በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ካሚላ ሮዛም | የሕይወት ታሪክ

ይሖዋን መታዘዝ የሕይወቴ ግብ ሆነ

ይሖዋን መታዘዝ የሕይወቴ ግብ ሆነ

 አያቶቼ ስለ ይሖዋ መንግሥት ተስፋዎች ያወቁት በ1906 ነው፤ ይህ ሲሆን ወንድ ልጃቸውን ዘጊ አናዳ በተባለ ተላላፊ የጉሮሮ በሽታ ካጡ ብዙም አልቆዩም ነበር። ሐኪማቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነበር፤ ያኔ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ነበር የሚጠሩት። ሐኪሙ ስለ ትንሣኤና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ሌሎች የሚያጽናኑ ተስፋዎች ነገራቸው። በዚህም የተነሳ አያቶቼ፣ እናቴና አክስቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ።

 እነዚህ ቤተሰቦቼ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በቅንዓት አገልግለዋል። እንዲያውም “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኢሊኖይ ግዛት ውስጥ በቺካጎ ከተማ በታየበት ወቅት ሴቶቹ አስተናጋጆች ሆነው አገልግለዋል። የሚያሳዝነው ግን ከእናቴ በቀር ሌሎቹ ይሖዋን ማገልገላቸውን አልቀጠሉም። እስከ 1930ዎቹ ዓመታት ድረስ ይሖዋን አብረው አምልከዋል፤ በጣም የሚቀራረብ ቤተሰብ ስለነበር ሁኔታው ለእናቴ ቀላል አልነበረም። እናቴ ለይሖዋ ያላት ታማኝነትና ታዛዥነት በእኔ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። የአባቴ ምሳሌም እንደዛው፤ እሱም ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነበር።

የቤተሰብ ፎቶ፣ 1948

 የተወለድኩት በ1927 ነው፤ ቤተሰባችን ውስጥ ካሉት ስድስት ልጆች እኔ የበኩር ነኝ። ደስ የሚለው፣ ሁላችንም በእውነት ጸንተናል። አባቴ አናጺ ነው፤ በቺካጎ ከተማ መውጫ ላይ ቆንጆ ቤት ውስጥ እንኖር ነበር። ትልቅ የአትክልት ጓሮ ነበረን፤ ዶሮና ዳክዬም እናረባ ነበር።

 ሥራ እወዳለሁ። ቤት ውስጥ የነበረኝ አንዱ ሥራ የቤተሰቡን የተቀደዱ ካልሲዎች መስፋት ነበር። አሁን አሁን፣ የተቀደደ ካልሲ የሚሰፋ ያለ አይመስለኝም፤ ያኔ ግን ካልሲ ተቀደደ ብሎ የሚጥል ሰው የለም። መርፌና ክር ይዘን ቀዳዳውን እንሰፋዋለን። በኋላ ላይ በሕይወቴ ውስጥ ብዙ የስፌት ሥራ ስለሠራሁ ገና ከልጅነቴ ይህን ክህሎት መማሬ በጣም ጠቅሞኛል።

ወላጆቼ የተዉት ግሩም ምሳሌ

 አባቴ፣ ቤተሰባችን ለመንፈሳዊ ነገሮች ሁሌም ትኩረት እንዲሰጥ ጥረት ያደርግ ነበር። ስለዚህ በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ በአገልግሎት አዘውትረን እንሳተፋለን፤ ደግሞም በየቀኑ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ እንወያያለን። ቅዳሜ ምሽት ደግሞ መጠበቂያ ግንብ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ እናጠናለን።

 አባቴ ለጎረቤቶቻችን ምሥክርነት እንዲሰጥ በማሰብ በኤሌክትሪክ የሚሠራ አንድ ማስታወቂያ ሳሎናችን መስኮት ላይ ገጠመ። ማስታወቂያውን የሠሩት ወንድሞች ናቸው፤ የሕዝብ ንግግሮችን ወይም ጽሑፎቻችንን ያስተዋውቃል። ማስታወቂያው ላይ ያለው መብራት ብልጭ ድርግም ስለሚል የአላፊ አግዳሚው ትኩረት መሳቡ አይቀርም። አባቴ ሌሎች ሁለት ማስታወቂያዎችም መኪናችን ላይ ገጥሞ ነበር።

