ዶሪና ካፓሬሊ | የሕይወት ታሪክ
ዓይናፋር ነኝ፤ ያሳለፍኩትን ሕይወት ግን ድገሚው ብባል ዓይኔን አላሽም!
ከድሮም ጀምሮ በጣም ዓይናፋር ነኝ። ይሖዋን በማገልገል ያከናወንኳቸውን አንዳንድ አስደናቂ ነገሮች ሳስብ ‘እኔ ነኝ ወይስ ሌላ ሰው’ ብዬ የምገረመው ለዚህ ነው።
የተወለድኩት በ1934 ፔስካራ ውስጥ ነው፤ ፔስካራ በማዕከላዊ ምሥራቅ ጣሊያን በኤድሪያቲክ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ቤት ውስጥ አራት እህትማማቾች ነው ያለነው፤ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ። አባታችን ስም ያወጣልን ከ“A” ጀምሮ በፊደል ቅደም ተከተል ነው፤ የእኔ ስም በ“D” የሚጀምረው ለዚህ ነው።
አባቴ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መማር ደስ ይለዋል። ሐምሌ 1943 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ፤ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት የጀመረ ሊቤራቶ ሪቺ የተባለ አንድ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረው በኋላ አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ አዋሰው። ብዙም ሳይቆይ አባቴ ስለተማረው ነገር ለሌሎች በቅንዓት መስበክ ጀመረ። እናቴም እውነትን ተቀበለች። ማንበብና መጻፍ ባትችልም በቃሏ የምታስታውሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እየጠቀሰች ስለተማረችው አስደናቂ ተስፋ ለሌሎች መናገር ጀመረች።
ትንሿ ቤታችን እንግዳ የማይጠፋባት ሆነች። የጉባኤ ስብሰባዎች የሚደረጉት ቤታችን ነበር። ያሉን መኝታ ክፍሎች ሁለት ብቻ ቢሆኑም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና አቅኚዎች ሲመጡ እናስተናግድ ነበር።
ሁለቱ ታላላቅ እህቶቼ ለመጽሐፍ ቅዱስ ብዙም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ በኋላም አግብተው ከቤት ወጡ። እኔና እህቴ ቼሲራ ግን አባታችን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ ማዳመጥ ደስ ይለን ነበር። ትንሿን ቡድናችንን ለመጎብኘት የሚመጡ ወንድሞች የሚሰጡትን ሞቅ ያለ ንግግርም በጉጉት ነበር የምናዳምጠው።
ከአባቴና ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር ብዙ ጊዜ አገልግሎት እወጣለሁ፤ ግን እንደ ምንም ብዬ ራሴን አደፋፍሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ያናገርኩት ከወራት በኋላ ነው። ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር እያደገ ስለሄደ ሐምሌ 1950 ተጠመቅኩ። አንድ ወንድም የጥምቀት ንግግሩን ቤታችን ከሰጠ በኋላ ወደ ባሕር ወርደን ተጠመቅኩ። በቀጣዩ ዓመት፣ ልዩ አቅኚ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት እኛ አካባቢ እንዲያገለግሉ ተመደቡ፤ እኔም አብሬያቸው አገልግሎት መውጣት ጀመርኩ። አብሬያቸው ባገለገልኩ ቁጥር ይበልጥ እየቀለለኝ መጣ። ለዚህ ልዩ የአገልግሎት መብት ያለኝ ፍቅርም እየጨመረ ሄደ።
ሕይወቴን የቀየረ ውሳኔ
