ኧርማ ቤንቲቮሊ | የሕይወት ታሪክ
‘የመልካም ስጦታ ሁሉ’ ምንጭ የሆነውን አምላክ ማገልገል
የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሉ እየተሰማ ነበር። እናቴ ታናሽ ወንድሜን አቅፋ በአቅራቢያችን ወዳለ የፍራፍሬ እርሻ ወሰደችንና ዛፎቹ ሥር ተደበቅን። በወቅቱ ገና ስድስት ዓመቴ ነበር።
የአየር ጥቃቱ ሲያቆም ከእናቴ ጋር ጓደኛዋን ለመፈለግ ሄድን። በጥቃቱ እንደሞተች ስናውቅ በጣም አዘንን። ከጥቂት ቀናት በኋላ ቀጣዩ የአየር ጥቃት ሲፈጸም አባቴ ብስክሌቱ ላይ ከፊት ለፊቱ አስቀመጠኝና በተቻለ ፍጥነት እየነዳ ከተማውን ለቆ ወጣ።
ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየታመሰች ነበር፤ ያ ጊዜ የትናንት ያህል ትዝ ይለኛል። በሕይወቴ ላይ ትልቁን አሻራ ያሳረፈው ግን ከልጅነቴ ጀምሮ ይሖዋን በሚያውቁና እሱን ከልባቸው በሚወዱ ሰዎች መከበቤ ነው።
ስጦታ የሆነው እውነት
በ1936 የክረምት ወቅት እኔ ከመወለዴ ከጥቂት ወራት በፊት አባቴ፣ ቪንቼንትሶ አርቱዚ ከተባለ ሰው ጋር የባቡር ሐዲዶችን ደህንነት የመከታተል ሥራ ይሠራ ነበር። በወቅቱ ቪንቼንትሶ ገና የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ከሐዲዶቹ ላይ በረዶ እየዛቁ በሚያነሱበት ጊዜ ቪንቼንትሶ የተማረውን ነገር ለአባቴ ይነግረው ነበር።
አባቴ፣ ቪንቼንትሶ የሚነግረው ነገር እውነት መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። አባቴን ጨምሮ ፋኤንዛ በተባለችው ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ጥቂት ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። የፋሺስት ጫና በነበረባቸው በእነዚያ ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች በይፋ መሰብሰብ የማይችሉ ከመሆኑም ሌላ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ይዞ ከተገኘ ሊታሰር ይችላል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ታስረው ነበር። ስለዚህ አባቴና ጓደኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እንዲሁም በእጃቸው ላይ ያሉ ጽሑፎችን ለማጥናት የሚገናኙት በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ ነጠል ብለው ያሉ ቤቶች ውስጥ ነበር። በተጨማሪም በየሳምንቱ ምሽት ላይ አባቴ ቤተሰባችንን አንድ ላይ ሰብስቦ መጽሐፍ ቅዱስን እናጠና ነበር።
ስጦታ የሆኑ ጥሩ ምሳሌዎች
በ1943 በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በመካፈላቸው ታስረው ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ ተለቀቁ። ከእነዚህ መካከል ማሪያ ፒትሳቶ የተባለች ነጠላ እህት ትገኝበታለች። በሰሜናዊ ጣሊያን ወዳለው ቤቷ ስትሄድ አንድ ምሽት እኛ ጋ አድራ ነበር። ማሪያ የጣሊያን ወንድሞችና እህቶች ጽሑፎችን እንዲያገኙ እንዲሁም በወቅቱ በጣሊያን የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት ይከታተል ከነበረው ከስዊዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር የመልእክት ልውውጥ እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ይህች እህት ስትታይ ደካማ ብትመስልም ጠንካራና ደፋር ሴት ነበረች። ከጦርነቱ በኋላ አልፎ አልፎ ወደ ፋኤንዛ ትመጣ የነበረ ሲሆን በመጣች ቁጥር አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን።
ሌላ የማልረሳት እህት፣ አልቢና ኩሚኔቲ ናት። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ ይህች እህት የምትኖረው ስብሰባ በምናደርግበት ሕንፃ ውስጥ ነበር። ከ1920ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በጣሊያን ኮልፖልተር (የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ) ሆና አገልግላለች። አልቢና ሥራው ገና አዲስ ሳለ ስለነበረው ሁኔታ ብዙ አስደናቂ ታሪኮችን አጫውታኛለች!
