንድ ወንድም እኔ ያለሁበት እስር ቤት እንዲመጣ አድርግ’ ብዬ ጸለይኩ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ያቀረብኩትን ምልጃ ከጠበቅሁት በላቀ መንገድ መልሶልኛል። ብዙም ሳይቆይ አልቤርቶ ኮንቲዮክ፣ ፍራንሲስኮ ዲኣስ እና አንቶኒዮ ሳንቼዝ የተባሉ ሦስት ታማኝ ወንድሞች በኦካንያ ማረሚያ ቤት ታሰሩ። ለአራት ዓመት ብቻዬን ከታሰርኩ በኋላ ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር መገናኘት ቻልኩ። አራታችን አንድ ላይ እናጠና እንዲሁም ለሌሎች እስረኞች እንሰብክ ነበር።

ነፃ መውጣትና ወደ ሥራ መመለስ

 በመጨረሻም በ1964 በአመክሮ ተለቀቅሁ። የተላለፈብኝ የ22 ዓመት እስራት ተቀንሶ ከ6 ዓመት ተኩል በኋላ ተፈታሁ። ከእስር ቤት በተለቀቅሁበት በዚያው ቀን ወደ ጉባኤ ስብሰባ ሄድኩ። ያጠራቀምኳትን ጥቂት ገንዘብ ወደ ማድሪድ በታክሲ ለመሄድ አዋልኳት፤ ደስ የሚለው ልክ የጉባኤ ስብሰባ ሊጀመር ሲል ደረስኩ። ከወንድሞች ጋር እንደገና መሰብሰብ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው! ሆኖም ስብሰባዎች ላይ መገኘት በመቻሌ ብቻ ረክቼ አልተቀመጥኩም። ጊዜ ሳላጠፋ ወደ አቅኚነት መመለስ ፈልጌ ነበር። ፖሊሶች ቢያስቸግሩንም ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ይሰጡ ነበር፤ ይህም ከፊታችን ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን አሳይቶናል።

 በዚሁ ጊዜ አካባቢ መርሰዲስ ከተባለች ወጣት ልዩ አቅኚ ጋር ተዋወቅሁ፤ መርሰዲስ ለሁሉም ሰው ለመስበክ ጥረት የምታደርግ ትሑትና ቀናተኛ እህት ናት። በጣም ደግና ለጋስ መሆኗም እንድወዳት አደረገኝ። ከመርሰዲስ ጋር ስለተዋደድን ከአንድ ዓመት በኋላ ተጋባን። እንደ መርሰዲስ ዓይነት አጋር ማግኘቴ ትልቅ በረከት እንደሆነ ይሰማኛል።

ከመርሰዲስ ጋር ከተጋባን ብዙም ሳንቆይ

 ከተጋባን ከጥቂት ወራት በኋላ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። በወረዳ ሥራ ላይ በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን እንጎበኛለን፤ በጉብኝቱ ወቅት ከወንድሞቻችን ጋር አብረን እንሰበሰባለን እንዲሁም በስብከቱ ሥራ እንካፈላለን። በመላው ስፔን አዳዲስ ጉባኤዎች እየተቋቋሙ በመሆኑ ወንድሞች ማበረታቻና እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። ለአጭር ጊዜ ያህል ደግሞ ሥራችንን በድብቅ በምናከናውንበት በባርሴሎና ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ እየተመላለስኩ የማገልገል መብት አግኝቼ ነበር።

 በ1967 መንግሥት ለሁሉም የስፔን ዜጎች ሃይማኖታዊ ነፃነት የሚሰጥ ሕግ አሳለፈ፤ በመሆኑም አምልኳችንን በነፃነት ማከናወን ጀመርን። በመጨረሻም በ1970 የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ። ስለዚህ ለአምልኮ በነፃነት መሰብሰብ፣ የራሳችን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት ሌላው ቀርቶ የራሳችን ቅርንጫፍ ቢሮ በይፋ መክፈት ቻልን።

አዳዲስ ቲኦክራሲያዊ ምድቦች

 በ1971 እኔና መርሰዲስ በባርሴሎና የሚገኘው አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ቋሚ አባላት ሆነን እንድናገለግል ተጋበዝን። ሆኖም ከአንድ ዓመት በኋላ መርሰዲስ አረገዘች፤ አቢጋኤል የተባለች ቆንጆ ልጅ ተወለደችልን። በመሆኑም የቤቴል አገልግሎታችንን ማቆምና በሌላ ምድብ መሰማራት ይኸውም ልጃችንን ማሳደግ ነበረብን።

