በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጄ ካምቤል | የሕይወት ታሪክ

ከአፈር ተነስቶ ከፍ ወዳሉ ቦታዎች መድረስ

ከአፈር ተነስቶ ከፍ ወዳሉ ቦታዎች መድረስ

 ልጅ ሳለሁ በጣም ዓይናፋር ነበርኩ። ከቤት ባልወጣና ከሰዎች ጋር ባልገናኝ እመርጣለሁ፤ እንደማልረባ ይሰማኝ ነበር። ከቤት ስወጣም ከሰዎች ጋር ብዙም አልነጋገርም ነበር፤ ሰዎች በአክብሮት እንደማይዙኝ ይሰማኛል። እስቲ ታሪኬን ልንገራችሁ።

 ጊዜው ነሐሴ 1967 ሲሆን በወቅቱ የ18 ወር ሕፃን ነበርኩ፤ አንድ ቀን፣ ዕለቱን በሰላም ከዋልኩ በኋላ ኃይለኛ ትኩሳት ጀመረኝ። በቀጣዩ ቀን ስነሳ እግሮቼ ከዱኝ። በምኖርበት ፍሪታውን፣ ሴራ ሊዮን ባለ ሆስፒታል በተደረገልኝ ምርመራ ፖሊዮ የተባለ በሽታ እንደያዘኝ ታወቀ፤ ይህ በቫይረስ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ በአብዛኛው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ልጆች ላይ የሚከሰት ሽባነትን የሚያስከትል በሽታ ነው። የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ቢደረግልኝም እግሮቼ ሊድኑ አልቻሉም። በጊዜ ሂደት የባሰ እየተልፈሰፈሱ ሄደው የሰውነቴን ክብደት መሸከም አቃታቸው። አባቴ የአካል ጉዳተኛ በመሆኔ ምክንያት “ግማሽ ልጅ” እንደሆንኩ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር። እንቅስቃሴዬ መሬት ላይ በመንፏቀቅ ብቻ የተገደበ ከመሆኑም ሌላ ለራሴ ያለኝ ግምት በጣም ወርዶ ነበር፤ በዚህም የተነሳ አፈር ላይ እንደተጣልኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።

መሬት ላይ እየተንፏቀቅኩ ያሳለፍኩት የልጅነት ሕይወት

 ባደግኩበት ግቢ ውስጥ እኔና እናቴ እንዲሁም ሌሎች በድህነት የሚማቅቁ ቤተሰቦች ይኖሩ ነበር። ሰዎች ይወዱኝ የነበረ ቢሆንም የምናፍቀው፣ ያጣሁትን የአባት ፍቅር ለማግኘት ነበር። አንዳንዶች የታመምኩት በድግምት ምክንያት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ሌሎች ደግሞ እናቴ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን የሚንከባከቡ ድርጅቶች በር ላይ ትታኝ እንድትሄድ ሐሳብ ያቀርቡላት ነበር። እንዲህ ብታደርግ እኔን ከመንከባከብ እንደምትገላገል ይነግሯታል። እናቴ ግን በሐሳባቸው አልተስማማችም፤ እኔን ለመንከባከብ ጠንክራ ትሠራ ነበር።

 መቆምም ሆነ መራመድ ስለማልችል መንፏቀቅ ነበረብኝ። ሆኖም መሬት ላይ እና ሌሎች የማይመቹ ቦታዎች ላይ ስንፏቀቅ ሰውነቴ ይጎዳ ነበር። ጉዳቱን ለመቀነስ፣ ወፈር ያሉ ልብሶችን ነበር የምለብሰው። እጆቼ እንዳይጎዱ ለመከላከል ነጠላ ጫማ እንደ ጓንት እጠቀማለሁ። በኋላም ለእጆቼ የተሻለ ጥበቃ የሚያደርጉ አነስ ያሉ እንጨቶችን መጠቀም ጀመርኩ። ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንጨቶቹን በእጆቼ ይዤ መሬት ላይ ወደ ፊት እሳባለሁ። ከዚያም ወገቤን እጥፍ አድርጌ እግሮቼን ወደ ፊት አመጣቸዋለሁ። በዚህ መልኩ አንድ “እርምጃ” ከተራመድኩ በኋላ ቀጣዩን እርምጃ ለመራመድ ይህንኑ አድካሚ ሂደት እደግመዋለሁ። ይህ እንቅስቃሴ በእጆቼና በትከሻዬ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። በጣም አድካሚ ከመሆኑ የተነሳ ከግቢያችን የምወጣው ከስንት አንዴ ነው። ትምህርት ቤት መሄድም ሆነ ከሌሎች ልጆች ጋር መጫወት አልችልም ነበር። ‘እናቴ የሆነ ነገር ብትሆን ምን ይውጠኛል?’ እያልኩ እጨነቅ ነበር።