በሸክላ ማጫወቻዎች በምንመሠክርበት ወቅት እናታችን አገልግሎት ይዛን ወጥታ

 አባቴ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ፣ ይሖዋ መታዘዝ ያለውን አስፈላጊነት ለእኛ ለልጆቹ አስተምሯል። እናቴም በምትችለው ሁሉ ታግዘው ነበር። የቤቱ የመጨረሻ ልጅ አምስት ዓመት ሲሆናት ደግሞ እናቴ በአቅኚነት ይሖዋን ማገልገል ጀመረች፤ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስም በአቅኚነት ቀጥላለች። እንደዚህ ዓይነት ወላጆች ስላሉኝ ዕድለኛ ነኝ።

 ያኔ ሕይወት አሁን እንዳለው አይደለም። ቴሌቪዥን አልነበረንም፤ ስለዚህ እኔና ታናናሾቼ መሬት ላይ ቁጭ እንልና ሬዲዮአችንን እናዳምጣለን፤ ደስ የሚሉ ተከታታይ ፕሮግራሞች ነበሩ። ከምንም በላይ ግን በጉጉት የምንጠብቀው፣ የይሖዋ ድርጅት በሬዲዮ የሚያስተላልፋቸውን መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ነበር።

ትላልቅ ስብሰባዎች፣ የሸክላ ማጫወቻዎችና ሳንድዊች ማስታወቂያዎች

 በይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ደስ ይለናል። በ1935 በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ስለ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማንነት ተነገረን፤ በራእይ 7:9, 14 ላይ የተጠቀሰው ይህ ቡድን ታላቁን መከራ በሕይወት አልፈው ምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎችን እንደሚያመለክት ተማርን። ከ1935 በፊት ሁለቱም ወላጆቼ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይካፈሉ ነበር። ከዚያ ስብሰባ በኋላ ግን መካፈሉን የቀጠለው አባቴ ብቻ ነው። እናቴ ተስፋዋ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንጂ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር መግዛት እንዳልሆነ ተረዳች።

 በ1941 ሴንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፤ በወቅቱ ለድርጅቱ አመራር ይሰጥ የነበረው ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ ልጆች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ መውጣቱን አበሰረ። ትዝ ይለኛል፣ ጭብጨባው ድምቅ ያለ ነበር። ያን ጊዜ 14 ዓመቴ ነበር፤ ከተጠመቅኩ አንድ ዓመት ገደማ ቢሆነኝ ነው። መጽሐፉ የሚሰጠው መድረክ ላይ ነበር፤ ከሌሎች ልጆች ጋር ተሰልፈን መጽሐፉን ለመቀበል ወደ መድረኩ ስንሄድ በደንብ ትዝ ይለኛል።

ከሎሬይን ጋር፣ 1944

 ያን ጊዜ የነበረው አገልግሎት አሁን ካለው ይለያል። በ1930ዎቹ ዓመታት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የሸክላ ማጫወቻዎች ተጠቅመን ለቤቱ ባለቤቶች የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች እንከፍትላቸው ነበር። አንድ በር ከማንኳኳታችን በፊት ሸክላውን አጠንጥነን መርፌውን ትክክለኛው ቦታ ላይ እናስቀምጠዋለን። የቤቱ ባለቤት ሲወጣ አጭር መግቢያ እንናገርና የአራት ደቂቃ ተኩሉን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እናስደምጠዋለን፤ ከዚያም ጽሑፍ እናበረክትለታለን። የአካባቢያችን ነዋሪዎች በአክብሮት ያዳምጡን ነበር። አመናጭቆ ያናገረን ሰው ትዝ አይለኝም። በ16 ዓመቴ አቅኚነት ስጀምር አባቴ የራሴን የሸክላ ማጫወቻ ሰጠኝ፤ በኩራት ነበር አገልግሎት ይዤው የምሄደው። የአገልግሎት ጓደኛዬም ሎሬይን የተባለች ደስ የምትል እህት ናት።

 ሌላኛው የምሥክርነት ዘዴ ደግሞ የማስታወቂያ ሰልፍ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይህን የምሥክርነት ዘዴ የምንጠራው “ሳንድዊች ማስታወቂያ ሰልፎች” ብለን ነበር፤ ምክንያቱም ማስታወቂያዎቹን ከፊትም ከኋላም ነበር የምናነግተው። ማስታወቂያዎቹ መፈክሮች ተጽፈውባቸው ነበር፤ ለምሳሌ “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” ወይም “አምላክንና ንጉሡን ክርስቶስን አገልግሉ” የሚሉት ነበሩ።