 አቢጋኤል ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ስትገባ ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ ወረዳ ሥራ መመለስ እንችል እንደሆነ ጠየቀን። እኛም ስለ ጉዳዩ ጸለይን እንዲሁም ጎልማሳ የሆኑ ወንድሞችን አማከርን። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ሄሱስ፣ መስኩ ላይ ከፈለጉህ እሺ ብለህ መሄድ አለብህ” አለኝ። በዚህ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ሌላ አስደሳች ምዕራፍ ተከፈተልን። መጀመሪያ አካባቢ፣ አቢጋኤልን መንከባከብ ስላለብን የምንጎበኘው በአቅራቢያችን ያሉ ጉባኤዎችን ነበር። ውሎ አድሮ ግን አቢጋኤል አድጋ የራሷን ሕይወት መምራት ጀመረች። እኛም በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል አጋጣሚ አገኘን።

 እኔና መርሰዲስ በወረዳ ሥራ ለ23 ዓመታት አገልግለናል። ይህን የአገልግሎት መብት በጣም እወደዋለሁ፤ ምክንያቱም ተሞክሮዬን ለወጣቶች ለማካፈል አጋጣሚ ይሰጠኛል። የጉባኤ ሽማግሌዎችንና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ባስተማርኩባቸው አንዳንድ ወቅቶች የምናርፈው ማድሪድ በሚገኘው ቤቴል ነበር። የሚገርመው ከቤቴል ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የጃራማ ወንዝ ይገኛል፤ በ1955 የተጠመቅሁት በዚህ ወንዝ ውስጥ ነበር። ወጣት ወንዶችና ሴቶች በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ለማሠልጠን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደዚህ አካባቢ እንደገና እመለሳለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም።

አንድ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት ላይ ሳስተምር

 ከ2013 ወዲህ እንደገና በልዩ አቅኚነት ተሰማርተናል። እውነቱን ለመናገር ከወረዳ ሥራ ወደ አቅኚነት መመለስ ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ይህ የጥበብ እርምጃ መሆኑ ከጊዜ በኋላ ታይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤና እክሎች አጋጥመውኛል፤ ከበድ ያለ የልብ ቀዶ ሕክምናም አድርጌያለሁ። በእነዚህ ጊዜያት እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት አስፈልጎኛል፤ እሱም ቢሆን እንደምንጊዜውም ፈጽሞ አልተወኝም። ታማኟ ባለቤቴ መርሰዲስም ለ56 ዓመታት ከጎኔ ሳትለይ ደግፋኛለች፤ የተሰጡኝን ቲኦክራሲያዊ ምድቦች በሙሉ መወጣት የቻልኩት በእሷ እገዛ ነው።

 አስተማሪ ስለነበርኩበት ወቅት ብዙ ጊዜ አስባለሁ፤ እነዚያ ወጣት ተማሪዎች ፊት ላይ የሚነበበው ስሜት ከአእምሮዬ አይጠፋም። ወጣቶቹ ለመማር ያላቸው ጉጉት፣ እኔ ራሴ ወጣት እያለሁ ይሖዋን ማገልገል ስጀምር የነበረኝን ግለት ያስታውሰኛል። በሕይወቴ ውስጥ በጭንቅ ውስጥ ያለፍኩባቸው ጊዜያት አሉ፤ ያም ቢሆን ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎችም አግኝቻለሁ። ያጋጠሙኝ የተለያዩ ፈተናዎችም እንኳ በጣም ጠቃሚ ትምህርት አስተምረውኛል፤ ከሁሉ በላይ ያገኘሁት ትምህርት፣ ምንጊዜም ቢሆን በራሴ ብርታት መታመን እንደሌለብኝ ነው። የደረሱብኝ መከራዎች የይሖዋን ኃያል እጅ የማየት አጋጣሚ ሰጥተውኛል፤ በጭንቄ ቀንም እንኳ የይሖዋ እጅ ፈጽሞ አልተለየኝም።—ፊልጵስዩስ 4:13

እኔና መርሰዲስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈላችንን ቀጥለናል

a ልዩ አቅኚ የሚባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ ወደሚልበት ቦታ በፈቃደኝነት ሄዶ የሚሰብክ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው።

b አራት ሜትር በአራት ሜትር በሆነው በዚህ እስር ቤት ውስጥ ሰባት ወራት አሳልፌያለሁ። ክፍሉ መጸዳጃ አልነበረውም፤ የምተኛውም መሬት ላይ አንዲት ስስ ብርድ ልብስ ለብሼ ነበር።

c “ዶን” ስፓኒሽ በሚነገርባቸው አገራት ውስጥ ከአንድ ሰው ስም በፊት የሚገባ የአክብሮት መጠሪያ ነው።