የመጀመሪያው የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን ፕዬሮ ጋቲ a ነው። አቅኚ እንድሆን አበረታታኝ፤ እንዲያውም የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ስለ መዛወር እንዳስብበት ጠየቀኝ፤ ይህ ፈጽሞ አስቤው የማላውቀው ነገር ነበር። በእኛ አካባቢ ሴት ልጆች ትዳር እስካልመሠረቱ ድረስ ከቤት መውጣታቸው የተለመደ አልነበረም። ስለዚህ መጋቢት 1952 እዚያው ወላጆቼ ቤት እያለሁ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ይህ ውሳኔ ሕይወቴን ምን ያህል እንደሚቀይረው የተረዳሁት በኋላ ላይ ነው።
በዚያው ጊዜ አካባቢ፣ አና የተባለች አንዲት የምናውቃት ወጣት እህት አቅኚነት መጀመር ፈለገች። አብረን ማገልገል እንድንችል ከእኛ ጋር መኖር ጀመረች። በ1954 እኔና አና ፔሩጃ ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተመደብን፤ ፔሩጃ እኛ ካለንበት 250 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት፤ በዚያ ላይ፣ በዚያች ከተማ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም።
ይህ ለእኔ እንደ ጀብዱ የሚቆጠር ነገር ነበር። ገና 20 ዓመቴ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ወላጆቼ ለትላልቅ ስብሰባዎች ይዘውኝ ሲሄዱ ካልሆነ በቀር ከከተማ ወጥቼ አላውቅም። ስለዚህ ዓለምን ያቋረጥኩ ያህል ነበር የተሰማኝ! እኔና አና ብቻችንን የመኖራችን ጉዳይ አባቴን ስላሳሰበው ቤት ሊያፈላልገን አብሮን መጣ። የስብሰባ አዳራሽም አድርገን ልንጠቀምበት የምንችል አንድ ክፍል ተከራየን። እርግጥ፣ ለተወሰነ ጊዜ ስብሰባ ላይ የምንገኘው እኔና እሷ ብቻ ነበርን። በፔሩጃና በአቅራቢያዋ ባሉ መንደሮችና ከተሞች ያሳለፍነው የስብከት ጊዜ ግን አስደሳች ነበር፤ ጥረታችንም ፍሬ ማፍራት ጀመረ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ፣ ወደ ፔሩጃ ተዛውሮ የመጣ አንድ ወንድም ስብሰባዎች ይመራልን ጀመር። በ1957 ሌላ ከተማ ሄደን እንድናገለግል ስንመደብ በዚያ አንድ ትንሽ ጉባኤ ተቋቁሞ ነበር።
ቀጥሎ የተመደብንበት ከተማ፣ በማዕከላዊ ጣሊያን የምትገኝ ተርኒ የተባለች ትንሽ ከተማ ነች። ተርኒ ውስጥ ለመስበክ ጓጉተን ነበር፤ ምክንያቱም በዚያ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ። ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነበር ማለት ግን አይደለም። የፋሺስት አገዛዝ በ1943 ቢያበቃም የይሖዋ ምሥክሮች እንዳይሰብኩ የሚከለክሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ነበሩ፤ እነዚህ ባለሥልጣናት ‘ፈቃድ ከሌላችሁ ከቤት ወደ ቤት እየሄዳችሁ መስበክ አትችሉም’ ይሉን ነበር።
ፖሊሶች የሚከታተሉን ጊዜ ነበር። አንዳንዴ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለን ለማምለጥ እንሞክር ነበር፤ ግን ያላመለጥንባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ሁለት ጊዜ በፖሊስ ተይዣለሁ። በአንደኛው አጋጣሚ ላይ፣ ከአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር እያገለገልኩ ነበር። ፖሊሶቹ ያዙንና ወደ ጣቢያ ወሰዱን፤ ‘ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራችሁ እየሰበካችሁ ነው’ ብለው የገንዘብ መቀጮ እንድንከፍል አዘዙን። የጣስነው ሕግ ስለሌለ መቀጮውን ለመክፈል ፈቃደኛ እንዳልሆንን ነገርናቸው። ከመፍራቴ የተነሳ ልቤ ድው ድው ይል ነበር! ያን ዕለት ብቻዬን ባለመሆኔ ይሖዋን አመሰገንኩት። በኢሳይያስ 41:13 ላይ የሚገኘውን የሚያጽናና ሐሳብ አስታወስኩ፤ ይሖዋ “አትፍራ። እረዳሃለሁ” ብሏል። በኋላ ላይ ለቀቁን፤ ጉዳያችንም በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ፤ ደስ የሚለው፣ ዳኛው በነፃ አሰናበቱን። ለሁለተኛ ጊዜ በፖሊስ የተያዝኩት ይህ ከሆነ ከስድስት ወራት በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ ግን ብቻዬን ነበርኩ። ደስ የሚለው፣ በዚህ ጊዜም ዳኛው በነፃ አሰናበቱኝ።
ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችሉ ተጨማሪ አጋጣሚዎች
በ1954 በደቡባዊ ጣሊያን በምትገኘው በኔፕልስ የተደረገውን ትልቅ ስብሰባ ፈጽሞ አልረሳውም። ወደ መሰብሰቢያ ቦታው እንደደረስኩ በጽዳት ሥራ ለመካፈል ራሴን አቀረብኩ፤ መድረኩ አካባቢ እንዳጸዳ ተመደብኩ። እያጸዳሁ ሳለ፣ አንድ መልከ መልካም ወጣት አስተናጋጅ አየሁ፤ ይህ ወጣት ሊቢያ ውስጥ የሚያገለግል አንቶኒዮ ካፓሬሊ የተባለ አቅኚ ነው። ቤተሰቦቹ ከጣሊያን ወደ ሊቢያ የሄዱት በ1930ዎቹ መጨረሻ ነበር።
አንቶኒዮ ደከመኝ የማያውቅና ደፋር ክርስቲያን ነው። ሊቢያ ውስጥ ለሚኖሩ ጣሊያናውያን ለመስበክ የሊቢያን በረሃ በሞተር ሳይክል ያቋርጥ ነበር። አልፎ አልፎ እንጻጻፍ ጀመር። በ1959 መጀመሪያ ላይ ግን ወደ ጣሊያን ተመለሰ። ለጥቂት ወራት ሮም በሚገኘው ቤቴል አገለገለ፤ ከዚያም በማዕከላዊ ጣሊያን በምትገኘው በቪቴርቦ ልዩ አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። እየተቀራረብን ሄድንና መስከረም 29, 1959 ተጋባን። ቪቴርቦ ውስጥ አብሬው ማገልገል ጀመርኩ።
የምንኖርበትና ስብሰባ የምናደርግበት ቤት ያስፈልገን ነበር። በኋላም መሬት ላይ ያለ አንድ ክፍል ተከራየን፤ ክፍሉ እንደ ሱቅ ነገር ሲሆን ከኋላው ትንሽዬ መጸዳጃ ቤት አለው። አልጋችንን አንዱ ጥግ ላይ አስቀመጥነውና መከለያ አደረግንለት። ስለዚህ እሱ እንደ መኝታ ክፍላችን ሆነ። የቀረውን ቦታ ደግሞ እንደ ሁኔታው ሳሎን ወይም የስብሰባ አዳራሽ አድርገን ተጠቀምንበት። ቤቱ ምቹ አልነበረም፤ ብቻሽን ኑሪበት ብትሉኝ የምመርጠው ዓይነት አይደለም። አንቶኒዮ አጠገቤ ስላለ ግን ብዙም ቅር አላለኝም።
በ1961 አንቶኒዮ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። በመጀመሪያ ግን፣ ያን ጊዜ የጉባኤ አገልጋዮች ለሚባሉት ወይም ለበላይ ተመልካቾች የተዘጋጀውን የአንድ ወር ሥልጠና መውሰድ ነበረበት። ስለዚህ ለአንድ ወር ሊለየኝ ግድ ሆነ ማለት ነው። እውነቱን ለመናገር፣ መጀመሪያ ላይ ከፍቶኝ ነበር፤ በተለይ ማታ ላይ እዚያች ክፍል ውስጥ ብቻዬን ስሆን ይጨንቀኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ አንቶኒዮን እየተጠቀመበት እንደሆነ በማወቄ ደስተኛ ነበርኩ። ራሴን በሥራ ለማስጠመድ ሞከርኩ፤ ስለዚህ ጊዜው ሳላስበው አለፈ።
የወረዳ ሥራ ብዙ መጓዝ ይጠይቃል። በሰሜናዊ ጣሊያን ከሚገኘው ከቬኔቶ በስተ ደቡብ እስካለችው እስከ ሲሲሊ ተጉዘናል። መጀመሪያ ላይ መኪና ስላልነበረን የሕዝብ መጓጓዣ ነበር የምንጠቀመው። በገጠራማው የሲሲሊ ክፍል ስንጓዝ ያጋጠመን አንድ የማልረሳው ገጠመኝ አለኝ። የሚያንገጫግጭ መንገድ ላይ በአውቶብስ ስንጓዝ ከቆየን በኋላ ፌርማታው ጋ ደረስን፤ ታዲያ ወንድሞች ምን ይዘው ቢቀበሉን ጥሩ ነው? ሻንጣችንን የሚሸከም አህያ ይዘው መጥተው ነበር። አንቶኒዮ ሙሉ ልብስና ከረባት ግጥም አድርጎ ለብሷል፤ እኔም የለበስኩት የስብሰባ ልብስ ነበር። እንደዚያ ዘንጠን፣ ቦርሳችንን እና የጽሕፈት መሣሪያውን አህያ ላይ ጭነን ከጎን ከጎኑ ስንሄድ እንግዲህ ይታያችሁ፤ ላየን ሰው በጣም ነው የሚያስቀው!
