በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማይልዝ ኖርዝኦቨር | የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ የእጄን ሥራ ባርኮልኛል

ይሖዋ የእጄን ሥራ ባርኮልኛል

 ወላጆቼ ሁሌም የይሖዋን ድርጅት ለመደገፍ የሚጥሩ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ በለንደን ቤቴል የነበሩ ወንድሞች የቤቴል ቤተሰብ የራሱ የወተት አቅርቦት እንዲኖረው እንደሚፈልጉ ሲሰሙ አባቴ ምርጥ ዘር የነበረችው ብቸኛዋ ላማችን የወለደችውን ጥጃ ለቤቴል ሰጠ። ከቤታችን የመጀመሪያዋ “ቤቴላዊ” ያቺ ጥጃ ናት እያልን እንቀልድ ነበር። የወላጆቼ መልካም ምሳሌነት ‘እጄ ሥራ እንዳይፈታ’ የማድረግና ለይሖዋ ምርጤን የመስጠት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብኝ አድርጓል። (መክብብ 11:6) እንዲያውም ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅኩት መንገድ እጄን የምጠቀምበት አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ጥረቴንም ባርኮልኛል። እስቲ ታሪኬን ልንገራችሁ።

 ያደግኩት ከታላቅ እህቴና ወንድሜ ጋር በእንግሊዝ ገጠራማ አካባቢ በምትገኝ ቢስተር የተባለች መንደር አቅራቢያ ነው። በዚያ ወላጆቼ በእርሻ ላይ የምትገኝ አንዲት ጎጆ ተከራይተው ነበር። አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ የእህቴንና የወንድሜን ፈለግ በመከተል ዘወትር አቅኚ ሆንኩ። በኋላም በስኮትላንድ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ከዚያም በ1970፣ 23 ዓመት ሲሞላኝ በለንደን ቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ። በዚያ ሳለሁ ስለ ምልክት ቋንቋ በሰፊው የማወቅ አጋጣሚ አገኘሁ። ይህ አጋጣሚ ሕይወቴን አዲስ መስመር አስያዘልኝ፤ ይህም የኋላ ኋላ ብዙ በረከትና ደስታ አስገኝቶልኛል።

ምልክት ቋንቋ መማር

 በቤቴል ሳለሁ ሚል ሂል በተባለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ በዚያም በርከት ካሉ መስማት የተሳናቸው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተዋወቅኩ። ቋንቋቸውን አለመቻሌ ከእነሱ ጋር ከመቀራረብ እንዲያግደኝ አልፈለግኩም። ስለዚህ በስብሰባ ሰዓት፣ መስማት ከተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ለመቀመጥ ወሰንኩ።

 በዚያን ጊዜ በብሪታንያ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ አልነበረም። መስማት የተሳናቸው ሰዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚካሄዱት ጉባኤዎች ላይ ከመገኘት ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚያስተረጉሙት መስማት የሚችሉ ወንድሞችና እህቶች፣ የእንግሊዝኛውን ቋንቋ ሰዋስው ቃል በቃል እየተከተሉ ያስተረጉሙ ነበር። መስማት የተሳናቸው ወንድሞቼና እህቶቼ በትዕግሥት ምልክት ቋንቋ ካስተማሩኝ በኋላ ግን ቋንቋው የራሱ የሰዋስው ሕግና የቃላት ቅደም ተከተል እንዳለው ተገነዘብኩ። ለእነሱ እንግሊዝኛ ባዕድ ቋንቋ ነው ሊባል ይችላል! ይህን ሐቅ መገንዘቤ መስማት የተሳናቸውን ጓደኞቼን ይበልጥ እንድወዳቸውና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በታማኝነት ለመገኘት የሚያደርጉትን ጥረት እንዳደንቅ አደረገኝ። ምልክት ቋንቋን በደንብ ለማወቅ የማደርገውንም ጥረት አጠናከርኩ።

 በብሪታንያ ያሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በስፋት የሚጠቀሙት የብሪታንያ ምልክት ቋንቋን ነው። በጊዜ ሂደት በስብሰባዎቻችን ላይ የሚያስተረጉሙት አስተርጓሚዎች የእንግሊዝኛውን ሰዋስው ተከትለው ከማስተርጎም ይልቅ የራሱ የሰዋስው ሕግ ያለውን የብሪታንያ ምልክት ቋንቋ መጠቀም ጀመሩ። ይህም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከስብሰባዎች ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አድርጓል። መስማት ከሚችሉ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸውም ጋር ይበልጥ አንድነት እንዲኖራቸው አስችሏል። ያለፉትን 50 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ የምልክት ቋንቋውን መስክ አትረፍርፎ እንደባረከው ይሰማኛል። የይሖዋ ፈቃድ ሆኖ እኔም የተወሰነ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻልኩባቸውን አንዳንድ ወሳኝ ለውጦች ላካፍላችሁ።