ማስታወቂያ ይዘን በምንመሠክርበት ወቅት ለፎቶ ቆመን

 በስብሰባዎቻችን ላይ ለተቃውሞ የሚያዘጋጅ ሐሳብ ይነገረን ነበር፤ ለእውነት ጥብቅና ለመቆም ምን ማለት እንዳለብንም እንማራለን። ደግሞም አልቀረም፣ ተቃውሞው መጣ። ለምሳሌ፣ ግርግር ወደሚበዛበት የንግድ አካባቢ ሄደን ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሔት ባበረከትንበት ወቅት ፖሊሶች መጥተው በመኪና ወደ ጣቢያ ወሰዱን። ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ተለቀቅን። ይህ የደረሰብን ይሖዋን በመታዘዛችን እንደሆነ ስለምናውቅ ተደሰትን።

ትዳር፣ ጊልያድ እና ወታደራዊ ምልመላ

እኔና ዩጂን በሠርጋችን ዕለት

 በኋላ ላይ ሎሬይን ሚኒያፖሊስ፣ ሚኒሶታ በተካሄደ የወረዳ ስብሰባ ላይ ያገኘችውን አንድ ወንድም አስተዋወቀችኝ፤ ዩጂን ሮዛም ይባላል። ዩጂን ያደገው ኪይ ዌስት፣ ፍሎሪዳ ውስጥ ነው። አሥረኛ ክፍል ሳለ በብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከትምህርት ቤት ተባረረ። ወዲያውኑ በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። አንድ ቀን፣ አብራው ከተማረች ልጅ ጋር በአጋጣሚ ተገናኘ። ዩጂን ጎበዝ ተማሪ ስለነበር ለምንድን ነው የተባረረው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ፈጥሮባት ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ ስለሰጣት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። እውነትን ተቀብላም ታማኝ እህታችን ሆነች።

ኪይ ዌስት ውስጥ፣ 1951

 እኔና ዩጂን በ1948 ተጋባን። የትዳር ሕይወታችንን ሀ ብለን የጀመርነው ኪይ ዌስት ውስጥ በአቅኚነት በማገልገል ነው። በኋላ ላይ በ18ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ላይ እንድንማር ተጋበዝን፤ የተመረቅነውም በ1952 መጀመሪያ ላይ ነው። አንደኛው የትምህርት ዓይነት ስፓንኛ ነበር፤ ስለዚህ ስፓንኛ በሚነገርበት አገር ውስጥ ሚስዮናዊ ሆነን እንደምንመደብ ጠብቀን ነበር። ሆኖም እንዳሰብነው አልሆነም። እኛ ጊልያድ በነበርንበት ወቅት የኮሪያ ጦርነት እየተፋፋመ ነበር፤ ዩጂንም ጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዲያገለግል ተመለመለ። ቀደም ሲል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሃይማኖታዊ አገልጋይ ነው በሚል ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ተደርጎ ስለነበር ይህ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም። አሁን ይህ የምልመላ ጥሪ ሲመጣ እዚያው ዩናይትድ ስቴትስ እንድንቆይ ተነገረን። በጣም ስለከፋኝ አለቀስኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ዩጂን ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ነህ ተባለ። ይህ ፈተና አንድ ትልቅ ነገር አስተምሮናል። አንደኛው በር ሲዘጋ ይሖዋ ሌላኛውን ሊከፍት ይችላል፤ ደግሞም እንደዚህ አድርጓል። ከእኛ የሚጠበቀው መታገሥ ብቻ ነው።

እኛ የነበርንበት የጊልያድ ትምህርት ቤት

የወረዳ ሥራ፣ በኋላም ወደ ካናዳ መሄድ

 ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቱሶን፣ አሪዞና ውስጥ በስፓንኛ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት ካገለገልን በኋላ በ1953 በወረዳ ሥራ ላይ ተመደብን። በኦሃዮ፣ በካሊፎርኒያ እና በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ አገልግለናል። በ1958 ካሊፎርኒያ እና ኦሪገን ውስጥ በአውራጃ ሥራ a ላይ ማገልገል ጀመርን። የምናርፈው ወንድሞች ቤት ነበር። ከዚያም በ1960 ወደ ካናዳ ሄድን፤ እዚያ ሳለን ዩጂን ለጉባኤ የበላይ ተመልካቾች በተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ አስተማሪ ነበር። እስከ 1988 ካናዳ ቆይተናል።