ወንድሞች በጣም ለጋሶች ናቸው፤ ያላቸውን ትንሽ ነገር እንኳ ለመስጠት አይሰስቱም። አንዳንዶቹ ቤቶች መጸዳጃ ቤትም ሆነ የቧንቧ ውኃ አልነበራቸውም። በአንድ ወቅት እንደ አጋጣሚ፣ ለበርካታ ዓመታት ሰው ያልኖረበት ቤት ውስጥ አረፍን። ሌሊት ላይ ዝም ብዬ ስገላበጥ አንቶኒዮ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። አንሶላውን ብድግ አድርገን ስናይ በጣም የሚያስደነግጥ ነገር ተመለከትን፤ ፍራሹ በነፍሳት ተወሮ ነበር! እንግዲህ በዚያ ውድቅት ሌሊት ተነስተን ምን ልናደርግ እንችላለን? ነፍሳቱን የቻልነውን ያህል ካራገፍን በኋላ ተመልሰን ለመተኛት ሞከርን።
የሚገርመው ግን፣ ለእኔ በጣም ተፈታታኝ የሆነብኝ እነዚህ ምቾት የሚነሱ ነገሮች አይደሉም። ትልቁ ፈተናዬ ዓይናፋርነቴ ነው። አንድን ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንጎበኝ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር መግባባት በጣም ይቸግረኛል። ነገር ግን እህቶችን ማበረታታትና ማገዝ እፈልግ ስለነበር የተለየ ጥረት አደረግኩ። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ፣ ሁሌም በሳምንቱ መጨረሻ የምንለያየው እንደ ቤተሰብ ሆነን ነው። ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ማገልገል እንዲሁም የእነሱን ልግስና፣ ታማኝነትና ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር ማየት ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል።
በወረዳና በአውራጃ ሥራ b ለጥቂት ዓመታት ከቆየን በኋላ በ1977 ሮም ወደሚገኘው ቤቴል ተጠራን፤ እዚያ የተጠራነው በ1978 ለሚደረገው “ድል አድራጊ እምነት” ለተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የሚደረገውን ዝግጅት እንድናግዝ ነው። ከጥቂት ወራት በኋላ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆንን። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ አንቶኒዮ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ እንዲያገለግል ተሾመ።
የቤቴልን ሕይወት መልመድ ነበረብኝ፤ አሁንም ቢሆን ነፃነት እንዳይሰማኝ ትልቅ ፈተና የሆነብኝ ዓይናፋርነቴ ነው። ሆኖም የይሖዋ በረከትና የሌሎች ቤቴላውያን እርዳታ ስላልተለየኝ ቤቴልን እንደ ቤቴ አድርጌ መመልከት ቻልኩ።
አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ
በቀጣዮቹ ዓመታት፣ ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ገጠመን፤ የጤና ችግር። በ1984 አንቶኒዮ የልብ ቀዶ ሕክምና አደረገ፤ ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ሌሎች የጤና እክሎችም ገጠሙት። ከዚያም በ1999 ካንሰር እንዳለበት ተነገረው። አንቶኒዮ ደከመኝን የማያውቅ ሰው ነበር፤ ለዚያ አስከፊ በሽታ ግን እጅ ሰጠ። በሽታው እያዳከመው ሲሄድ ማየት ልቤን ሰብሮት ነበር። ይሖዋ ውዱን ባለቤቴን ለመንከባከብ የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠኝ አጥብቄ ጸለይኩ። ደግሞም የመዝሙር መጽሐፍን ብዙ ጊዜ አነብ ነበር። ጭንቅ ሲለኝ ያረጋጋኝ እነዚህን ነገሮች ማድረጌ ነው። መጋቢት 18, 1999 አንቶኒዮ ሕይወቱ አለፈ። በትዳር ሕይወት 40 ዓመታት ገደማ አሳልፈናል።
