በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚልቲያዲስ ስታቭሩ | የሕይወት ታሪክ

“ይሖዋ ተንከባክቦናል እንዲሁም መርቶናል”

“ይሖዋ ተንከባክቦናል እንዲሁም መርቶናል”

የ13 ዓመት ልጅ ገደማ እያለሁ እንደ አብዛኞቹ እኩዮቼ ሁሉ በቤታችን አቅራቢያ የሚያልፉ መኪኖችን ማየት ያስደስተኝ ነበር፤ የምንኖረው በትሪፖሊ፣ ሊባኖስ ነበር። አንድ በጣም የወደድኳት ቆንጆ ቀይ የአሜሪካ መኪና ነበረች፤ የመኪናዋ ባለቤት ሶርያዊ ነው። እኛ የምንሄድበት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ይቺን መኪና በድንጋይ እንድንመታት ሲነግረን ምን ያህል እንደደነገጥኩ ማሰብ ትችላላችሁ፤ ቄሱ ይህን ያለን የመኪናዋ ባለቤት የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ነው።

 ቄሱን ‘እንዴ ሹፌሩን ብንመታውስ?’ ብለን ጠየቅነው። ቄሱም መልሶ “በሉት! ከገደላችሁት ደሙን ከእጃችሁ ላይ በእኔ ልብስ ታጸዳላችሁ!” አለን። የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆኔ በጣም ብኮራም ቄሱ በቁጣ ተሞልቶ የተናገራቸው እነዚያ ቃላት ከጊዜ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗን ትቼ እንድወጣ አድርገውኛል። መለስ ብዬ ሳስበው ይህ ሁኔታ ስለ ይሖዋ እውነቱን እንድማር አጋጣሚ ከፍቶልኛል።

ስለ ይሖዋ እውነቱን ማወቅ

 ያደግሁት በትሪፖሊ ነው፤ በዚህች የወደብ ከተማ የተለያየ ባሕል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ይኖሩ ነበር። እንደማንኛውም ቤተሰብ ሁሉ የእኛ ቤተሰብም በባሕሉና በሃይማኖቱ ይኮራ ነበር። እኔና ታላላቅ ወንድሞቼ ‘የእምነት ወታደሮች’ a የተባለውን ቡድን ተቀላቀልን፤ ይህ ቡድን የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወም ነበር። አንድም የይሖዋ ምሥክር አግኝተን ባናውቅም ቄሳችን የይሖዋ ምሥክሮች የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ወንበዴዎች እንደሆኑና የቡድኑ መሪ ይሖዋ እንደሚባል ነግሮን ነበር። ቄሱ የይሖዋ ምሥክሮችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንድናጠቃቸው በተደጋጋሚ ይነግረን ነበር።

 እኔ አላወቅሁም እንጂ ሦስቱ ወንድሞቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው ነበር። ሆኖም ወንድሞቼ በእነሱ ላይ ጥቃት ከመሰንዘር ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን አብረዋቸው ለማጥናት ተስማሙ፤ ዓላማቸው የይሖዋ ምሥክሮች ስህተት እንደሆኑ ማሳየት ነበር። አንድ ቀን ምሽት ወደ ቤት ስመለስ ሳሎናችን ውስጥ በርከት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤተሰቦቼና ከጎረቤቶቻችን ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲወያዩ አገኘኋቸው። በጣም ተናደድኩ! ‘ወንድሞቼ እንዴት የኦርቶዶክስን እምነት ይክዳሉ?’ ብዬ አሰብኩ። ጥያቸው ልወጣ ስል የታወቀ የጥርስ ሐኪም የሆነ የይሖዋ ምሥክር ጎረቤታችን ቁጭ ብዬ ውይይቱን እንዳዳምጥ ጋበዘኝ። አንድ የቤተሰባችን ወዳጅ መዝሙር 83:18⁠ን ከራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጮክ ብሎ እያነበበ ነበር። ቄሳችን ሲዋሸን እንደነበረ የገባኝ የዚያን ጊዜ ነው። ይሖዋ የወንበዴዎች ቡድን መሪ ሳይሆን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ነው!