 በካናዳ ስላሳለፍነው ጊዜ ሳስብ አንድ የማልረሳው ታሪክ አለ። አንድ ቀን ከአንዲት እህት ጋር ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን ነበር። አንድ ቤት ስናንኳኳ አንድ ቤተሰብ አገኘን፤ መጀመሪያ ያነጋገርነው እናትየዋን ነበር። ጌል ትባላለች፤ ልጆቿ አያታቸውን በሞት በማጣታቸው እንዳዘኑ ነገረችን። “ለምንድን ነው የሞተው?” “የት ነው የሄደው?” እያሉ በጥያቄ ያፋጥጧታል። ጌል መልስ አልነበራትም። እኛም የሚያጽናኑ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እያነበብን መልሱን ነገርናት።

 እዚህ አካባቢ የመጣነው በወረዳ ጉብኝት ላይ ሆነን ስለነበር ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየት አልቻልንም። አብራኝ ታገለግል የነበረችው እህት ግን ጌልን ልትጠይቃት ተመልሳ ሄደች። ውጤቱ ምን የሆነ ይመስላችኋል? ጌል እውነትን ተቀበለች፤ ባለቤቷ ቢል እንዲሁም ክሪስቶፈር፣ ስቲቭ እና ፓትሪክ የተባሉት ሦስት ወንዶች ልጆቻቸውም እንደዛው። በአሁኑ ወቅት ክሪስ በካናዳ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። ስቲቭ ፓልም ኮስት፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ ነው። ፓትሪክ ደግሞ የታይላንድ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ነው። እኔና ዩጂን ከዚህ ቤተሰብ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተን ነበር። ይሖዋን እንዲያውቁ ትንሽም ቢሆን የራሴን ድርሻ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!

ከሆስፒታል ጉብኝት እስከ ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ

 ካናዳ ሳለን ዩጂን አስደሳችና ፍሬያማ የሆነ አዲስ የአገልግሎት በር ተከፈተለት። ይሖዋ የከፈተለት ይህ የአገልግሎት በር ምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

 ከዓመታት በፊት፣ ብዙ ሰዎች ‘ለሕክምናም ቢሆን ደም አንወስድም’ ስለሚለው አቋማችን የተሳሳተ ግንዛቤ ነበራቸው፤ ይህም ስለ እኛ ብዙ መጥፎ ወሬ እንዲዛመት አድርጓል። በመላው ካናዳ ያሉ ጋዜጦች፣ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ልጆቻቸው ደም እንዳይወስዱ በመከልከላቸው ለሞት እየዳረጓቸው ነው የሚሉ ዘገባዎችን ይዘው ይወጡ ነበር። ባለቤቴ እነዚህ የሐሰት ክሶች እንዲጠሩ በሚከናወነው ሥራ የመሳተፍ መብት አግኝቶ ነበር።

 በ1969 ቡፋሎ፣ ኒው ዮርክ ውስጥ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ለማካሄድ ሲታቀድ ዩጂን ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ሆኖ በአካባቢው ያሉ ትላልቅ ሆስፒታሎችን ጎብኝቶ ነበር፤ ከካናዳና ከመላው ዩናይትድ ስቴትስ 50,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ለስብሰባው እንደሚመጡም አብራሩላቸው። ሐኪሞቹ ከደም ጋር በተያያዘ ያለንን አቋም እንዲሁም ይህ አቋማችን ተገቢ የሆነበትን ምክንያት መረዳታቸው አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም በስብሰባው ላይ አስቸኳይ ሕክምና የሚጠይቅ ነገር ቢያጋጥም የምንሄደው ወደ እነሱ ነው። ወንድሞች ያለደም የሚሰጥ ሕክምናን በተመለከተ አመኔታ ካተረፉ መጽሔቶች ላይ የተወሰዱ ርዕሶችን ለሐኪሞቹ ሰጧቸው። ዩጂን እና ሌሎቹ ወንድሞች ሐኪሞቹ የሰጡት አዎንታዊ ምላሽ ብርታት ስለሆናቸው በካናዳ የሚገኙ ሆስፒታሎችን ራሳቸው ቅድሚያ ወስደው መጎብኘት ጀመሩ። ለየጉባኤው ሽማግሌዎችም አስቸኳይ ሕክምና የሚጠይቁ ሁኔታዎችን እንዴት አድርገው እንደሚይዙ ጥሩ ሥልጠና ሰጡ።

 እነዚህ ጥረቶች ቀስ በቀስ ፍሬ አፈሩ። እንዲያውም ጨርሶ ይሆናል ብለን ያልገመትነው አንድ ዝግጅት እንዲቋቋም ምክንያት ሆነዋል። ይህ ዝግጅት ምን ይሆን?