አልቢና ጽሑፎቻችንንና ሌሎች ታሪካዊ ዕቃዎችን ትሰበስብ ነበር። አንድ ቀን ከስብስቦቿ መሃል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ ይጠሩበት የነበረው ስም ነው) ያደርጉት የነበረ የመስቀልና የዘውድ ቅርጽ ያለበት ጌጥ አየሁ። በወቅቱ መስቀል አረማዊ አመጣጥ እንዳለው ስለተማርኩ፣ ባየሁት ነገር በመገረም ሳቅሁ። ከዚያም አልቢና መቼም የማልረሳውን አንድ ነገር ተናገረች። ዘካርያስ 4:10 ላይ ያለውን ሐሳብ በአእምሮዋ ይዛ “ሥራው በትንሹ የተጀመረበትን ቀን አትናቂ!” አለችኝ።
የተናገረችው ነገር ትልቅ ቁም ነገር አስተምሮኛል። የድሮዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነትን ሙሉ በሙሉ ባይረዱም ላከብራቸው ይገባል። በዚያ ላይ በጣሊያንኛ ማግኘት የሚቻለው ሁሉንም ጽሑፎች ስላልነበር ወንድሞች ማስተካከያ ከተደረገባቸው ትምህርቶች ጋር ለመተዋወቅ የተወሰነ ጊዜ ይወስድባቸው ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ጥረታቸውን ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት እኔም ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረኝ ይገባል።
አልቢና በዕድሜ ብዙ ብትበልጠኝም ከእሷ ጋር መነጋገር በጣም ያስደስተኝ ነበር። እሷ፣ ማሪያ እና ከባድ ፈተናዎችን ተቋቁመው ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ሌሎች ቀናተኛ እህቶች ለእኔ አርዓያ ሆነውልኛል። ከእነሱ ጋር ጊዜ የማሳለፍ አጋጣሚ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ።
ስጦታ የሆነው የቤቴል አገልግሎት
በ1955 የበጋ ወራት “ድል አድራጊው መንግሥት” በተባለው ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሮም አቀናሁ። እግረ መንገዴን ከተለያዩ አገሮች ከመጡ ልዑካን ጋር ቤቴልን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ‘አቤት! እዚህ ማገልገል ብችል እንዴት ጥሩ ነው!’ ብዬ አሰብኩ።
ታኅሣሥ 18, 1955 ተጠመቅኩ። ገና ተማሪ ብሆንም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ቆርጬ ነበር። በ1956 በጀኖአ ከተማ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ በቤቴል የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሰማሁ። ሆኖም የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ ሆኖ የመጣው ወንድም እህቶች እንደማይፈለጉ ተናገረ።
በኋላ ላይ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን የነበረውን ፕዬሮ ጋቲ a የተባለውን ወንድም ስለ ግቤ አማከርኩት። ግለት የነበረውና ቀናተኛ ሰባኪ የሆነው ይህ ወንድም “አንቺ ልዩ አቅኚ እንድትሆኚ ነው የድጋፍ ደብዳቤ የምጽፈው” አለኝ።
ከጊዜ በኋላ ከቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ደረሰኝ። አቅኚ እንድሆን እንደተሾምኩ የሚገልጽ ደብዳቤ ነበር የጠበቅኩት፤ ግን አልነበረም። ለቤቴል አገልግሎት እንዳመለክት የሚጋብዝ ደብዳቤ ነበር!
