በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዴቪድ ሜዛ | የሕይወት ታሪክ

ከባድ ውጣ ውረዶችን ያለፈ ደስተኛ ቤተሰብ

ከባድ ውጣ ውረዶችን ያለፈ ደስተኛ ቤተሰብ

መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናሁና ምክሮቹን ሥራ ላይ ካዋልኩ በኋላ በአንድ ወቅት ፈጽሞ የማይቻል ይመስለኝ የነበረውን ነገር አገኘሁ፦ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት። እኔ፣ ባለቤቴና ሦስት ልጆቻችን በአንድነትና በሙሉ ልብ ይሖዋን እናገለግል ነበር።

ሆኖም ሚያዝያ 24, 2004 እንዳጋጠመን ያለ አሳዛኝ ክስተት ያጋጥመናል ብለን ፈጽሞ አስበን አናውቅም።

 ባለቤቴ ኬይ ሴት ልጃችንን ሎረንን ስትወልድ ጥሩ አባት መሆን ስለሚቻልበት መንገድ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ሁለተኛው ልጃችን ማይክል ሲወለድም እንደዚያው ነበርኩ። የወላጆቼ ትዳርም ቢሆን በጠብ የተሞላ ነበር፤ በመጨረሻም በፍቺ ተደመደመ። ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን ብፈልግም እንዲህ መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አላውቅም ነበር።

 ይባስ ብሎ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ የአልኮል መጠጥና የዕፅ ሱሰኛ ሆኜ ነበር። አዋቂ ከሆንኩ በኋላ ሕይወቴ በጣም ተበላሸ። ቁማርን ጨምሮ የነበሩብኝ ሱሶች የተለያዩ መጥፎ ውሳኔዎችን ወደ ማድረግ መርተውኛል። በኋላም ነገሩ እየተባባሰ ስለሄደ ኬይ ሁለት ልጆቻችንን ይዛ ትታኝ ሄደች። ይህ ቅስሜን ሰበረው።

 ምን ባደርግ ልትመለስ እንደምትችል ኬይን ጠየቅኳት። የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው ከግሎሪያ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን መወያየት ጀምራ ነበር። ስለዚህ ያቀረበችልኝ ቅድመ ሁኔታ ግልጽ ነበር፦ መጽሐፍ ቅዱስን አጥና አለችኝ። ይህ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ባላውቅም ኬይ እንድትመለስ ለማድረግ ስል ብቻ ከግሎሪያና ከባለቤቷ ከቢል ጋር ለመገናኘት ተስማማሁ።

ሕይወቴን የለወጠው ውይይት

 ቢልና ግሎሪያ ቤታችን ሲመጡ እርስ በርስ ባላቸው ቅርርብ በጣም ተደነቅኩ። የእኔ እኩያ የሆኑት ልጆቻቸው ሕይወታቸውን ትርጉም ባለው መንገድ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ሰማሁ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ጀመርኩ።

 በዚያን ዕለት ከቢልና ከግሎሪያ ጋር፣ ስለነበሩብኝ አንዳንድ ችግሮች ተነጋገርን። መጽሐፍ ቅዱስ ገላትያ 6:7 ላይ ምን እንደሚል አሳዩኝ፤ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” ‘እስከዛሬ ድረስ በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ሕይወቴን መርቼ ቢሆን ኖሮ ከብዙ ጣጣ እድን ነበር!’ ብዬ አሰብኩ።

ኬይ እና ዴቪድ

 በጊዜ ሂደት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋሌ ሕይወቴን በጣም እንዳሻሻለልኝ አስተዋልኩ። እኔና ኬይ ሲጋራ ማጨሳችንን አቆምን፤ ከነበሩብኝ ሌሎች ሱሶችም መላቀቅ ቻልኩ። በ1985 ሦስተኛው ልጃችን ዴቪድ ተወለደ። ዴቪ በሚለው የቁልምጫ ስሙ ነው የምንጠራው። እሱ ሲወለድ ጥሩ አባት ለመሆን ብቁ እንደሆንኩ ተሰማኝ።