 ወደ አምላክ በመጸለይ፣ ለማኝ እንዳልሆን እንዲረዳኝ ጠየቅኩት። ወደ እሱ ከቀረብኩና በትክክለኛው መንገድ ካገለገልኩት እንደሚንከባከበኝ ይሰማኝ ነበር። በመሆኑም በ1981 የሆነ ቀን ላይ ተነስቼ እንደምንም ከግቢያችን በመውጣት በሰፈራችን ወደሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ሄድኩ። ሰዎቹ እኔን የሚያዩበትን መንገድ ስመለከት ጭንቅ አለኝ። ፓስተሩ በጥሩ መንገድ አልተቀበለኝም፤ በዚያ ላይ የተቀመጥኩት ሌሎች የከፈሉበት ወንበር ላይ ስለነበር እናቴን ተቆጣት። በዚህም የተነሳ ድጋሚ ወደዚያ ላለመሄድ ወሰንኩ።

በሰማይ ካለው አባቴ ጋር ተዋወቅኩ

 በ1984 የ18 ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ቀን ጠዋት እንደተለመደው በቤታችን የላይኛው ክፍል ወዳለው መስኮት ሄጄ ተቀመጥኩ። በአካባቢያችን የሚከናወነውን ነገር የማየው እዚያ ቁጭ ብዬ ነበር። ከዚያ ግን ወደ ታች ወርጄ ከግቢያችን ውጭ ወዳለ ብዙ ጊዜ ሰው የማይኖርበት ቦታ ሄድኩ። እዚያ ስደርስ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩ ሁለት ወንዶች አገኘሁ። እነዚህ ሰዎች ወደፊት ከበሽታዬ የምገላገልበት አስደሳች ጊዜ እንደሚመጣ ነገሩኝ። ኢሳይያስ 33:24⁠ን እና ራእይ 21:3, 4⁠ን አነበቡልኝ። ከዚያም በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለ የሚያማምሩ ሥዕሎች ያሉት ብሮሹር ሰጡኝና በቀጣዩ ጊዜ ተመልሰው መጥተው ይበልጥ እንደሚያስተምሩኝ ቃል ገቡልኝ።

 በቀጣዩ ጊዜ ሲመጡ፣ ፖሊን ከተባለች በቅርቡ ወደ አገሪቱ የመጣች ሚስዮናዊ ጋር እንደሚያስተዋውቁኝና ከእሷ ጋር ውይይቴን መቀጠል እንደምችል ነገሩኝ። በኋላም እንዳሉት ከእሷ ጋር አገናኙኝ፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በእኔና በፖሊን መካከል ያለው ግንኙነት ልክ እንደ እናትና እንደ ልጅ ሆነ። ወላጅ እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን “ከአዲሷ እናቴ” ጋር ማጥናቴን እንድቀጥል ታበረታታኝ ነበር፤ ፖሊን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር፣ ትዕግሥትና ደግነት ታሳየኝ እንዲሁም ሁሌም ትኩረት ሰጥታ ትንከባከበኝ ነበር። ንባብም አስተምራኛለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን ጽሑፍ በመጠቀም ስናፍቀው ከነበረው አፍቃሪ አባት ጋር አስተዋወቀችኝ።

ፖሊን የተባለች ሚስዮናዊ መጽሐፍ ቅዱስን አስጠንታኛለች

 ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር በደስታ እንድሞላ አደረገኝ። አንድ ቀን ፖሊንን የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት a ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት እችል እንደሆነ ጠየቅኳት፤ ስብሰባው የሚደረገው እኛ ቤት አቅራቢያ ነበር። ፖሊንም እሺ አለችኝ። በቀጣዩ ማክሰኞ፣ ይዛኝ ለመሄድ ስትል ቤት መጥታ እስክተጣጠብና እስክለባብስ ጠበቀችኝ። የሆነ ሰው ፖሊንን የታክሲ እንድትከፍልልኝ እንድጠይቃት ነግሮኝ ነበር፤ እኔ ግን “እንጨቶቼን ይዤ ራሴው እሄዳለሁ” አልኩት።

 የምንሄድበት ሰዓት ሲደርስ እናቴና ጎረቤቶቻችን ስጋት ገብቷቸው ያዩኝ ነበር። ከግቢው እየወጣን ሳለን አንዳንድ ጎረቤቶቻችን ፖሊንን “ልጅቷን አስገድደሽ ነው የምትወስጃት!” ብለው ጮኹባት።