ጥር 1958 ቤቴል ገባሁ። በወቅቱ የቤቴል ቤተሰብ 12 ሰዎችን ብቻ ያቀፈ ነበር። የተመደብኩት በቅርንጫፍ ቢሮው የነበሩትን ሁለት ተርጓሚዎች እንዳግዝ ነው። ሥራው በጣም ብዙ ሲሆን እኔ ደግሞ በትርጉም ሥራ ምንም ልምድ አልነበረኝም። በይሖዋ እርዳታ ግን የተሰጠኝን ምድብ እየወደድኩት መጣሁ።
ሆኖም ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የትርጉም ሥራው በአዲስ መልክ ሲደራጅ እኔ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ወደ መስክ ተመደብኩ። በወቅቱ ቤቴልን እንደ ቤቴ አድርጌ መቁጠር ጀምሬ ስለነበር ለውጡ አስደነገጠኝ። በጊዜ ሂደት ግን አዲሱ ምድቤንም ከይሖዋ እንደተገኘ ሌላ ስጦታ አድርጌ መቁጠር ጀመርኩ።
ስጦታ የሆኑ ቀናተኛ የስብከት ባልደረቦች
መስከረም 1, 1959 ክሬሞና በተባለች ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። የአቅኚነት አገልግሎት ጓደኛዬ ከዴንማርክ የመጣች ዶረስ ማየር የተባለች እህት ናት። የምትበልጠኝ በጥቂት ዓመታት ብቻ ቢሆንም ብዙ ተሞክሮ ያላትና የማከብራት አቅኚ ነበረች። ዶረስ ደፋር፣ በቀላሉ የማትፈራና ቆራጥ ሰው ነች። ሁለታችንም በክልላችን ውስጥ ለመስበክ እነዚህ ባሕርያት ያስፈልጉን ነበር፤ ምክንያቱም በመላው ከተማ ውስጥ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ ነበርን።
ዶረስ ወደ ክሬሞና የሄደችው ከእኔ ቀድማ ስለነበር በአንድ የኪራይ አፓርታማ ውስጥ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት አድርጋ ነበር። እንቅስቃሴያችንን ለማስተዋል ጊዜ ያልወሰደባቸው የአካባቢው የካቶሊክ ቄሶች በጣም ስለተበሳጩ በስብከታቸው ላይ እኛን ማውገዝ ጀመሩ።
አንድ ቀን በአካባቢው ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ ተጠራን። ፖሊሶቹ ባያስሩንም የሌላ አገር ዜጋ የሆነችው ዶረስ ክሬሞናን ለቃ መውጣት እንዳለባት በግልጽ ነገሩን። በኋላም ዶረስ ወደ ዴንማርክ ተመልሳ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሏን ቀጠለች።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ብሩኒልደ ማርኪ የተባለች ሌላ ነጠላ እህት በክሬሞና እንድታገለግል ተመደበች። ብሩኒልደ ገርና ማራኪ ባሕርይ ያላት ሴት ነበረች፤ የስብከቱንም ሥራ ትወድ ነበር። ከእሷ ጋር ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ያስጀመርን ሲሆን አንዳንዶቹ ጥሩ እድገት አድርገዋል።
የስብከቱ ሥራ በክሬሞና በትንሹ በተጀመረበት ጊዜ በሥራው እንድካፈል አጋጣሚውን ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በአሁኑ ጊዜ በዚያ ከተማ አምስት ጉባኤዎች አሉ!
ያልጠበቅኩት አስደሳች ዜና
በክሬሞና ማገልገል ከጀመርኩ ገና ሁለት ዓመት ሳይሞላኝ ከቅርንጫፍ ቢሮው ስልክ ተደወለልኝ። ሐምሌ 1961 ከሚደረገው “በአንድነት ይሖዋን ማምለክ” የሚል ርዕስ ካለው የስድስት ቀን ትልቅ ስብሰባ ጋር በተያያዘ የሚከናወን ብዙ የትርጉም ሥራ ነበር። ስለዚህ ድጋሚ በቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ። ከደስታዬ የተነሳ ዘለልኩ! የካቲት 1, 1961 ወደ ቤቴል ተመለስኩ።
ለረጅም ሰዓታት እንሠራ የነበረ ቢሆንም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ ሥራ መጠመድ ልዩ መብት ነበር። ወራቱ በፍጥነት ነጉደው ስብሰባው የሚካሄድበት ጊዜ ደረሰ።
በስብሰባው ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ወደ ጣሊያንኛ እንደሚተረጎም የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። ‘ወደፊት ብዙ ሥራ ይኖራል ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ። ደግሞም አልተሳሳትኩም። የቤቴል ቆይታዬ ተራዘመልኝ። እንዲያውም ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ አሁንም በቤቴል እያገለገልኩ ነው!