ስፌት ክፍል ውስጥ መሥራት ያስደስተኝ ነበር

 በ1980ዎቹ አጋማሽ ዩጂን ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ስልክ ተደወለለት፤ የደወለው ሚልተን ሄንሸል ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሐኪሞች መረጃ መስጠት እንዲቻል ታስቦ የተጀመረ አንድ ፕሮግራም ነበር፤ የበላይ አካሉ ይህ ፕሮግራም እንዲሰፋ ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም እኔና ዩጂን ወደ ብሩክሊን ተዛወርን፤ ከዚያም ጥር 1988 የበላይ አካሉ፣ የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት የሚል ዲፓርትመንት በዋናው መሥሪያ ቤት አቋቋመ። በኋላም ባለቤቴና ሌሎች ሁለት ወንድሞች ሴሚናር እንዲያካሂዱ ተመደቡ፤ በመጀመሪያ በዩናይትድ ስቴትስ ከዚያም በሌሎች አገሮች። ብዙም ሳይቆይ በየቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የሆስፒታል መረጃ ዲፓርትመንቶች፣ በተለያዩ ከተሞች ደግሞ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። ይሖዋ ባደረገው በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮችና ልጆቻቸው እንደተጠቀሙ ሳስብ ይገርመኛል። ከዩጂን ጋር ወደተለያዩ አገሮች ሄደን እሱ ሴሚናር ላይ ሲሆን ወይም ሆስፒታሎችን ሲጎበኝ እኔ እዚያው ባለው ቤቴል ውስጥ እሠራለሁ፤ ብዙውን ጊዜ የምሠራው ስፌት ክፍል ወይም ኩሽና ነው።

የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ሥልጠና፣ ጃፓን

ትልቁ ፈተናዬ

 በሕይወቴ ውስጥ ትልቁ ፈተና ያጋጠመኝ በ2006 ነው፤ ውዱ ባለቤቴ ዩጂን ሕይወቱ አለፈ። ወዳጄና አጋሬ የነበረው ባለቤቴ በጣም ይናፍቀኛል! ይህን ፈተና እንድቋቋም የረዳኝ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ። አንድ ነገር ብቻ አይደለም፤ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ፣ በመጸለይና አዘውትሬ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት አደርጋለሁ። የቤቴል ቤተሰብ በዕለት ጥቅሱ ላይ የሚያደርገውን ውይይት አዳምጣለሁ። ጥቅሱ የተወሰደበትን ምዕራፍም አነብባለሁ። ቤቴል ውስጥ በተመደብኩበት የስፌት ክፍልም ራሴን በሥራ አስጠምዳለሁ፤ ትልቅ መብት አድርጌ ነው የማየው። እንዲያውም ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በኒው ጄርሲ እና በኒው ዮርክ ለሚገኙት የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች መጋረጃ የመስፋት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። አሁን የማገለግለው ፊሽኪል ቤቴል ውስጥ ነው፤ እዚህ ልብስ እንደ ማስተካከል ያሉ አነስ ያሉ ሥራዎችን አከናውናለሁ። b

 ለእኔ በሕይወት ውስጥ ከምንም በላይ አስፈላጊው ነገር ይሖዋን መውደድ እንዲሁም እሱንና ድርጅቱን መታዘዝ ነው። (ዕብራውያን 13:17፤ 1 ዮሐንስ 5:3) እኔና ዩጂንም በሕይወታችን ውስጥ ለዚህ ቅድሚያ በመስጠታችን በጣም ደስተኛ ነኝ። ይሖዋም ይህን አይቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መጨረሻ የሌለው ሕይወት በመስጠት ወሮታችንን እንደሚከፍለን አልጠራጠርም፤ ከውዱ ባለቤቴ ጋር ዳግም እንደሚያገናኘኝም እርግጠኛ ነኝ!—ዮሐንስ 5:28, 29

a የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን እንደሚጎበኙት ሁሉ የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ሥራ ወረዳዎችን መጎብኘት ነበር፤ በተጨማሪም በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ይሰጡ ነበር።

b መጋቢት 2022 ይህ ርዕስ እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት የ94 ዓመቷ እህት ካሚላ ሮዛም ሕይወቷ አልፏል።