በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፊሊስ ሊያንግ | የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ፈቃደኝነቴን አይቶ ባርኮኛል

ይሖዋ ፈቃደኝነቴን አይቶ ባርኮኛል

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው ርብቃ ለይሖዋ ፈቃድ ስትል ሕይወቷን የሚቀይር ነገር እንድታደርግ ተጠየቀች። መልሷ “አዎ፣ እሄዳለሁ” የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 24:50, 58) ራሴን ያን ያህል ተፈላጊ ሰው እንደሆንኩ አድርጌ መቁጠሬ ባይሆንም ሕይወቴን ሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ተመሳሳይ የፈቃደኝነት መንፈስ ለማሳየት ጥሬያለሁ። ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ሆኖም ይሖዋ የፈቃደኝነት መንፈስ የሚያሳዩ አገልጋዮቹን ምን ያህል እንደሚባርክ፣ አንዳንድ ጊዜም ያልጠበቁትን ነገር እንደሚያደርግላቸው ተመልክቻለሁ።

አንድ አረጋዊ ሰው ውድ ሀብት ይዞልን መጣ

 ቤተሰባችን የሚኖረው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነበር፤ ሮደፖርት ወደተባለ ከተማ ከተዛወርን ከጥቂት ዓመታት በኋላ አባቴ ሞተ። በመሆኑም ቤተሰቤን ለመደጎም ሥራ መቀጠር ነበረብኝ፤ በ1947 ገና በ16 ዓመቴ የስልክ አገልግሎት በሚሰጥ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ሙሉ ቀን ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። አንድ ቀን ቤት እያለሁ አንድ አረጋዊ ሰው በራችንን አንኳኳ፤ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ኮንትራት እንድንገባ ጋበዘን። እሱን ላለማስቀየም ስንል እሺ አልን።

 ብዙም ሳይቆይ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት የማግኘት ጉጉት አደረብን። እናቴ በወጣትነቷ የደች ተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበረች፤ ከጊዜ በኋላ፣ ቤተክርስቲያኗ በምታስተምረውና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መካከል ልዩነት እንዳለ ማስተዋል ጀመረች። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማን፤ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። በ1949 ከቤተሰባችን መካከል መጀመሪያ እኔ ተጠመቅሁ። ተቀጥሬ መሥራቴን ለተወሰኑ ዓመታት ቀጥያለሁ፤ ፍላጎቴ ግን ይሖዋን ማገልገል ነበር።

እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ለመሄድ ፈቃደኛ መሆን

FomaA/stock.adobe.com

ኩክሲስተርስ

 በ1954 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። የት ሄጄ ባግዝ እንደሚሻል የደቡብ አፍሪካን ቅርንጫፍ ቢሮ ጠየቅሁ። ቅርንጫፍ ቢሮው በፕሪቶሪያ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረበልኝ፤ አብራኝ የምታገለግል አቅኚ እህትም ተመደበችልኝ። በዚያ ያገኘነው ቤት ከሞላ ጎደል ምቹ ነበር፤ ደግሞም ትዝ ይለኛል፣ በአቅራቢያችን ኩክሲስተርስ የሚባል ጣፋጭ የተጠበሰ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ነበር።

 በኋላ ላይ፣ አብራኝ የምታገለግለው አቅኚ አገባች፤ ያን ጊዜ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ የነበረው ወንድም ጆርጅ ፊሊፕስ ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ግብዣውን ደስ እያለኝ ተቀበልኩ።

 በ1955 ሃሪስስሚዝ በተባለች ከተማ በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። እኔና አዲሷ የአቅኚነት ጓደኛዬ ቤት ማግኘት ተቸግረን ነበር። በአንድ ወቅት የአካባቢው ቤተክርስቲያን ስለ እኛ ሲሰሙ አከራያችንን ከቤት እንድታስወጣን አስገደዷት።