በአንድነት ይሖዋን ማገልገል

 እኔና ኬይ ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱት ስናስተምር እኛም ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንደቻልን አስተውለናል። ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ! እንደተባለው ካሉ ጽሑፎች ብዙ ትምህርት አግኝተናል። በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤያችን ያሉ ቤተሰቦች ለእኛም ሆነ ለልጆቻችን ጥሩ አርዓያ ሆነውልናል።

ማይክል እና ባለቤቱ ዲያና

 በኋላ ሦስቱም ልጆቻችን አቅኚዎች ሆኑ። በ2004 መጀመሪያ አካባቢ ሎረን በስፓንኛ ጉባኤ ማገልገል ጀመረች። ማይክልና ባለቤቱ ዲያና በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ወደ ጉዋም ለመሄድ እየተዘጋጁ ነበር፤ ማይክል በቤቴል ሲያገለግል ቆይቶ ሊያገባ ሲል ነው የወጣው። ዴቪ ደግሞ 19 ዓመት የሞላው ሲሆን በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ማገልገል ከጀመረ ብዙም አልቆየም።

 እኔና ኬይ ልጆቻችን ባደረጉት ምርጫ በጣም ደስተኞች ነበርን። “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም” የሚለው 3 ዮሐንስ 4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውን ሆኖልን ነበር። በወቅቱ በአንድ የስልክ ጥሪ ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ይቀየራል ብለን አላሰብንም ነበር።

ልብ የሚሰብር ክስተት

 ሚያዝያ 24, 2004 እኔና ኬይ ራት ለመብላት ከሌሎች ሁለት ባልና ሚስት ጋር ወጣ አልን። ሬስቶራንቱ የሚገኘው ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ስለነበር ስድስታችንም በእኔ መኪና ተያይዘን ሄድን። ራት ከበላን በኋላ ሻይ ቡና ለማለት ሌሎቹን አንድ ካፌ አወረድኳቸውና መኪና ማቆሚያ ቦታ ለመፈለግ ሄድኩ። በዚህ መሃል ስልክ ተደወለልኝ። የደወለው አንድ ጓደኛዬ ነበር፤ በጣም እንደተጨነቀ ድምፁ ያስታውቃል።

 “አንድ አሳዛኝ ነገር ተከስቷል። ዴቪ አደጋ አጋጥሞታል” አለኝ።

 እኔም የሚሰጠኝን መልስ ለመስማት በመስጋት “በጣም ተጎዳ?” ብዬ ጠየቅኩት።

 መጀመሪያ ላይ ምንም ሊነግረኝ አልቻለም። ከዚያ ግን ፈራ ተባ እያለ ዴቪ እንደሞተ ነገረኝ።

 ስልኩን ከዘጋሁት በኋላ ብርታት እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ከዚያም ወደ ካፌው ገባሁና ስላመመኝ ወደ ቤት ብንሄድ የተሻለ እንደሆነ ነገርኳቸው። እነሱ ፊት ለኬይ ስለ ዴቪ ልነግራት አልፈለግኩም።

 ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል እስከ ቤት ድረስ ያደረግኩት ጉዞ በጣም ከባድ ነበር። ኬይ፣ ዴቪ በቅርቡ ሊጠይቀን እንደሚመጣ ለሌሎቹ በደስታ ታወራለች። ሌሎች ብዙ ሰዎች ግን ከኬይ አስቀድመው የልጃችንን ሞት ሰምተው ስለነበር ስልኬ በማጽናኛ መልእክቶች እየተጨናነቀ ነበር።

 አብረውን የነበሩትን ሰዎች ቤታቸው አድርሰን ወደ ቤታችን ተመለስን። ኬይ ልክ ስታየኝ የሆነ ከባድ ችግር እንደተፈጠረ ገባት። “ምን ሆነሃል?” ብላ ጠየቀችኝ። ቀጥሎ የምናገራቸው ቃላት የኬይን ልብ ምን ያህል እንደሚሰብሩት ገብቶኝ ነበር። ምክንያቱም ከሁለት ሰዓት ገደማ በፊት እኔም ያ ስልክ ሲደወልልኝ ምን ያህል ልቤ እንደተሰበረ አውቀዋለሁ።

የደረሰብንን ሐዘን መቋቋም

 እኔና ኬይ ከዚህ በፊትም ቢሆን ችግሮች አጋጥመውናል፤ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚንከባከብም እናውቃለን። (ኢሳይያስ 41:10, 13) ይሄኛው ግን እስካሁን ካጋጠሙን ችግሮች ሁሉ ፈጽሞ የተለየ ነው። በተደጋጋሚ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር፦ ‘እንደ ዴቪ ያለ ለይሖዋ ሕይወቱን ሁሉ የሰጠ ሰው እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥመዋል? ይሖዋ ጥበቃ ያላደረገለት ለምንድን ነው?’