በምልክት ቋንቋ መስክ ከፍተኛ እድገት ተገኘ

 በ1973 ማለትም ሽማግሌ ሆኜ ከተሾምኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ማይክል ኢገርስ የተባለ መስማት የተሳነው ወንድም በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ አንዳንድ ስብሰባዎችን እንድናደርግ ሐሳብ አቀረበ። ቅርንጫፍ ቢሮው እኔና አንድ ሌላ የጉባኤ ሽማግሌ በደቡብ ምሥራቅ ለንደን በሚገኝ ዴትፎርድ የተባለ ቦታ በምልክት ቋንቋ ወርሃዊ ስብሰባዎችን እንድናደራጅ ፈቃድ ሰጠ።

 ውጤቱ አስደናቂ ነበር! በለንደን እና በደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኙ። በመጨረሻ መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት ቻሉ። ከስብሰባው በኋላ ሻይ ቡና እያልን ተሞክሮዎችን አወራን። ለአንዳንዶቹ ወንድሞችና እህቶች እረኝነት ማድረግ የምችልበት አጋጣሚም አገኘሁ።

 ከጊዜ በኋላ በርሚንግሃም እና ሸፊልድ በተባሉት ከተሞችም በምልክት ቋንቋ ስብሰባዎች መካሄድ ጀመሩ። የብሪታንያ ምልክት ቋንቋን መማር የሚፈልጉ መስማት የሚችሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶችም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ጀመር። ከእነዚህ ፈቃደኛ ወንድሞችና እህቶች መካከል አብዛኞቹ ከጊዜ በኋላ በመላው አገሪቱ የምልክት ቋንቋን መስክ ለማስፋፋት አግዘዋል።

የዕድሜ ልክ የሕይወት አጋር አገኘሁ

በሠርጋችን ቀን

 በ1974 በቤቴል አቅራቢያ ባለ ጉባኤ ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆና ከምታገለግል ስቴላ ባርከር የተባለች ቆንጆ እህት ጋር ተዋወቅኩ። እኔና ስቴላ በጣም የተዋደድን ሲሆን በ1976 ትዳር መሠረትን፤ ከዚያም አብረን በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ጉባኤያችን የሚገኘው በሰሜን ለንደን ባለ ሃክኒ የተባለ ቦታ ነበር። በዚያ ሳለን ስቴላም ከእኔ ጋር በምልክት ቋንቋ መስክ ማገልገል ጀመረች። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ እንደተጋባን በአቅኚነት አብረን ማገልገላችን ለትዳራችን ጥሩ ጅማሬ እንደሆነልን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።

 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኔና ስቴላ በቤቴል በተመላላሽነት እንድናገለግል ተጋበዝን። ሕይወታችን በእንቅስቃሴ የተሞላ ነበር! ከቤቴል ሥራዬ ጎን ለጎን ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግል እንዲሁም ለሽማግሌዎች በተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ አስተምር ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ በእንግሊዝኛ በሚካሄዱ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምልክት ቋንቋውን ትርጉም የማስተባበር ሥራ ተሰጠኝ። ሥራው አድካሚ ቢሆንም አስደሳችና እረፍት የሚሰጥ ነበር።​—ማቴዎስ 11:28-30

 በ1979 እና በ1982 ሁለቱ ወንዶች ልጆቻችን ሳይመን እና ማርክ ተወለዱ። ወላጅነት ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም አስደሳችም ነው። ይህን ከባድ ኃላፊነት መወጣት የቻልነው እንዴት ነው? እኔና ስቴላ በቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቼ ምክንያት ከቤት ራቅ ብዬ መጓዝ ሲኖርብኝ በቤተሰብ አብረን ለመሄድና እግረ መንገዳችንን ዘና ብለን ለመምጣት ወሰንን። ልጆቻችን ይሖዋን ማገልገል አስደሳች ነገር እንደሆነ እንዲያዩ ፈልገን ነበር! ውጤቱ ምን ሆነ? ልጆቻችን ከፍ እያሉ ሲሄዱ ምልክት ቋንቋ የተማሩ ከመሆኑም ሌላ በአቅኚነት ማገልገልም ጀመሩ። ከዚያም የወላጆቼ ጥጃ “የቤቴል አገልግሎቷን” ከጀመረች ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ሳይመን እና ማርክም በቤቴል ማገልገል ጀመሩ። በዚህ በጣም ተደሰትን!

