ታፓኒ ቪታላ | የሕይወት ታሪክ
መስማት የተሳናቸውን ሰዎች የመርዳት ፍላጎቴን ማሳካት
የይሖዋ ምሥክሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኛቸው “መስማት የተሳናቸው ሰዎች [ጆሮ] ይከፈታል” የሚለውን ተስፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩኝ። (ኢሳይያስ 35:5) ሆኖም ስወለድ ጀምሮ መስማት ስለማልችል ድምፅን መስማት ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ከበደኝ። በዚህም የተነሳ ይህ ተስፋ ያን ያህል አላጓጓኝም። ይበልጥ የተደሰትኩት የአምላክ መንግሥት ማንኛውንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል፣ ጦርነት፣ ሕመም፣ አልፎ ተርፎም ሞት እንደሚያስወግድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲያሳዩኝ ነው። በጊዜ ሂደት፣ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች መስማት የተሳናቸው ሰዎች የማካፈል ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ።
የተወለድኩት በ1941 በቪራት፣ ፊንላንድ ሲሆን ሁሉም የቤተሰቤ አባላት ማለትም ወላጆቼ፣ ታናሽ ወንድሜና እህቴ እንዲሁም አብዛኞቹ ዘመዶቻችን መስማት የተሳናቸው ናቸው። የምንነጋገረው በምልክት ቋንቋ ነው።
አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማር
የምማረው ከቤታችን 240 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር፤ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ምልክት ቋንቋ መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ ነው። በወቅቱ ፊንላንድ ውስጥ የምልክት ቋንቋ ትምህርት ቤቶች፣ ተማሪዎች የንግግር ቋንቋን ከንፈር ከማንበብ ችሎታ ጋር አጣምረው እንዲጠቀሙ ያስገድዱ ነበር። አስተማሪዎቻችን ምልክት ቋንቋ ስንጠቀም ካዩን በማስመሪያ ወይም በቀጭን ዱላ በኃይል ስለሚመቱን ጣቶቻችን ለቀናት ያብጡ ነበር።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ የግብርና ኮሌጅ ገባሁ። ወላጆቼ እርሻ ስለነበራቸው ሙያውን መማር ነበረብኝ። ከኮሌጅ ስመለስ ጠረጴዛ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን አየሁ። አባቴ እነዚህ መጽሔቶች አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንደያዙና መስማት የሚችሉ አንድ ባልና ሚስት እሱንና እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ እያስተማሯቸው እንደሆነ ነገረኝ። እነዚያ ባልና ሚስት ከወላጆቼ ጋር የሚነጋገሩት ወረቀትና እስክሪብቶ በመጠቀም ነበር።
አባቴ፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ውብ ገነት እንደምትሆንና የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ነገረኝ። እኔ ግን የተማርኩት የሞቱ ሰዎች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ነው። አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮቹ ጋር የሚነጋገረው በምልክት ቋንቋ ስላልሆነ የነገሩትን ነገር በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ።
ባልና ሚስቱ ድጋሚ ከወላጆቼ ጋር ለመወያየት ሲመጡ አባቴ ስለነገረኝ ነገር ጠየቅኳቸው። እነሱም “አባትህ ያለው ልክ ነው” ብለው አረጋገጡልኝ። ከዚያም ኢየሱስ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ስለ ትንሣኤ የተናገረውን ሐሳብ አሳዩኝ። አምላክ ክፋትን ሁሉ ከምድር ላይ የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ሰዎች ፍጹም ጤንነትና ሰላም አግኝተው ለዘላለም እንደሚኖሩ ነገሩኝ።—መዝሙር 37:10, 11፤ ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:1-4
ይበልጥ ማወቅ ስለፈለግኩ አንቴሮ ከተባለ መስማት የሚችል የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። አንቴሮ የምልክት ቋንቋ ስለማይችል የማስጠኛ መጽሐፉ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች መልስ ወረቀት ላይ እጽፍለት ነበር። እሱም መልሶቹን ካነበበ በኋላ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ወይም ሐሳቦችን ይጽፍልኛል። ይህን ዘዴ በመጠቀም በየሳምንቱ ለሁለት ሰዓት ያህል በትዕግሥት ያስጠናኝ ነበር።
