በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሪ ሬኖልድስ | የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ምርጤን እንድሰጠው ረድቶኛል

ይሖዋ ምርጤን እንድሰጠው ረድቶኛል

 ሴሲል የተባለ በዕድሜ የገፋ መንፈሳዊ ወንድም የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ ሲሰጠኝ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ። የሰጠኝ ለግል ጥናት ይጠቀምበት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ስለነበር ኅዳጉ ላይ በእጅ የተጻፉ ማስታወሻዎች ነበሩት። ‘እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ ነው!’ ብዬ አሰብኩ።

 ሴሲል ለሌሎች ከልቡ የሚያስብ ትሑት ወንድም ነበር። የእሱ፣ የእናቴ እንዲሁም በጉባኤያችን የነበሩ ሌሎች ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ “ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት” እንዲያድርብኝ ወይም ለይሖዋ ምርጤን ለመስጠት እንድነሳሳ አድርጎኛል። (ፊልጵስዩስ 2:13) እስቲ ታሪኬን ልንገራችሁ።

የእናቴ ቅንዓት ለተግባር አነሳስቶኛል

 የተወለድኩት በ1943 ነው። ወላጆቼ የሚኖሩት በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ ሸንኮራ አገዳ በሚመረትበት አካባቢ በምትገኝ ቡንዳበርግ የተባለች ባሕር ዳርቻ ያለች ከተማ አቅራቢያ ባለ እርሻ ላይ ነበር። የአካባቢው ሰዎች ቅዳሜ ምሽት ላይ ወደ ከተማ ወጣ ብለው አብረው ጊዜ የማሳለፍ ልማድ ነበራቸው። በ1939 ወላጆቼ እንደተለመደው ወደ ከተማ ወጣ ብለው ሳለ ሁለት አቅኚዎችን (የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) አገኙ፤ አቅኚዎቹ ወላጆቼን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አነጋገሯቸው። በተማሩት ነገር ልባቸው በጣም ስለተነካ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ስለዚህ እኔና እህቴ ጂን ያደግነው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው። የሚያሳዝነው ግን አባቴ ቤት ውስጥ ባጋጠመ አደጋ ሕይወቱ አለፈ። በወቅቱ ገና ሰባት ዓመቴ የነበረ ሲሆን በአባቴ ሞት በጣም ተደናግጬ ነበር። ያም ሆኖ አባቴ ጠንካራ ሠራተኛና ተጫዋች ሰው እንደነበር በደንብ አስታውሳለሁ። እሱን በትንሣኤ ለማግኘትና ከእሱ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ በጣም እጓጓለሁ!—የሐዋርያት ሥራ 24:15

 እናቴ ደግና ምክንያታዊ ሰው ነበረች። እኔና እህቴ የምንወደውንና የምንጠላውን ነገር በነፃነት እንድንናገር ዕድል ትሰጠናለች። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ግን ጥብቅ ነበረች። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንገኝ ነበር፤ ደግሞም እናታችን እኔና ጂን የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ልጆች ጋር ከትምህርት ሰዓት ውጭ በምናሳልፈው ጊዜ ላይ ገደብ እንድናበጅ ትመክረን ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ እንደዚያ ያለ ጥብቅ አቋም በመያዟ ደስተኛ ነኝ።

የ14 ዓመት ገደማ ልጅ ሳለሁ

 እናታችን ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪ ነበረች፤ በተደጋጋሚ የእረፍት ጊዜ አቅኚ (አሁን ረዳት አቅኚ ይባላል) ሆና ታገለግል ነበር። ከ50 ወደሚበልጡ ቤቶች በቋሚነት በመሄድ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ታበረክት እንደነበር አስታውሳለሁ። ዕድሜዋ ከገፋና አቅሟ ከደከመ በኋላም እንኳ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የምታሳየው አሳቢነት አልቀነሰም። ለሌሎች በተለይም ለልጆቿ የነበራት ፍቅር እንድንወዳትና እሷን ለመምሰል እንድንጥር አነሳስቶናል። በመሆኑም በ1958 በ14 ዓመቴ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅኩ።