 ከጊዜ በኋላ ጆሃንስበርግ በሚገኘው ፓርክኸርስት አካባቢ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚያ አብረውኝ የሚያገለግሉ ሁለት ሚስዮናውያን እህቶች ነበሩ። በኋላ ላይ አንደኛዋ አገባች፤ ሁለተኛዋ ደግሞ ሌላ አካባቢ ተመደበች። ደስ የሚለው አይሊን ፖርተር የምትባል አንዲት የምወዳት እህት በዚያ ትኖር ነበር። እሷና ቤተሰቧ ለእኔ የሚሆን ክፍል ባይኖራቸውም አብሬያቸው እንድኖር ጋበዘችኝ፤ አንደኛው ጥግ ላይ መጋረጃ ጋርደው መኝታ አዘጋጁልኝ። አይሊን ደግና የምታበረታታ እህት ነበረች፤ ከእሷ ጋር መኖር ጨርሶ አልከበደኝም። ብዙ የቤት ውስጥ ሥራ ቢኖርባትም ለእውነት ያላት ቅንዓት ያስደንቀኝ ነበር።

 ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በኢስተርን ኬፕ ግዛት በምትገኘው አሊዋል ኖርዝ ከተማ ተመደብኩ፤ የአቅኚነት ጓደኛዬ መርሊን (መርል) ሎረንስ ትባላለች። ሁለታችንም ያኔ በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ነበርን። በዚያ የምትኖር ዶሮቲ የምትባል አንዲት አረጋዊት እህት ጥሩ ምሳሌ ሆናልናለች፤ በጣም ስለምንወዳት ‘አክስቴ’ ብለን ነበር የምንጠራት። ከብዙ ዓመታት በፊት አገልግሎት ላይ ሳለች ውሾች ክፉኛ ጎድተዋት ነበር፤ ይህ ግን ቅንዓቷን አላቀዘቀዘባትም።

 በ1956 መርል በ28ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ላይ ተጋበዘች። አብሬያት ብሄድ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር! ደስ የሚለው ግን እህት ዶሮቲ በጣም ተንከባክባኛለች፤ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ቢኖረንም የቅርብ ጓደኛሞች ሆንን።

 በኋላ ላይ እኔም እንደ መርል በጊልያድ ትምህርት ቤት ላይ እንድካፈል ተጋበዝኩ! ምን ያህል እንደተደሰትኩ መገመት ትችላላችሁ። ጊልያድ ከመሄዴ በፊት ናይጀል በምትባል ከተማ ስምንት ወር ቆይቻለሁ፤ በዚያ አብራኝ የምታገለግለው እህት ካቲ ኩክ የተባለች የጊልያድ ምሩቅ ነበረች። ካቲ ለጊልያድ ይበልጥ እንድጓጓ አድርጋኛለች፤ በመጨረሻም ጥር 1958 ወደ ኒው ዮርክ ሄድኩ።

ለመሠልጠን ፈቃደኛ መሆን

 በጊልያድ ከሁለት እህቶች ጋር አንድ ክፍል ውስጥ እንድኖር ተመደብኩ፤ አንደኛዋ ቲያ አሉኒ የተባለች የሳሞአ እህት ስትሆን ሌላኛዋ ደግሞ አይቪ ካቬ የተባለች የማኦሪ እህት ናት። ደቡብ አፍሪካ እያለሁ በአፓርታይድ ሥርዓት የተነሳ ነጮች ከሌሎች ዘሮች ጋር መቀላቀል አይችሉም ነበር፤ ስለዚህ ከእነዚህ እህቶች ጋር መኖር ለእኔ ለየት ያለ አጋጣሚ ነበር። ወዲያውኑ ነው የቀረብኳቸው፤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎችን ባቀፈ ትምህርት ቤት ላይ በመገኘቴም በጣም ተደሰትኩ።