በ1995 ከስቴላ እና ከሁለቱ ልጆቻችን ጋር

መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መርዳት

 እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ በብሪታኒያ አንድም መስማት የተሳነው የጉባኤ ሽማግሌ አልነበረም፤ የነበሩት የተወሰኑ የጉባኤ አገልጋዮች ብቻ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ አገልጋዮች “የማስተማር ብቃት” ያላቸውና የበላይ ተመልካች ሆነው ለማገልገል ብቁ መሆናቸውን የሚገመግሙት ምልክት ቋንቋ የማይችሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች ነበሩ። (1 ጢሞቴዎስ 3:2) መስማት ከተሳናቸው የጉባኤ አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆነው ወንድም በርናርድ ኦስትን የሚያገለግለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚካሄድ ጉባኤ ውስጥ ነበር። በርናርድ ለይሖዋ በጎች ከልቡ የሚያስብ የተከበረ ወንድም ነው። ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል መሾሙን ስሰማ በጣም ደስ አለኝ! እንዲያውም በብሪታንያ የመጀመሪያው መስማት የተሳነው የጉባኤ ሽማግሌ እሱ ነው።

 በ1996 በምልክት ቋንቋ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ ተደረገ፤ ቅርንጫፍ ቢሮው በብሪታንያ የመጀመሪያው ምልክት ቋንቋ ጉባኤ እንዲቋቋም ፈቃድ ሰጠ። ጉባኤው የሚገኘው በምዕራብ ለንደን፣ ኢሊንግ የተባለ ቦታ ነበር። ከዚያ በኋላ በምልክት ቋንቋ መስክ ብዙ እድገት ታይቷል።

ከሁሉም ክርስቲያናዊ ስብስባዎች ተጠቃሚ መሆን

 በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ከቤቴል የአገልግሎት ዘርፍ ጋር አብሬ በመሥራት ከምልክት ቋንቋ መስክ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እሰጥ ነበር። አንዳንዴ ወንድሞች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው በመጻፍ፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚካሄዱ ሳምንታዊና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች እንዲረዱ ማገዝ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይጠይቃሉ። መጀመሪያ ላይ፣ በሳምንታዊና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ንግግሮች ወደ ምልክት ቋንቋ የሚተረጎሙበት ዝግጅት አልነበረም፤ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችም አልነበሩም። ስለዚህ መስማት የሚችሉትንም ሆነ መስማት የተሳናቸውን ወንድሞች ይሖዋን በትዕግሥት እንዲጠባበቁ በተደጋጋሚ ማበረታታት አስፈልጎኛል።

 በመጨረሻም ትዕግሥታችን ፍሬ አፈራ! ብዙም ሳይቆይ ቅርንጫፍ ቢሮው በእንግሊዝኛ በሚካሄዱ ሳምንታዊና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምልክት ቋንቋ ትርጉም እንዲኖር ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። በተጨማሪም መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ተናጋሪውንና አስተርጓሚውን በደንብ ማየት እንዲችሉ ከፊት እንዲቀመጡ ዝግጅት ተደረገ። መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ይሖዋ በእርግጥ እንደሚወዳቸውና በእሱ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ማስተዋል ቻሉ።

 ሚያዝያ 1, 1995 በዌስት ሚድላንድስ ባለች ደድሊ የተባለች ከተማ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ የመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ ልዩ ስብሰባ ተካሄደ። ቀደም ሲል በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ያገለግል የነበረውን ወንድም ዴቪድ መሪን ስብሰባውን በማደራጀቱ ሥራ የማገዝ አጋጣሚ አግኝቻለሁ። መስማት የተሳናቸው አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በፕሮግራሙ ላይ ለመገኘት ሲሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘዋል፤ በስተ ሰሜን ከስኮትላንድ፣ በስተ ደቡብ ምዕራብ ደግሞ ከኮርንዎል ድረስ የመጡ ወንድሞችና እህቶች ነበሩ። ሁሉም ተሰብሳቢዎች ከ1,000 በላይ ሰዎች በተገኙበት በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ በመገኘታቸው ምን ያህል ተደስተው እንደነበር ትዝ ይለኛል።

በ1995 ለመጀመሪያ ጊዜ በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ከወንድም ዴቪድ መሪ ጋር