ከተጠመቅሁ ብዙም ሳይቆይ

 ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ ስለፈለግሁ ቤታችን በሚካሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመርኩ፤ ጥናቱን የሚመራው ወንድም ሚሼል አቡድ ነበር። አንድ ቀን ጓደኛዬ ከልጅነቴ ጀምሮ ግራ ሲያጋባኝ የነበረውን ጥያቄ አነሳ። “አምላክን የፈጠረው ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ወንድም አቡድ መልስ ለመስጠት ሶፋው ላይ ተኝታ የነበረችውን ድመት እንደ ምሳሌ ተጠቀመ። ድመቶች ሰዎች የሚያወሩትን ነገርና የሚያስቡበትን መንገድ መረዳት እንደማይችሉ ሁሉ እኛም ከአምላክ ጋር በተያያዘ የማንረዳቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ አብራራልን። ይህ ቀላል ምሳሌ ስለ ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መረዳት የማልችለው ለምን እንደሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለይሖዋ አምላክ ወሰንኩና በ1946 በ15 ዓመቴ ተጠመቅሁ።

አቅኚነት ሕይወቴ ዓላማ እንዲኖረው ረድቶኛል

 በ1948 በፎቶግራፍ ሙያ ተሰማርቶ ከነበረው ከወንድሜ ከሐና ጋር መሥራት ጀመርኩ። ከወንድሜ ሱቅ አጠገብ ሥዕሎች የሚሸጡበት ሱቅ ነበረ፤ የሱቁ ባለቤት ናጂብ ሳሌም b የተባለ ወንድም ነው። ናጂብ ደፋር ወንጌላዊ ነበር፤ በ100 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በድፍረት ሰብኳል። በመንደሮቹ ውስጥ አብሬው ስሰብክ የሰዎች ተቃውሞ ሳይበግረው በድፍረት እንደሚሰብክ አስተውያለሁ። በዚያ ላይ ደግሞ ከማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት በቀላሉ ለመጀመር አይቸገርም። የእሱ ቅንዓት በእኔ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ናጂብ ሳሌም (ከበስተ ጀርባ በቀኝ በኩል) በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል

 አንድ ቀን ሥራ ላይ እያለን ሜሪ ሻያ የተባለች ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣች ሊባኖሳዊት እህት ወደ ሱቃችን መጣች። ሜሪ ሥራ የሚበዛባት እናት ብትሆንም ቀናተኛ አቅኚም ነበረች። ከእሷ ጋር ያደረግነው ጭውውት የሕይወቴን አቅጣጫ ቀይሮታል። ሜሪ ስትሰብክ ያገኘቻቸውን ተሞክሮዎች እየነገረችን ከሁለት ሰዓት በላይ አብራን ቆየች። ሜሪ ከመሄዷ በፊት ትኩር ብላ አየችኝና “ሚሊቶ የምታስተዳድረው ቤተሰብ የለህም፤ ታዲያ ለምን አቅኚ አትሆንም?” አለችኝ። እኔም ራሴን ለማስተዳደር መሥራት ስላለብኝ አቅኚ መሆን እንደማልችል ነገርኳት። እሷ ግን “አሁን ስንጫወት ምን ያህል ነው የቆየነው?” ብላ ጠየቀችኝ። “ሁለት ሰዓት ገደማ” አልኳት። ሜሪም እንዲህ አለችኝ፦ “እንግዲህ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያን ያህል ስትሠራ አላየሁህም። በየቀኑ የዚህን ያህል ሰዓት ብትሰብክ እኮ አቅኚ መሆን ትችላለህ። ለምን ለአንድ ዓመት ያህል አትሞክረውም? ከዚያ በኋላ የፈለግከውን ትወስናለህ።”

 በባሕላችን ወንዶች የሴቶችን ምክር መስማታቸው የተለመደ ነገር ባይሆንም ሜሪ የተናገረችው ነገር ምክንያታዊ እንደሆነ ተሰማኝ። ከሁለት ወራት በኋላ ማለትም ጥር 1952 በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ ደግሞ በ22ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድካፈል ግብዣ ቀረበልኝ።

በ1953 ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ሲሰናበቱኝ

 ከጊልያድ ከተመረቅሁ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ደግሞ ዶሪስ ውድ ከተባለች ደስተኛ እንግሊዛዊት እህት ጋር ትዳር መሠረትኩ፤ እሷም እንደ እኔ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚስዮናዊነት ታገለግል ነበር።

ሶርያ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መስበክ

 እኔና ዶሪስ ከተጋባን ብዙም ሳንቆይ አሌፖ፣ ሶርያ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ የስብከቱ ሥራችን ታግዶ ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸውን አብዛኞቹን ሰዎች የምናገኘው በሌሎች ሰዎች በኩል ነበር።

 አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ፍላጎት ወዳሳየች አንዲት ሴት ቤት ሄድን። ሴትየዋ በሩን የከፈተችው በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች ነው። “በጣም መጠንቀቅ አለባችሁ! ፖሊሶች አሁን መጥተው ነበር። የት እንደምትኖሩ ለማወቅ እየተከታተሏችሁ ነው” አለችን። የሚስጥር ፖሊሶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የት እንደምንመራ አውቀው ነበር። ስለዚህ በመካከለኛው ምሥራቅ ሥራውን በበላይነት የሚመሩትን ወንድሞች አነጋገርናቸው። እነሱም በተቻለ ፍጥነት አገሪቱን ለቅቀን እንድንወጣ መከሩን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ትተን በመሄዳችን ብናዝንም የይሖዋን ፍቅራዊ ጥበቃ እንዳገኘን ተሰምቶናል።