ከጥሩ ወዳጆቼ ያገኘሁት ማበረታቻ

 ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ጉባኤያችን የነበረ ሩዶልፍ የተባለ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣትም ተጠመቀ። ሩዶልፍ የመጣው ከጀርመን ነው። እኔና ሩዶልፍ ሁሌ ቅዳሜ ጠዋት፣ ቤተሰቦቻቸው ዕቃ እስኪገዛዙ ድረስ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው ለሚጠብቁ ሰዎች እንሰብክ ነበር።

 ሩዶልፍ ቀናተኛ ወንድም ነው፤ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከእሱ ጋር የእረፍት ጊዜ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ይጋብዘኝ ነበር። በአንድ ወቅት ከቡንዳበርግ በስተ ሰሜን 190 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኝ ግላድስቶን የተባለች ከተማ ሄደን ለስድስት ሳምንት አገልግለናል። እሱ ያሳየኝ አሳቢነት እንዲሁም የእረፍት ጊዜ አቅኚ ሆኜ ሳገለግል ያገኘሁት ደስታ ዘወትር አቅኚ ሆኖ የማገልገል ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አደረገ። በ16 ዓመቴ እዚህ ግብ ላይ መድረስ ቻልኩ፤ መላ ሕይወቴን፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማሳለፍ ቆርጬ ነበር።

 አቅኚነት እንደጀመርኩ የተመደብኩት ከቡንዳበርግ በስተ ሰሜን በምትገኝ ማካይ የተባለች ባሕር ዳርቻ ላይ ያለች ከተማ ነበር፤ ይህች ከተማ ለግሬት ባሪየር ሪፍ ቅርብ ናት። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በ17 ዓመቴ በአውስትራሊያ ብዙ ሰዎች በማይኖሩበት ከከተማ ወጣ ብሎ ያለ አካባቢ ልዩ አቅኚ a ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በአቅኚነት አብሮኝ ያገለግል የነበረው በዕድሜ 30 ዓመት የሚበልጠኝ ቤነት (ቤን) ብሪክል የተባለ ቅቡዕ ወንድም ነው። b ብዙ ተሞክሮ ካለውና ብዙዎች እንደተዋጣለት አቅኚ ከሚቆጥሩት ከዚህ ወንድም ጋር ማገልገል እንዴት ያለ ልዩ መብት ነው!

በ1963 ርቆ በሚገኝ አካባቢ ላለች አንዲት አቦርጂን ሴት ስሰብክ

 በሰሜን ምዕራብ ኩዊንስላንድ የነበረው ክልላችን የካርፔንታሪያ ባሕረ ሰላጤን የሚያዋስን ነበር። ብዙ ሰዎች በማይኖሩበት በዚያ ክልል ውስጥ በወቅቱ የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች እኔና ቤን ብቻ ነበርን። አንዳንዴ ከአንዱ ቤት ወደ ቀጣዩ ቤት ለመድረስ ለሰዓታት መንዳት ያስፈልገናል። አቧራማ በሆኑ መንገዶች ላይ ለረጅም ሰዓታት ስንጓዝ ቤን ብዙ ጊዜ በአገልግሎት ስላገኛቸው ተሞክሮዎች ያጫውተኛል። ለምሳሌ በአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታግዶ በነበረበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የድምፅ ማጉያ የተገጠመላቸውን መኪኖች c ተጠቅመው ሲሰብኩ የነበረውን ሁኔታ ይነግረኛል።

አንድ ወንድም እና እኔ (መሃል ላይ) ርቆ በሚገኝ አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ

 የቀኑ መጨረሻ ላይ አገልግሎታችንን ስንጨርስ መንገዱ ዳርቻ አካባቢ ያለ አመቺ ቦታ ፈልገን ድንኳን እንተክላለን። d ራታችንን ለመሥራት እንጨት እንለቅምና እሳት እናቀጣጥላለን። ለአልጋነት የምጠቀመው መሬት ላይ የሚነጠፍ ውኃ የማያሳልፍ ንጣፍ፣ ብርድ ልብስና ትራስ ነበር። በሰው ሠራሽ መብራቶች ያልደበዘዘውንና በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ቀና ብዬ ስመለከት በይሖዋ ሥራዎች ምን ያህል እደመም እንደነበር አስታውሳለሁ።