 በዚህ ጊዜ ፖሊን “ጄ፣ መሄድ ትፈልጊያለሽ?” በማለት በእርጋታ ጠየቀችኝ። ይህ በይሖዋ እንደምታመን የማሳይበት አጋጣሚ ነበር። (ምሳሌ 3:5, 6) “አዎ!” ስል መለስኩላት። ከዚያም “ይህ የራሴ ውሳኔ ነው” አልኩ። እንዲህ ስል ጎረቤቶቼ መቃወማቸውን አቁመው ወደ በሩ ስሄድ ዝም ብለው ይመለከቱኝ ጀመር። ከግቢው ስወጣ በደስታ አጨበጨቡልኝ።

 ስብሰባው ልዩ ነበር! በጣም ነበር የተደሰትኩት! ሁሉም ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። በንቀት ዓይን የተመለከተኝ ሰው አልነበረም። የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ። ስለዚህ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በስብሰባው ላይ በቋሚነት መገኘት ጀመርኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ በሚደረጉት ተለቅ ያሉ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት እችል እንደሆነ ጠየቅኩ። ድሃ ስለነበርኩ ያለኝ ሁለት ቀሚስና አንድ ነጠላ ጫማ ብቻ ነበር። ያም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች እንደማያገሉኝ እርግጠኛ ነበርኩ። እነሱም አላሳፈሩኝም።

 ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለመድረስ እስከ መንገዱ ጫፍ በራሴ መሄድ፣ ከዚያም ተራራው ሥር ድረስ ታክሲ መያዝ ያስፈልገኛል። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ወንድሞች በእጃቸው ተሸክመው ወደ አዳራሹ ያስገቡኛል።

 የይሖዋን ጥሩነት ቀምሼ ስላየሁ እሱን መጠጊያዬ የማድረግ ፍላጎት አደረብኝ። በቋሚነት በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። (መዝሙር 34:8) በዝናባማው ወቅት ብዙ ጊዜ ወደ አዳራሹ የምደርሰው በስብሼና ጭቃ በጭቃ ሆኜ ስለሆነ እዚያ ከደረስኩ በኋላ ልብሴን እቀይራለሁ፤ ሆኖም በከፈልኩት መሥዋዕትነት ተቆጭቼ አላውቅም!

 በ1985 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ ተሞክሮዬ ወጥቶ ነበር። በስዊዘርላንድ የምትኖር ጆዜት የተባለች የይሖዋ ምሥክር የዓመት መጽሐፍ ላይ ተሞክሮዬን ስታነብ ልቧ በጣም ስለተነካ በእጅ የሚነዳ ባለ ሦስት እግር ጋሪ ላከችልኝ፤ ጋሪው ቆንጆ የጭቃ መከላከያና ከኋላው ደማቅ አንጸባራቂ አለው። ይሄን ጋሪ ካገኘሁ በኋላ ኮራ ብዬ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ጀመርኩ። ትናንሽ ልጆች በጋሪዬ በጣም ነበር የሚደነቁት፤ ዘናጩ ወንበሬ ላይ ቁጭ ብዬ ስነዳ ማየት ደስ እንደሚላቸው ይነግሩኛል። ከወደቅኩበት አፈር ተነስቼ ልክ እንደ ንግሥት እንደሆንኩ ተሰማኝ፤ ሰዎች ያከብሩኝ ጀመር።

ከፍ ወዳሉ ቦታዎች መድረስ

 ቀድሞውንም ቢሆን ቀላልና በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ሕይወት ስለምመራ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ አልተቸገርኩም። ለመንቀሳቀስ የሚያስችለኝ ጋሪ ስላለኝ ደግሞ በአገልግሎት መካፈል ቻልኩ፤ ከዚያም ነሐሴ 9, 1986 ተጠመቅኩ። መጠመቄ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል፤ ፈጽሞ እደርስባቸዋለሁ ብዬ ያላሰብኳቸው ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ አድርሶኛል። ውስጣዊ ደስታና እርካታ ማግኘት ችያለሁ፤ ለራሴ ያለኝ ግምትና በራስ የመተማመን ስሜቴም ጨምሯል፤ ምክንያቱም አሁን የሚወደኝ አባትና ከልብ የሚያስቡልኝ ሰዎች አግኝቻለሁ።