ኢራቅ ውስጥ ስናገለግል ይሖዋ መርቶናል

 በ1955 ባግዳድ፣ ኢራቅ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ኢራቅ ውስጥ ለሁሉም ሰው በዘዴ መስበክ ብንችልም ትኩረት ያደረግነው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ነበር።

ኢራቅ ውስጥ ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር

 በገበያ ቦታ ወይም መንገድ ላይ ከምናገኛቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋርም ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ጭውውት ለመጀመር እንሞክር ነበር። ዶሪስ ብዙ ጊዜ የሰዎችን ቀልብ የሚስብ ነገር አንስታ ውይይት ትጀምር ነበር። ለምሳሌ፣ “አባቴ ሁላችንም በፈጣሪያችን ፊት እንቆማለን ይል ነበር” ትላቸዋለች። (ሮም 14:12) ከዚያም “ይህ ሐሳብ በሕይወቴ ውስጥ በጣም ጠቅሞኛል። እርስዎስ ምን ይመስልዎታል?” ትላለች።

 ባግዳድ ውስጥ ለሦስት ዓመት ገደማ አገለገልን፤ በዚያ በነበርንበት ጊዜ ወንድሞች የስብከቱን ሥራ በዘዴ እንዲያደራጁ ረድተናቸዋል። በምንኖርበት የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ በአረብኛ ስብሰባዎች እናደርግ ነበር። ቅን ልብ ያላቸው አሦራውያን ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታቸው በጣም ያስደስተን ነበር። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የክርስትናን እምነት እንደሚከተሉ የሚናገሩ ናቸው። በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው በመካከላችን ያለውን ፍቅርና አንድነት በገዛ ዓይናቸው ሲመለከቱ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች መሆናችንን ተገነዘቡ።—ዮሐንስ 13:35

በባግዳድ በሚስዮናውያን ቤታችን ውስጥ ስብሰባ እናደርግ ነበር

 የምንሰብከውን የሰላም መልእክት ከተቀበሉን ሰዎች መካከል ኒኮላ አዚዝ የተባለ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ይገኝበታል፤ የአርሜንያና የአሦር ዝርያ ያለው ኒኮላ ረጋ ያለና ትሑት ሰው ነው። ኒኮላ እና ባለቤቱ ሔለን፣ ይሖዋ እና ልጁ ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመቀበል ጊዜ አልወሰደባቸውም። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ኒኮላ እና ሌሎች 20 ሰዎች በኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ የተጠመቁበትን ቀን አልረሳውም።

ኢራን ውስጥ የይሖዋን እጅ አይተናል

በ1958 ኢራን ውስጥ

 ሐምሌ 14, 1958 በተደረገው መፈንቅለ መንግሥት የኢራቁ ንጉሥ ዳግማዊ ፋይሰል ተገደለ፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኛም ከአገሪቱ ስለተባረርን ወደ ኢራን ሄድን። በዚያም ለውጭ አገር ሰዎች እየሰበክን ለስድስት ወራት ያህል አገልግሎታችንን በዘዴ ስናከናውን ቆየን።

 የኢራን ዋና ከተማ የሆነችውን ቴህራንን ለቅቀን ከመውጣታችን በፊት ፖሊሶች ለምርመራ ወደ ጣቢያ ወሰዱኝ። ይህ አጋጣሚ ፖሊሶች ሁልጊዜ እየተከታተሉን እንዳሉ እንድገነዘብ አደረገኝ። ከምርመራው በኋላ ለዶሪስ ፖሊሶች እየተከታተሉን እንደሆነ ነገርኳት። ለደህንነታችን ሲባል እኔ ወደ ቤት ባልመለስ የተሻለ እንደሆነ ተስማማን። እንዲሁም አገሪቱን ለቅቀን እስክንወጣ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ አብረን ላለመሆን ወሰንን።

 ዶሪስ አውሮፕላን ማረፊያ እስክንገናኝ ድረስ ልትቆይበት የምትችል ጥሩ ቦታ አገኘች። ሆኖም ፖሊሶች ሳያዩዋት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዴት ልትሄድ ነው? ዶሪስ ስለ ሁኔታው ወደ ይሖዋ ጸለየች።

 በድንገት ኃይለኛ ዝናብ ስለጣለ ፖሊሶቹን ጨምሮ ሁሉም ሰው መጠለያ ፍለጋ መሯሯጥ ጀመረ። መንገዶቹ ሁሉ ጭር ስላሉ ዶሪስ በነፃነት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ሄደች። ዶሪስ “ይህ ዝናብ ተአምር ነው!” ብላለች።