 በዚህ ርቆ የሚገኝ አካባቢ የመኪና ብልሽት በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል። በአንድ ወቅት እየሄድን ሳለ የሆነ የመኪናችን ክፍል ተሰበረ። ቀኑ ሞቃታማ ሲሆን ውኃም እያለቀብን ነበር። የተበላሸውን ዕቃ ለመተካት ቤን ሌላ መኪና ተሳፍሮ ክሎንከሪ ወደተባለ ከተማ ሄደ። እኔ መኪናውን እየጠበቅኩ ለሦስት ቀን ገደማ ቆየሁ። በየቀኑ የተወሰኑ መኪኖች ያልፉ ነበር፤ አንዳንድ ሹፌሮች ውኃ በመስጠት ደግነት አሳዩኝ። አንድ ሰውዬ ደግሞ የሆነ ያረጀ መጽሐፍ ሰጠኝ። “አንብበው፤ ይጠቅምህ ይሆናል” አለኝ። መጽሐፉ በድርጅታችን የተዘጋጀ ባይሆንም የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ስላሳለፉት ሕይወት የሚያወሳ መሆኑ በጣም አስገረመኝ!

 እኔና ቤን ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ አብረን በአቅኚነት አገልግለናል። ስንለያይ ቤን መጨረሻ ላይ ያለኝን ነገር አልረሳውም፤ ‘ወንድሜ፣ እስከ መጨረሻው መታገልህን ቀጥል” አለኝ። ቤን ይሖዋን በታማኝነትና በቅንዓት በማገልገል ረገድ የተወው ምሳሌ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ያለኝን ቁርጠኝነት ይበልጥ አጠናከረው።

ጊልያድ ከዚያም ታይዋን

 ርቆ በሚገኘው የአውስትራሊያ ክልል ለተወሰኑ ዓመታት ያህል በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንድሆን ተጋበዝኩ፤ ይህ ሥራ በወረዳው ውስጥ ካለ ከእያንዳንዱ ጉባኤና ርቆ ያለ የአገልግሎት ቡድን ጋር አንድ ሳምንት ገደማ ማሳለፍን የሚጠይቅ ነው። በወረዳ ሥራ በቆየሁባቸው ዓመታት በአራት ወረዳዎች እንዳገለግል ተመድቤአለሁ። ከእነዚህ መካከል በኩዊንስላንድ እና በኒው ሳውዝ ዌልስ ያሉ ጉባኤዎች ይገኙበታል። ከዚያም በ1971 አንድ ያልጠበቅኩት መብት አገኘሁ፤ በኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የሚስዮናዊነት ትምህርት ቤት ማለትም በጊልያድ ትምህርት ቤት 51ኛ ክፍል እንድማር ተጠራሁ። ለአምስት ወራት ያህል ያገኘሁት ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሁም ከተማሪዎችና ከአስተማሪዎች ጋር ያሳለፍኩት የሚያበረታታ ጊዜ ቀጥሎ በታይዋን ለተሰጠኝ የሚስዮናዊነት ምድብ አስታጥቆኛል።

በጊልያድ ትምህርት ቤት አንድ ክፍል ውስጥ የነበርነው ተማሪዎች

 ከኒው ዚላንድ የመጣውን ኢየን ብራውንን ጨምሮ ከእኛ ክፍል ዘጠኝ ተማሪዎች ወደ ታይዋን ተመደብን። ኢየን የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጓደኛዬ ነበር። ሁለታችንም ስለ ታይዋን ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ካርታ ላይ እስክናይ ድረስ ታይዋን የት እንዳለች እንኳ እርግጠኞች አልነበርንም።

 በኩዊንስላንድ ባሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችና በታይዋን መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነበር! መጋፈጥ የነበረብን የመጀመሪያውና ትልቁ ተፈታታኝ ነገር ቻይንኛ ቋንቋ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከሚተላለፈው ትምህርት ውስጥ የምረዳው አንድም ነገር አልነበረም፤ መንፈሳዊ ማበረታቻ የምናገኝበት ትልቁ ምንጭ ደግሞ የጉባኤ ስብሰባ ነው። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በደንብ ለመግባባትም እቸገር ነበር። ይህ ሁኔታ እኔና ኢየን በጊልያድ ያገኘነው ሥልጠናና በዚያ ያካበትነው ጥልቅ እውቀት ያለውን ጥቅም እንድናስተውል አድርጎናል። የጊልያድ ሥልጠና፣ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከልብ የመነጨ ጸሎት ወደፊት መቀጠል እንድንችል ረድተውናል። በአካባቢው ካሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በደንብ መግባባት ባንችልም ለእኛም ሆነ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆኖልናል።