 ልጆቻችንም በዴቪ ሞት በጣም ተጎድተዋል። ሎረን ለዴቪ እንደ ሁለተኛ እናቱ ነበረች። ስለዚህ የእሱን ሞት መቀበል በጣም ከብዷት ነበር። ማይክልም እንደዚያው። ማይክል ከቤት ከወጣ አምስት ዓመት ገደማ ቢሆነውም ትንሹ ወንድሙ ምን ያህል እንደጎለመሰ ማየቱ በጣም አስደስቶት ነበር።

 ሐዘኑ ከደረሰብን ጊዜ አንስቶ የጉባኤው ድጋፍ አልተለየንም። ለምሳሌ ኬይ በልጃችን ሞት የተነሳ ገና ድንጋጤ ውስጥ እያለች የጉባኤያችን ወንድሞችና እህቶች ቤታችን መጥተው አጽናንተውናል፤ ደግሞም ድጋፍ አድርገውልናል። (ምሳሌ 17:17) ያሳዩንን ፍቅር መቼም አልረሳውም!

 እኔና ኬይ ሐዘኑን ለመቋቋም ስንል የጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማዳችንን ይዘን ቀጠልን፤ በክርስቲያን ስብሰባዎችም ላይ አዘውትረን እንገኝ ነበር። እንዲህ ማድረጋችን ሐዘኑን አላስወገደልንም። ሆኖም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን እንድንቀጥል የሚረዱንን ነገሮች ማቋረጥ እንደሌለብን ተገንዝበን ነበር።—ፊልጵስዩስ 3:16

ሎረን እና ባለቤቷ ጀስቲን

 ማይክልና ዲያና እኛ ወዳለንበት አካባቢ ተዛውረው መኖር ጀመሩ፤ ሎረንም እኛ ወዳለንበት የእንግሊዝኛ ጉባኤ ተመለሰች። ለቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት አብረን መሆናችን ሁላችንም በተወሰነ መጠንም ቢሆን ከሐዘኑ እንድንጽናና ረድቶናል። ሎረን ትዳር ከመሠረተች በኋላ ደግሞ ባለቤቷ ጀስቲን ትልቅ ድጋፍ አድርጎልናል።

ከባድ ጉዞ

 ዴቪ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ሐዘናችንን ለመቋቋም ስንል የወሰድነው ሌላም እርምጃ ነበር። ይህን እርምጃ መውሰድ በጣም ከብዶን የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ በጣም ጠቅሞናል። እስቲ ይህን ታሪክ ደግሞ ኬይ ትንገራችሁ።

 “ባለቤቴ፣ ዴቪ እንደሞተ ሲነግረኝ የሆነ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደገባሁ ተሰማኝ። ለረጅም ጊዜም ከዚያ ጨለማ አልወጣሁም። በከባድ ሐዘን ከመዋጤ የተነሳ ምንም ነገር ማድረግ አልቻልኩም። ያለማቋረጥ አለቅስ ነበር። እውነት ለመናገር አንዳንድ ጊዜ በይሖዋም ሆነ በሕይወት ባሉ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ላይ እበሳጭ ነበር። ሙሉ በሙሉ ሚዛኔን እንደሳትኩ ተሰማኝ።

 “ወደ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ መሄድ ፈለግኩ። ዴቪ ከመሞቱ በፊት ባሉት ጊዜያት የኖረበትንና ይሖዋን ያገለገለበትን ቦታ የማየት፣ እዚያ የመገኘት ፍላጎት አደረብኝ። ግን ሐዘኑ ለእኔ ገና አዲስ ነበር። ያን ጉዞ ለማድረግ ምንም አቅም አልነበረኝም።