በ1960 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ፤ ፕሮግራሙ ወደ ምልክት ቋንቋ ይተረጎም ነበር። ዓርብ ከሰዓት በኋላ፣ በቀጣዩ ቀን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት እንደሚኖር የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። ስለዚህ ቅዳሜ ጠዋት የዋና ልብሴንና ፎጣዬን ይዤ ሄጄ ተጠመቅኩ! a ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ እንዲሁም ታናሽ ወንድሜና እህቴም ተጠመቁ።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ማካፈል
የተማርኳቸውን ነገሮች ለሌሎች መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማካፈል እፈልግ ነበር፤ ይህን ማድረግ የምችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ደግሞ ምልክት ቋንቋ መጠቀም ነው። መጀመሪያ ላይ፣ በተወለድኩበት አካባቢ ላሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በቅንዓት መስበክ ጀመርኩ።
ብዙም ሳይቆይ፣ ትልቅ የንግድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ታምፐሬ ተዛወርኩ። በዚያ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለማግኘት ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ የቤቶቹን ባለቤቶች፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ያውቁ እንደሆነ እጠይቃቸው ነበር። በዚህ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አገኘሁ፤ ከዚያም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በታምፐሬ ከአሥር የሚበልጡ መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎች ተገኙ።
በ1965 ማይረ ከተባለች ደስ የምትል እህት ጋር ተዋወቅኩ። ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ትዳር መሠረትን። ማይረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምልክት ቋንቋ የተማረች ሲሆን አብረን ይሖዋን ባገለገልንባቸው 50 ዓመታት ታማኝና ትጉ አጋር ሆናኛለች።
ከተጋባን ከሁለት ዓመት በኋላ ልጃችን ማርኮ ተወለደ። እሱ መስማት ስለሚችል የአፍ መፍቻ ቋንቋው የሆነውን የፊኒሽ ቋንቋንና የፊኒሽ ምልክት ቋንቋን እዚያው ቤት ውስጥ መማር ቻለ። ማርኮ በ13 ዓመቱ ተጠመቀ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ብዙ አዳዲስ ሰዎች በታምፐሬ ያለውን የምልክት ቋንቋ ቡድን ተቀላቀሉ። ስለዚህ በ1974፣ መስማት የተሳናቸው የይሖዋ ምሥክሮች ወደሌሉባት ተኩ የተባለች ከተማ ተዛወርን። በዚህች ከተማም ከቤት ወደ ቤት እየሄድን መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ፈለግን። በተኩ በቆየንባቸው ዓመታት ውስጥ 12 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ተጠምቀዋል።
በባልቲክ አገራት ማገልገል
በ1987 ማርኮ በቤቴል እንዲያገለግል ተጋበዘ። በተኩ ያለው የምልክት ቋንቋ ቡድን ተጠናክሮ ስለነበር ወደ ሌላ አካባቢ ለመዛወር ዕቅድ ማውጣት ጀመርን።
በወቅቱ በምሥራቅ አውሮፓ ባሉ ክልሎች የስብከት ነፃነት ተገኝቶ ነበር። ስለዚህ መስማት ከተሳነው ሌላ ወንድም ጋር ጥር 1992 ወደ ታሊን፣ ኢስቶኒያ ተጓዝን።
በዚያም መስማት የተሳነው ወንድም ካላት አንዲት እህት ጋር ተገናኘን። ወንድሟ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ባይኖረውም መስማት የተሳናቸው ብዙ ኢስቶኒያውያንን እንድናገኝ በደግነት ረዳን። በኢስቶኒያ በቆየንበት የመጨረሻ ምሽት ላይ በታሊን በተደረገ የኢስቶኒያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ወሰደን። በስብሰባው ላይ በጊዜ ተገኝተን ጠረጴዛውን በኢስቶኒያኛ እና በሩሲያኛ በተዘጋጁ መጽሔቶችና መጻሕፍት ሞላነው። በዚያን ዕለት 100 መጻሕፍትና 200 መጽሔቶች ያበረከትን ሲሆን ወደ 70 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን አድራሻ ተቀበልን። በኢስቶኒያ በምልክት ቋንቋ የሚደረገው አገልግሎት መሠረት የተጣለው በዚያ ምሽት ነበር!
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኔና ማይረ በተደጋጋሚ ለስብከት ወደ ኢስቶኒያ መሄድ ጀመርን። ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት የምናሳልፈውን ጊዜ በመቀነስ ዘወትር አቅኚዎች ሆንን። ወደ ታሊን በጀልባ ለመጓዝ እንዲቀለን ስንል በ1995 ወደ ሄልሲንኪ አቅራቢያ ተዛወርን። በኢስቶኒያ በአገልግሎት ያገኘነው ውጤት ከጠበቅነው እጅግ የላቀ ነበር!
በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩን ሲሆን ከጥናቶቻችን መካከል 16ቱ እድገት አድርገው ተጠመቁ፤ ከእነዚህ መካከል ማየትም ሆነ መስማት የማይችሉ ሁለት እህትማማቾች ይገኙበታል። እህትማማቾቹን የማስጠናቸው እጅ ለእጅ ተያይዞ ምልክት ማሳየትን የሚጠይቅ ታክታይል የምልክት ቋንቋ የተባለ ዘዴ በመጠቀም ነበር።
መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ማስጠናት ፈታኝ ነበር። በወቅቱ በክልላችን በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ስላልነበረ በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡትን ማራኪ ሥዕሎች አንድ መጽሐፍ ላይ ሰብስቤ በመለጠፍ አገልግሎት ላይ እጠቀምባቸው ነበር።
በፊንላንድ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ወደ ላትቪያ እና ሊትዌኒያ ሄጄ በእነዚህ የባልቲክ አገራት በምልክት ቋንቋ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል እንድገመግም ግብዣ አቀረበልኝ። በተደጋጋሚ ወደ እነዚህ አገራት በመሄድ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመፈለጉ ሥራ የአካባቢውን ወንድሞችና እህቶች አግዘናል። ሁሉም አገር ማለት ይቻላል፣ የራሱ ምልክት ቋንቋ አለው። በመሆኑም የሊትዌኒያ፣ የላትቪያና የኢስቶኒያ ምልክት ቋንቋ ተምሬአለሁ፤ በተጨማሪም በባልቲክ አገራት የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ሩሲያውያን የሚጠቀሙበትን የሩሲያ ምልክት ቋንቋ በተወሰነ መጠን ተምሬአለሁ።
የሚያሳዝነው ለስምንት ዓመታት ያህል ወደ ባልቲክ አገሮች እየተጓዝን ካገለገልን በኋላ ማይረ ፓርኪንሰንስ የሚባል የነርቭ በሽታ ስለያዛት ለማቆም ተገደድን።
መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት መደራጀት
በ1997 በፊንላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን ተቋቋመ። እኔና ማይረ የምንኖረው በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ ስለነበር የምልክት ቋንቋ ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ ሥራ መርዳት ችለናል፤ ከልጃችን ከማርኮ ጋር አብረን ነበር የምንሠራው። አሁንም አልፎ አልፎ በዚህ ሥራ አግዛለሁ። በኋላም ማርኮና ባለቤቱ ኪርሰ በሌሎች አገሮች ያሉ የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድኖችን በማሠልጠኑ ሥራ ተካፍለዋል።
ቅርንጫፍ ቢሮው መስማት የሚችሉ አስፋፊዎች ምልክት ቋንቋ እንዲማሩም ዝግጅት አድርጎ ነበር። ይህ ዝግጅት ብዙዎች የምልክት ቋንቋ ቡድኖችንና ጉባኤዎችን በመቀላቀል የስብከቱን ሥራና ስብሰባዎችን እንዲደግፉ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን ተቀብለው እንዲሠሩ አስችሏል።
የመርዳት ፍላጎቴ አሁንም አልቀዘቀዘም
በ2004 እኔና ማይረ በሄልሲንኪ የመጀመሪያው የፊኒሽ ምልክት ቋንቋ ጉባኤ እንዲቋቋም መርዳት ቻልን። በሦስት ዓመት ውስጥ ጉባኤው ብዙ አቅኚዎች ያሉበት ጠንካራና ቀናተኛ ጉባኤ ሆነ።
በድጋሚ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር ማቀድ ጀመርን። በ2008 ወደ ታምፐሬ አቅራቢያ የተዛወርን ሲሆን ከ34 ዓመት በፊት ለቀን ወደሄድነው የምልክት ቋንቋ ቡድን ተመለስን። ከአንድ ዓመት በኋላ ይህ የምልክት ቋንቋ ቡድን በፊንላንድ ሁለተኛው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ሆነ።
በእነዚህ ዓመታት ግን የማይረ ጤንነት ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ ነበር። በ2016 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ያለአንዳች ቅሬታ አስታምሜአታለሁ። ማይረ በጣም ትናፍቀኛለች፤ ሕመም በማይኖርበት አዲስ ዓለም ውስጥ እሷን የማገኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:4
መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ምሥራቹን የማካፈሉ ሥራ ላለፉት 60 ዓመታት የሕይወቴ ዋነኛ ክፍል ሆኖ ቆይቷል፤ ያም ሆኖ ምሥራቹን የመስበክ ፍላጎቴ አሁንም አልቀዘቀዘም!
a በዚህ ወቅት የጉባኤ ሽማግሌዎች የጥምቀት ዕጩዎችን አስቀድመው የሚያነጋግሩበት ዝግጅት ገና አልተጀመረም ነበር።