 ይሖዋ ላደረገልኝ ነገር ውለታውን መመለስ ስለፈለግኩ በአቅኚነት ለማገልገል አሰብኩ፤ ሆኖም በአቅኚነት ማገልገል መቻሌ አጠራጠረኝ። (መዝሙር 116:12) ስለ ጉዳዩ ከጸለይኩ በኋላ ለመሞከር ወሰንኩ። ከጥር 1, 1988 ጀምሮ አቅኚ የሆንኩ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ አላቋረጥኩም። ይህም ብዙ በረከቶች አስገኝቶልኛል! ወርሃዊ የሰዓት ግቤ ላይ ለመድረስ የሚረዱኝ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ። በተጨማሪም ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ምን ያህል እንደሚደግፈኝ አይቻለሁ።—መዝሙር 89:21

 አቅኚ ከሆንኩ በኋላ ከበፊቱ የበለጠ ስለምንቀሳቀስ እግሮቼ ደካማ ቢሆኑም የተወሰነ ለውጥ ማሳየት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የፊዚዮቴራፒ ሕክምናና ጡንቻዎቼን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ስለፈለግኩ በቅርቡ ወደተከፈተ አንድ ክሊኒክ ሄድኩ። ሆኖም በዚያ የምትሠራ አንዲት ነርስ፣ ብዙ ጊዜ ስላልቀረኝ ባልለፋ እንደሚሻል ነገረችኝ። ሌላ የሥራ ባልደረባዋም ተመሳሳይ ነገር ስትነግረኝ ተስፋ ቆረጥኩ። ስለዚህ ወደ ቤቴ ተመለስኩና ይሖዋ የተስፋ መቁረጥ ስሜቴን ለመቋቋምና የሆነ ዓይነት ሕክምና ለማግኘት እንዲረዳኝ ለመንኩት።

 አገልግሎት ከሁሉ የተሻለ ሕክምና ሆኖልኛል። ብዙ እንቅስቃሴ የማደርግበት አጋጣሚ ሰጥቶኛል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፣ ብዙ ጊዜ እንዳልቀረኝ ከነገሩኝ ነርሶች መካከል አንዷ በስብሰባ አዳራሽ በኩል ስታልፍ አየችኝ። አሁንም በሕይወት በመኖሬ በጣም ተገረመች!

 ያለሁበት ሁኔታ ከባድ ቢሆንም በይሖዋ አገልግሎት ቀናተኛ ሆኜ ለመቀጠል ጥረት አድርጌአለሁ። ወንድሞች ቀናተኛ በመሆኔና ወደ ስብሰባ በጊዜ በመድረሴ ያመሰግኑኛል። በስብሰባዎች ላይ ሁሌም ቀደም ብዬ መገኘቴ ወንድሞቼንና እህቶቼን ሰላም ለማለትና እነሱን ትኩረት ሰጥቼ ለማዋራት ጊዜ ይሰጠኛል።

 የይሖዋን ጥሩነት ቀምሼ አይቻለሁ፤ በሕይወቴም ብዙ በረከቶችን አግኝቻለሁ። ሦስት ሰዎች እንዲጠመቁ መርዳት ችያለሁ። ከሦስቱ አንዷ የሆነችው አሜሊያ በ137ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት የመማር አጋጣሚ አግኝታለች። እኔም አስደናቂ የይሖዋ ዝግጅት በሆነው የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ ተካፍያለሁ! ይሖዋ የተደቆሰውን መንፈሴን ጠግኖልኛል፤ ለራሴ የነበረኝን ዝቅ ያለ አመለካከት እንዳስተካክል ረድቶኛል፤ በራሴ መተማመን እንድችልም ረድቶኛል። አሁን ሰዎች ያከብሩኛል። እንደ ድሮው በራሴ አልሸማቀቅም። በእውነት ቤት ውስጥ ጥሩ ወዳጆች አግኝቻለሁ፤ በምኖርበት በፍሪታውን ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱና በዓለም ዙሪያ ጭምር።

 አምላክ ማንኛውም የአካል ጉዳት የማይኖርበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ስለሰጠው ተስፋ ከተማርኩ አሁን 40 ዓመት ገደማ ሆኖኛል። ይህ ተስፋ ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ ማሰቤ አሁንም ያበረታታኛል፤ ደግሞም የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። አምላኬ ይሖዋ እንደማይዘገይ ስለማውቅ እሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። (ሚክያስ 7:7) እስካሁንም ድረስ በትዕግሥት መጠባበቄ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል። ይሖዋ የተለያዩ ችግሮችንና ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል። ሁሌም ልክ በትክክለኛው ጊዜ ላይ የእርዳታ እጁን ይዘረጋልኛል። ይሖዋ እንፏቀቅበት ከነበረው አፈር ላይ አንስቶ ፈጽሞ ያላሰብኩት ከፍታ ላይ ስላደረሰኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ሁሌም ከፊቴ ፈገግታ አይለይም።

a አሁን የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተብሎ ይጠራል።