 “አንድ የቅርብ ጓደኛዬ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ያሉ የዴቪ ጓደኞችም በዴቪ ሞት በጣም እንዳዘኑና ቤተሰቡን ማግኘት እንደሚፈልጉ ነገረችኝ። እሷ የሰጠችኝ ማበረታቻ ኃይሌን አሰባስቤ ጉዞውን እንዳደርግ ረዳኝ።

 “በቤተሰብ ያደረግነው ያ ጉዞ በወቅቱ የሚያስፈልገንን ማጽናኛ ሰጥቶናል። ዴቪ ምን ያህል መንፈሳዊ ሰው እንደሆነ አወቅን። ዴቪ በሚያገለግልበት ጉባኤ ውስጥ ያለው ብቸኛው የጉባኤ ሽማግሌ ዴቪ ኃላፊነቶቹን በመወጣት ረገድ ሁሌም እምነት የሚጣልበት ሰው እንደነበር ነገረን።

 “ዴቪ በኖረበት አካባቢ መንገድ ላይ ስንሄድ ሰዎች ወደ እኛ እየመጡ ዴቪ ስላደረገላቸው መልካም ነገር ይነግሩን ነበር። ዴቪ ደግ እንደሆነ ድሮም አውቃለሁ። ይህ አጋጣሚ ግን ልጄ የኢየሱስን ፈለግ ምን ያህል በጥብቅ ለመከተል ጥረት እንዳደረገ ይበልጥ አረጋገጠልኝ።

ዴቪ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሲያገለግል

 “ከዴቪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም መካከል አንዱን አግኝተን ነበር። ሰውየው በአንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ነው የሚኖረው። የኑሮ ሁኔታው በጣም ዝቅተኛ ነው። ሆኖም የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች ዴቪ ሰውየውን ምንም ሳይጸየፈው በአክብሮት ይይዘው እንደነበር ነገሩን። ይህን ሳውቅ በልጄ በጣም ኮራሁ!

 “ይህ ጉዞ እስካሁን ካደረግኳቸው ጉዞዎች ሁሉ በጣም ከባዱ ነበር። ሆኖም ዴቪን ከሚያውቁትና ሐዘናችንን ከሚጋሩ ሰዎች ጋር መገናኘታችን በጣም አጽናናን። ጉዞው ለጊዜውም ቢሆን ሐዘናችን ቀለል እንዲልልን አድርጓል።”

የዴቪ ምሳሌ ሌሎችን አበረታቷል

 የጥር 8, 2005 ንቁ! መጽሔት ስለ ዴቪ ሞትና በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ስላከናወነው አገልግሎት የሚናገር ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። በወቅቱ ቤተሰባችን ይህ ርዕስ በሰዎች ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ ይሳድራል ብሎ አላሰበም። ለምሳሌ ግንቦት 2019 ላይ ኒክ የተባለ ወንድም የሚከተለውን ሐሳብ አካፍሎን ነበር፦

 “በ2004 መጨረሻ ላይ የኮሌጅ ተማሪ ነበርኩ። በወቅቱ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ግብ አልነበረኝም። ደስተኛም አልነበርኩም። ወደ ይሖዋ በመጸለይ የወጣትነት ጊዜዬን በተሻለ መንገድ እንድጠቀምበት እንዲረዳኝ ለምኜው ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ንቁ! መጽሔት ላይ የዴቪን ተሞክሮ አነበብኩ። ለጸሎቴ መልስ እንዳገኘሁ ተሰማኝ!

 “ከኮሌጅ ወጥቼ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ስፓንኛ የመማርና ወደ ውጭ አገር ሄዶ የማገልገል ግብም አወጣሁ። ከጊዜ በኋላ በኒካራጓ ማገልገል ጀመርኩ፤ ከባለቤቴም ጋር በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የመማር አጋጣሚ አገኘሁ። ሰዎች አቅኚ ለመሆን ያነሳሳኝ ምን እንደሆነ ሲጠይቁኝ የዴቪን ተሞክሮ እነግራቸዋለሁ።”