 ከኢራን ከወጣን በኋላ በሌላ ክልል ተመደብን። በዚያም የተለያየ ዘርና ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ሰብከናል። በ1961 በወረዳ ሥራ ተሰማርተን በመካከለኛው ምሥራቅ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የእምነት አጋሮቻችንን እየጎበኘን ነበር።

የይሖዋ መንፈስ የሚያከናውነውን ሥራ ማየት

 በመካከለኛው ምሥራቅ አገልግሎታችንን ስናከናውን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አንድነት የመፍጠር ኃይል እንዳለው ያየሁባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። ኤዲ እና ኒኮላ የተባሉ ሁለት ፍልስጤማውያንን መጽሐፍ ቅዱስ ሳስጠና ያደረግነው አስደሳች ውይይት አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። ሁለቱም በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ያስደስታቸው ነበር፤ ሆኖም በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተነሳ ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን አቋረጡ። ይሖዋ ልባቸውን እንዲከፍትላቸው ጸለይኩ። ኤዲ እና ኒኮላ አምላክ የፍልስጤማውያንን ብቻ ሳይሆን የመላውን የሰው ዘር ችግር እንደሚያስወግድ ሲማሩ ጥናታቸውን ቀጠሉ። (ኢሳይያስ 2:4) ብሔራዊ ስሜታቸውን አስወግደው ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ ኒኮላ ቀናተኛ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኗል።

 እኔና ዶሪስ ወደ ተለያዩ አገሮች ስንጓዝ፣ ወንድሞቻችን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸው የሚያሳዩት ታማኝነት ያስደንቀን ነበር። ወንድሞቻችን ብዙ ፈተና ስለሚያጋጥማቸው የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ስጎበኛቸው እነሱን ለማበረታታት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርግ ነበር። (ሮም 1:11, 12) ምንጊዜም ቢሆን ከወንድሞቼ የተሻልኩ እንደሆንኩ አድርጌ ላለማሰብ ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ። (1 ቆሮንቶስ 9:22) እገዛ የሚያስፈልጋቸውን የእምነት አጋሮቼን ማበረታታት ይህ ነው የማይባል እርካታ አምጥቶልኛል።

 መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናናቸው በርካታ ሰዎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው። አንዳንዶቹ በአገራቸው ውስጥ ከሚካሄደው ውጊያ ለመሸሽ ሲሉ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ሌሎች አገራት ሄደዋል። ሆኖም እነዚህ ወንድሞች በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ አረብኛ ተናጋሪዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ብዙ ሥራ ማከናወን ችለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከልጆቻቸው አንዳንዶቹ ተጨማሪ ደፋር ሰባኪዎች በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተመልሰዋል። እኔና ዶሪስ በበርካታ መንፈሳዊ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን መከበባችን ምን ያህል እንደሚያስደስተን መገመት ትችላላችሁ!

ለዘላለም በይሖዋ መመካት

 በሕይወታችን ሁሉ ይሖዋ ተንከባክቦናል እንዲሁም መርቶናል፤ የእሱን እጅ በተለያዩ መንገዶች አይተናል። ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝን ጭፍን ጥላቻና ብሔራዊ ኩራት እንዳስወግድ ይሖዋ ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። ደፋር ከሆኑና ከማያዳሉ የእምነት ባልንጀሮቼ ያገኘሁት ሥልጠና፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተለያየ ባሕልና ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ረድቶኛል። እኔና ዶሪስ ወደ ተለያዩ አገሮች ስንጓዝ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል፤ አንዳንዴም ምን ሊያጋጥመን እንደሚችል አለማወቃችን ያስጨንቀን ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ በራሳችን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አምላክ መታመን እንዳለብን አስተምሮናል።—መዝሙር 16:8

 ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸውን በርካታ አሥርተ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ የሰማዩ አባቴ በጣም ብዙ ውለታ እንደዋለልኝ ይሰማኛል። ውዷ ባለቤቴ ዶሪስ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንዳናገለግል ምንም ነገር፣ የሞት ዛቻም እንኳ ቢሆን እንቅፋት ሊሆንብን እንደማይገባ ብዙ ጊዜ ትናገራለች፤ እኔም በእሷ ሐሳብ እስማማለሁ። ይሖዋ በመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ምሥራች እንድናሰራጭ ስለፈቀደልን ሁልጊዜ እናመሰግነዋለን። (መዝሙር 46:8, 9) ይሖዋ በእሱ የሚመኩትን ሁሉ ምንጊዜም እንደሚመራቸውና እንደሚጠብቃቸው ስለምናውቅ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንጠባበቃለን።—ኢሳይያስ 26:3

a ስለዚህ ቡድን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የ1980 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 186-188 ተመልከት።

b የናጂብ ሳሌም የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 2001 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22-26 ላይ ወጥቷል።