ቻይንኛ መማር

 ታይዋን ከደረስን በኋላ ሁላችንም አጭር የቻይንኛ ቋንቋ ሥልጠና ተሰጠን። አስተማሪያችን ከ25ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀች ካትሊን ሎጋን e የተባለች ከአውስትራሊያ የመጣች እህት ነበረች። ሁላችንም ሙሉ ትኩረታችንን ቋንቋውን በመማር ላይ አደረግን። ደግሞም ሥልጠናው ላይ እንደተበረታታነው የተማርነውን ነገር ወዲያውኑ ለመጠቀም እንሞክር ነበር። እኔና ኢየን ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ስንወጣ አንድ አጭር መግቢያ በቃላችን ይዘን ነበር። ወደ ክልላችን ስንሄድ የመጀመሪያውን በር ማን እንደሚያንኳኳ ተነጋገርን። ኢየንን በዕድሜ ስለምበልጠው ታላቅነቴን ተጠቅሜ እሱ እንዲጀምር አደረግኩት። የቤቱ ባለቤት ግርማ ሞገስ ያለው ቻይናዊ ነበር። ሰውየው፣ ኢየን ቻይንኛ እና እንግሊዝኛ እየቀላቀለ ሲናገር በትዕግሥት አዳመጠው። ከዚያ ግን ጥርት ባለ እንግሊዝኛ ምን እንደፈለግን ሲጠይቀን በጣም ተደነቅን! የተወሰነ ከተወያየን በኋላ የውይይታችን መጨረሻ ላይ እንድንጸና አበረታታን። የተናገራቸው ደግነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ቤን ይል እንደነበረው ‘እስከ መጨረሻው መታገላችንን እንድንቀጥል’ ብርታት ሰጥተውናል።

 ክልላችን የዋና ከተማውን የታይፔን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍን ነበር። በወቅቱ በዚያ አካባቢ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ጥቂት ስለነበሩ ክልሉ ያልተነካ ነበር ሊባል ይችላል። እኔና ኢየን በዚህ ሳንበገር ወደ ሥራ ገባን። ያኔ በአብዛኛው በአንድ ወር ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጽሔቶችን እናበረክት ነበር። እርግጥ አንዳንዶቹ መጽሔቶቹን የሚወስዱት ማን እንደሆንን ለማወቅና ምን እንደምንል ለመረዳት ስለፈለጉ ብቻ ሳይሆን አይቀርም! ያም ሆኖ የእውነት ዘር ቅን በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ሥር እንደሚሰድ በመተማመን ይህን ዘር ለመዝራት የቻልነውን ሁሉ እናደርግ ነበር።

ከአዲሷ የዕድሜ ልክ ጓደኛዬ ያገኘሁት እርዳታ

በ1974 እኔና ወንኋ አገልግሎት ላይ ሆነን

 በዚያ ሳገለግል ወንኋ ከተባለች ታይዋናዊት እህት ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። ወንኋ እውነትን የምትወድና የአካባቢዋ ሰዎች ልክ እንደ እሷ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት የምትፈልግ ሰው ነች። በዚህም የተነሳ ብዙ ሚስዮናውያን የቋንቋ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ረድታለች፤ እኔንም ጨምሮ ማለት ነው። በዚህ ሂደት ይህችን ትጉ እህት የወደድኳት ሲሆን በ1974 ትዳር መሠረትን።