ከይሖዋ ያገኘኋቸው ሌሎች ውድ ስጦታዎች
ከይሖዋ ያገኘሁት ሌላው ውድ ስጦታ ነጠላነቴ ነው። ስለማግባት አስቤ አላውቅም ማለቴ አይደለም። እንዲያውም የሆነ ወቅት ላይ ነጠላ ሆኖ ስለመኖር ሳስብ በጣም እጨነቅ ነበር። ስለዚህ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። እሱ ከማንም የበለጠ ያውቀኛል። በመሆኑም ለእኔ ከሁሉ የተሻለው ምርጫ የትኛው እንደሆነ እንዳስተውል እንዲረዳኝ ለመንኩት።
እንደ ማቴዎስ 19:11, 12 እንዲሁም 1 ቆሮንቶስ 7:8, 38 ያሉት ጥቅሶች ልዩ ትርጉም ይሰጡኝ ጀመር፤ ይሖዋ እውነታውን ግልጽ ስላደረገልኝና ውስጣዊ ሰላም ስለሰጠኝ አመሰገንኩት። በውሳኔዬ አንዴም ተቆጭቼ አላውቅም፤ ነጠላነቴን ለይሖዋ ምርጤን ለመስጠት መጠቀም በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ በትርጉም ክፍል ሥራ ላይ ብዙ ለውጦች ሲደረጉ አይቻለሁ፤ ምክንያቱም የይሖዋ ድርጅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ “የብሔራትን ወተት” ለሥራው ይጠቀማል። (ኢሳይያስ 60:16) እነዚህ ለውጦች የዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር አንድነት አጠናክረዋል። ለምሳሌ በ1985 ጣሊያንኛውና እንግሊዝኛው የመጠበቂያ ግንብ እትም እኩል መውጣት ጀመሩ። በዛሬው ጊዜ jw.org ላይ የተለያዩ ርዕሶችንና ቪዲዮዎችን ማግኘት የሚቻል ሲሆን አብዛኞቹ የሚወጡት ከእንግሊዝኛው እኩል ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ እንዲሆኑና መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ በግልጽ ማየት ይቻላል።
በሕይወቴ ውስጥ በብዙ መንገዶች የይሖዋን ልግስና አይቻለሁ። ልዩ አቅኚ ሆኜ ፍሬያማ አገልግሎት እንዳገለግል አጋጣሚውን ሰጥቶኛል። በቤቴል የማገልገል ምኞቴን አሳክቶልኛል፤ በዚያም የተለያየ ዕድሜና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችያለሁ። በተጨማሪም እናቴ በ68 ዓመቷ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ስትሆን የማየት ልዩ በረከት አግኝቻለሁ። በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ በሚነሱበት ጊዜ እሷንም ሆነ የቀሩትን ቤተሰቦቼን ለማየት እናፍቃለሁ።—ዮሐንስ 5:28, 29
ይሖዋ “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ያለው ቃል በሚፈጸምበት ጊዜ ለአገልጋዮቹ ምን ነገሮችን እንደሚያደርግላቸው ማየት ያጓጓኛል። (ራእይ 21:5) በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ነገር ቢኖር ይሖዋ ‘መልካም ስጦታን ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከትን ሁሉ’ በእኛ ላይ ማፍሰሱን ይቀጥላል።—ያዕቆብ 1:17
a የፕዬሮ ጋቲ የሕይወት ታሪክ በሐምሌ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-23 ላይ ወጥቷል።