የሚገርመው ነገር፣ ሐዘን ሲደርስብህ በሰዎች መካከል ሆነህም እንኳ ብቸኝነት ይሰማሃል። በእርግጥ፣ አብረውኝ የሚያገለግሉ ቤቴላውያንና በወረዳ ሥራ የተዋወቅናቸው ወንድሞችና እህቶች እኔን ለማጽናናት ያላደረጉት ነገር የለም። ያም ቢሆን ባለቤቴን ማጣቴ ልቤን አቁስሎት ነበር፤ በተለይ ማታ ላይ ወደ ክፍሌ ተመልሼ ብቻዬን ስሆን ልቤ በጣም ይረበሻል። ጸሎትና ጥናት በጣም ረድተውኛል፤ ጊዜው ሲያልፍም ቁስሌ ቀስ በቀስ እየሻረ ሄደ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ከአንቶኒዮ ጋር ያሳለፍናቸውን ነገሮች እያስታወስኩ መደሰት ቻልኩ። ከእሱ ጋር ያሳለፍነው ሕይወት አሁንም ጥሩ ትዝታዬ ነው፤ አንቶኒዮ በይሖዋ መታሰቢያ ውስጥ እንዳለና ከሞት ተነስቶ እንደገና እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ።
ቤቴል ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ፤ አሁን የምሠራው ልብስ ስፌት ክፍል ውስጥ ነው። የማከናውነው ሥራ ሰፊ የሆነውን የቤቴል ቤተሰብ እንደሚጠቅም ማወቄ በጣም ያስደስተኛል። በአገልግሎትም ራሴን ለማስጠመድ እሞክራለሁ። እርግጥ ነው፣ የቀድሞውን ያህል ማድረግ አልችልም፤ ያ የወጣትነት ፍቅሬ፣ ትንሽ ልጅ እያለሁ ለአገልግሎት የነበረኝ አድናቆት ግን አሁንም አለ። የመንግሥቱን ምሥራች ማወጅ በጣም ያስደስተኛል። ወጣቶች አቅኚ እንዲሆኑ የማበረታታው ለዚህ ነው። አቅኚነት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ በራሴ ሕይወት አይቻለሁ።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን 70 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ በጣም እንደረዳኝና እንደባረከኝ ይሰማኛል። አሁንም ቢሆን ዓይናፋር ነኝ፤ በይሖዋ አገልግሎት ያደረግኳቸውን ነገሮች ሳስብ ‘በይሖዋ እርዳታ ባይሆን ኖሮ አልችለውም ነበር’ እላለሁ። በአገልግሎት ያላየሁት ቦታ የለም፤ ብዙ አስደሳችና አስደናቂ ጊዜያት አሳልፌያለሁ፤ በሕይወቴ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ካሳደሩ ብዙ ሰዎች ጋር ተዋውቄያለሁ። ያሳለፍሽውን ሕይወት ትደግሚዋለሽ ወይ ብባል ዓይኔን አላሽም!
a የፕዬሮ ጋቲ የሕይወት ታሪክ ሐምሌ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል፤ “ሞትን እፈራ ነበር—አሁን ግን ‘ሕይወት እንደሚትረፈረፍልኝ’ ተስፋ አለኝ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b የአውራጃ የበላይ ተመልካች በአንድ አውራጃ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎችን የሚጎበኝ የበላይ ተመልካች ነው።