 ወንኋ ሚስዮናውያኑ በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ረድታለች። ለምሳሌ የታይዋናውያንን ባሕልና አስተሳሰብ እንድንድረዳ በማገዝ ቋንቋውን እንድንማር ረድታናለች። በተጨማሪም ክልላችን ውስጥ በአብዛኛው የሚገኙት ቡዲስቶችና ታኦይስቶች ስለነበሩ እነሱን ያገናዘበ መግቢያ እንድንዘጋጅ ታግዘናለች። በአገሪቱ የቀድሞ አባቶች አምልኮ ሰፊ ተቀባይነት የነበረው ከመሆኑም ሌላ አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አይደለም አንብበው አይተው እንኳ አያውቁም። ስለዚህ መግቢያችን በፈጣሪ ላይ ማለትም ስሙ ይሖዋ በመሆኑና እሱ እንዳለ እርግጠኛ መሆን በምንችልበት ምክንያት ላይ ያተኮረ እንዲሆን አደረግን። ለምሳሌ አንድ ገበሬ ወይም ዓሣ አጥማጅ “ምግባችንን የምንጠባበቀው ከሰማይ ነው” የሚል ሐሳብ ከተናገረ እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፦ “ለመሆኑ ምግባችንን ሁሉ የሚሰጠን አካል ማን ነው? ሁሉን ቻይ የሆነው፣ ሁሉን ነገር የፈጠረውና አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው አምላክ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይመስልህም?”

በ1975 ከወንኋ ጋር

 በጊዜ ሂደት ልፋታችን ፍሬ አስገኘ፤ የመንግሥቱ ዘር ቅን በሆኑ በርካታ ሰዎች ልብ ላይ ሥር መስደድ ጀመረ። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ተብትበው ከያዟቸው የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች ለመላቀቅ ይታገሉ ነበር። ሚስዮናውያኑና በአካባቢው ያሉ አስፋፊዎች ባደረጉላቸው ድጋፍ በትግሉ ማሸነፍና ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። (ዮሐንስ 8:32) ብዙ ወንድሞች ከጊዜ በኋላ በጉባኤያቸው ውስጥ ኃላፊነቶችን ተቀብለው መሥራት እንዲሁም በአገሪቱ ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ ወይም በቤቴል ማገልገልን ጨምሮ በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች መካፈል ጀምረዋል።

 ከ1976 ጀምሮ የመስክ ሚስዮናዊነቴን ሳላቆም በታይዋን ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የማገልገል መብት አገኘሁ። በ1981 እኔና ወንኋ ቤቴል እንድንገባ የተጋበዝን ሲሆን በቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ ማገልገሌን ቀጠልኩ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጀመርኩ አሁን 60 ዓመት አልፎኛል። ከእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ50 የሚበልጡትን ያሳለፍኩት በታይዋን ነው፤ ከውዷ ባለቤቴ ጋር ያገለገልኩበት ጊዜ ደግሞ ወደ 50 ዓመት ይጠጋል። የቀድሞ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጓደኛዬ ኢየን ብራውን በ2013 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ እዚሁ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቀጥሏል።

በ1997 በታይዋን ባለው ቢሮዬ ስሠራ

 እኔና ወንኋ በቤቴል ሥራ፣ በቻይንኛ ጉባኤ እንቅስቃሴዎችና በአገልግሎት ለመጠመድ ጥረት እናደርጋለን። ለእነዚህ ውድ መብቶች ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ገና ልጅ ሳለሁ እሱን በሙሉ ልቤ የማገልገል ፍላጎትና ኃይል ሰጥቶኛል፤ በስተርጅናችንም ለእኔና ለወንኋ እንዲህ ያለ ድጋፍ መስጠቱን ቀጥሏል።

a ልዩ አቅኚ የሚባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ ወዳለበት አካባቢ ተልኮ ለማገልገል ራሱን በፈቃደኝነት የሚያቀርብ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው።

b የቤነት ብሪክል የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1972 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ወጥቷል።

c እነዚህ መኪኖች የመንግሥቱን መልእክት እስከ ሩቅ ቦታ ድረስ ማሰማት የሚችሉ የድምፅ ማጉያዎች ከውጭ በኩል የተገጠሙላቸው ነበሩ።

d በዚህ አካባቢ ስለሚከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ ለማየት ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች መስበክ—አውስትራሊያ የተባለውን ቪዲዮ ተመልከት።

e የሃርቪ እና የካትሊን ሎጋን የሕይወት ታሪክ በጥር 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።