 በ2001 ቅርንጫፍ ቢሮው እኔንና ወንድም መሪን ለቀጣዩ ዓመት በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ የክልል ስብሰባ እንድናደራጅ ኃላፊነት ሰጠን። ይህ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነበር! ሆኖም ይሖዋ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያደረጉትን ጥረት ስለባረከ ስብሰባው የተሳካና የማይረሳ ሊሆን ችሏል! ከዚያ በኋላ ባሉት የተወሰኑ ዓመታት በምልክት ቋንቋ የሚካሄዱ የወረዳና የክልል ስብሰባዎችን በበላይ ተመልካችነት የመከታተል መብት አግኝቻለሁ፤ በይሖዋ እርዳታ ሥራውን የሚረከቡ ብቃት ያላቸው ወጣት ወንድሞች እስከተገኙበት ጊዜ ድረስ በዚህ ኃላፊነት ቀጥያለሁ።

መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የተዘጋጁ ቪዲዮዎች

 በ1998 በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያው ጽሑፍ ማለትም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር በቪዲዮ ካሴት በመውጣቱ በጣም ተደሰትን፤ ከዚያ በኋላም በርካታ ጽሑፎች ተተረጎሙ። ብሮሹሩን ተጠቅመን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተናል።

 በ2002 በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ የመንግሥቱ መዝሙሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብሪታንያ ምልክት ቋንቋ ተተረጎሙ። መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ምልክት የሚያሳየውን ወንድም ተከትለው ውብ የሆኑትን ቃላት “መዘመር” እንዲሁም ስሜት ቀስቃሽ በሆነው የሙዚቃው ምት መመሰጥ ቻሉ። መስማት የተሳነው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ለመጀመሪያ ጊዜ መዝሙሩን “እየተከተለ ሲዘምር” በደስታ ያነባ እንደነበር አስታውሳለሁ!

 በ2002 በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ሌላም ታሪካዊ ነገር ተከናውኗል። በለንደን ያለው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ አስቀድሞ የተቀረጸ ድራማ እንዲያዘጋጅ ተጋበዘ። ሆኖም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ምንም ልምድ አልነበረንም! በዚህ ጊዜም ቢሆን የይሖዋን እርዳታ ማየት ችለናል፤ ፊልሞችን መሥራትና ማቀናበር የሚችሉ ወንድሞችን እንድናገኝ ረዳን። የተገኘው ውጤት በጣም አስደናቂ ነበር! ደግሞም ከ2003 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ውስጥ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ የቪዲዮ ድራማዎችን በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ የማዘጋጀቱን ሥራ የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ስለነበር ይህ ልምድ በጣም ጠቅሞኛል።

 እኔና ስቴላ በቤቴል ከልጆቻችን ጋር ማገልገል በመቻላችን ደስተኞች ነን። ሆኖም ሥራው ከባድ ነው! ለበርካታ ሳምንታት የሚዘልቀው ልምምድና ቀረጻ፣ ተቀጂዎቹንም ሆነ የዝግጅት ቡድኑን በአካልና በአእምሮ የሚያዝል ነው። የሚደረገው ጥረት ግን አያስቆጭም! መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ሕያው ሲሆኑላቸውና የደስታ እንባ ሲያነቡ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥራል።

 የይሖዋ መንፈሳዊ ስጦታ በዚህ አላበቃም። በ2015 በብሪታንያ ምልክት ቋንቋ በቪዲዮ የተዘጋጀውን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም አገኘን። ከዚያም በ2019 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የማቴዎስ መጽሐፍ በቪዲዮ መልክ ተዘጋጅቶ ወጣ። አሁን ሙሉው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ያለን ሲሆን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝግጅት ደግሞ በጥሩ ሁኔታ እየገፋ ይገኛል። መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን ለማመስገን ቃላት ያጥራቸዋል!

 እኛ የይሖዋ ሕዝቦች በሰማይ ያለው አባታችን ያለውን ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍቅር በሚያንጸባርቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ታቅፈናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) እኔና ቤተሰቤ የይሖዋ ድርጅት መስማት የተሳናቸውንና ዓይነ ስውራንን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎችን ለመርዳት የሚያውለውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ስናስብ በጣም እንገረማለን። a

 እነዚህ ጥረቶች በእርግጥም ብዙ ፍሬ አስገኝተዋል፤ በአሁኑ ጊዜ በብሪታንያ በርካታ የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። ‘ሥራው በትንሹ ከተጀመረበት’ ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ ያለውን እድገት ማየት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታና እርካታ ይሰማኛል። (ዘካርያስ 4:10) እርግጥ ነው፣ ለሁሉም ነገር ምስጋና የሚገባው ይሖዋ ነው። ድርጅቱን የሚመራው እሱ ነው። አገልጋዮቹ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰብኩ የሚያስታጥቃቸው እሱ ነው። የመንግሥቱ ዘር ምሥራቹን መስማት በሚገባቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርገውም እሱ ነው።

በ2023 ከስቴላ ጋር