 በ2019 በቦነስ አይረስ፣ አርጀንቲና በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ በተገኘንበት ወቅትም ሌላ አስገራሚ ነገር አጋጠመን። እዚያ ሳለን ባረፍንበት ሆቴል ውስጥ እንግዶችን እንድትቀበል ከተመደበች አቢ የተባለች እህት ጋር ተዋወቅን። ይህች እህት ያሳየችን ደግነትና ፍቅር በጣም አስደነቀን። እኔም ሆንኩ ኬይ ልክ ስናያት ዴቪ ነው ትዝ ያለን።

የዴቪ ተሞክሮ አቢ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድትገባና ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ ተዛውራ እንድታገለግል አነሳስቷታል

 ወደ ሆቴል ክፍላችን ስንመለስ ስለ ዴቪ የሚናገረውን የንቁ! መጽሔት ሊንክ ለአቢ ላክንላት። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልስ ጻፈችልን። ልታነጋግረን በጣም ፈልጋ ነበር። ስለዚህ የሆቴሉ እንግዳ መቀበያ ጋ ተገናኘን። ከዚያም አቢ መስከረም 2011 አቅኚነት እንድትጀምርና ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ ሄዳ እንድታገለግል ያነሳሳት የዴቪ ተሞክሮ እንደሆነ እንባ እየተናነቃት ነገረችን። “በአገልግሎት ክልሌ ላይ አስቸጋሪ ነገር ባጋጠመኝ ቁጥር ይህን ርዕስ ደግሜ አነበዋለሁ” አለችን። የሚገርመው የመጽሔቱንም ቅጂ ይዛ ነበር!

 እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች የአንድ ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አባል እንደሆንን በግልጽ ያሳያሉ። በዚህ ዓለም ላይ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ካለው አንድነት ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ነገር የለም!

 እኔና ኬይ፣ ዴቪ በሌሎች ላይ ስላሳደረው በጎ ተጽዕኖ ስናስብ በጣም እንጽናናለን። እንደ እውነቱ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት ምርጣቸውን እየሰጡ ያሉ ወጣቶቻችን በሙሉ በሌሎች ላይ እንዲህ ያለ በጎ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው። ምናልባትም ሳይታወቃቸው የእነሱን ቅንዓት የሚመለከቱ ሰዎችን ሕይወት እየነኩ ነው። መልካም ምሳሌነታቸው ሌሎች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ያነሳሳል።

“በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው”

 ኢየሱስ ሉቃስ 20:37 ላይ ይሖዋ ራሱን “የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ” ብሎ እንደጠራ ተናግሯል። ይሖዋ የእነሱ አምላክ እንደሆነ የተናገረው በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አሁንም የእነሱ አምላክ እንደሆነ ተናግሯል! ለምን? ቁጥር 38 ላይ ኢየሱስ “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው” በማለት ነግሮናል።

 አዎ፣ በይሖዋ ፊት ታማኝ አገልጋዮቹ ሁሉ ሕያው ናቸው። ይህም እነሱን ለማስነሳት ምን ያህል እንደሚጓጓ ያሳየናል! (ኢዮብ 14:15፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ይሖዋ ስለ ዴቪም ሆነ በሞት ስላንቀላፉት ሌሎች አገልጋዮቹ እንዲህ እንደሚሰማው እርግጠኛ ነኝ።

 ዴቪን ድጋሚ ለማየት በጣም እጓጓለሁ፤ ግን ከዚያም በላይ የሚያጓጓኝ ነገር አለ። ይህም ኬይና ዴቪ ሲገናኙ ማየት ነው። ማንም ሰው ይህን ያህል በሐዘን ሲደቆስ አይቼ አላውቅም። ሉቃስ 7:15 ለእኔ ልዩ ትርጉም ያለው ጥቅስ ነው። ጥቅሱ “የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት” ይላል።

 መስከረም 2005 እኔም እንደ ኬይ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከባለቤቴ፣ ከልጆቻችንና ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር በአቅኚነት ማገልገል ልዩ መብት ነው። እንደ ቤተሰብ አንድ ሆነን በመደጋገፍ የምንወደውን ዴቪን ዳግመኛ የምናገኝበትን አዲሱን ዓለም በተስፋ እንጠባበቃለን።