 ከጊልያድ አስተማሪዎቻችን አንዱ ወንድም ማክስዌል ፍሬንድ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚያስተምርበት መንገድ ትንሽ ጠንከር ያለ ነው። ክፍሉ ውስጥ ሦስት መብራቶች አዘጋጅቶ ነበር፤ “ቅጥነት፣” “ፍጥነት” እና “ግለት” የሚል ተለጥፎባቸው ነበር። ወንድም ፍሬንድ አንድ ተማሪ ንግግር ወይም ሠርቶ ማሳያ ሲያቀርብ ድምፁ ከሦስቱ አንዱ እንደጎደለው ከተሰማው መብራቱን ያበራበታል። በተፈጥሮዬ ዓይናፋር ስለሆንኩ ብዙ መብራት ከሚበራባቸው ተማሪዎች አንዷ ነበርኩ፤ በዚህ የተነሳ ያለቀስኩበት ጊዜም ነበር! እንደዚያም ሆኖ ለወንድም ፍሬንድ ልዩ ፍቅር ነበረኝ። በትምህርታችን መሃል የጽዳት ሥራ ተሰጥቶኝ ስደክም ሲያየኝ ቡና ይዞልኝ ይመጣ ነበር።

 ወራት እያለፉ ሲሄዱ ‘የት እመደብ ይሆን?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። የቀድሞ የአቅኚነት ጓደኛዬ መርል ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቃ ፔሩ ተመድባ ነበር። አብራት የተመደበችው ሚስዮናዊት እህት በቅርቡ ታገባ ነበር። ስለዚህ በእሷ ምትክ እኔን እንዲልኩኝ ወንድም ናታን ኖርን እንድጠይቀው ሐሳብ አቀረበችልኝ፤ በወቅቱ ሥራውን በኃላፊነት የሚመራው እሱ ነበር። ወንድም ኖር በየተወሰነ ሳምንቱ ጊልያድ ይመጣ ስለነበር እሱን የማነጋገር አጋጣሚ አገኘሁ። በኋላ ላይ ስመረቅ ፔሩ ተመደብኩ!

በተራራማ አካባቢ ማገልገል

ከመርል (በስተ ቀኝ) ጋር በፔሩ፣ 1959

 ፔሩ ውስጥ በሊማ ከተማ እንደገና ከመርል ጋር የማገልገል አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ! የስፓንኛ ቋንቋ ችሎታዬ ገና ብዙ ይቀረው ነበር፤ ያም ቢሆን ገና ከጅምሩ እድገት የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩኝ። በኋላ ላይ እኔና መርል በአያኩቾ እንድናገለግል ተመደብን፤ አያኩቾ ተራራ ላይ ከፍ ብላ የምትገኝ ከተማ ናት። እውነቱን ለመናገር ምድቡ ቀላል አልሆነልኝም። የተወሰነ ስፓንኛ ብማርም እዚያ ያሉ ብዙ ሰዎች የሚናገሩት የኬችዋ ቋንቋ ብቻ ነው። አየሩ ስስ በሆነበት ተራራማ አካባቢ መኖርም ትንሽ አታግሎናል።

በፔሩ ሳገለግል፣ 1964

 በአያኩቾ ያከናወንኩት አገልግሎት ያን ያህል ስኬታማ እንደሆነ አልተሰማኝም ነበር፤ እውነት በዚህ አካባቢ ሥር የሚሰድድም አልመሰለኝም። በአሁኑ ወቅት ግን አያኩቾ ውስጥ ከ700 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ፤ የኬችዋ (አያኩቾ) ቋንቋ የርቀት የትርጉም ቢሮ የሚገኘውም እዚሁ ነው።

 ከጊዜ በኋላ መርል፣ ራሞን ካስቲዮ የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች አገባች፤ በ1964 ራሞን ለ10 ወር ትምህርት ጊልያድ ሄደ። አብረውት ከሚማሩት ወንድሞች አንዱ ፉ ሎን ሊያንግ የተባለ ወጣት ነው። ከዚህ ወጣት ጋር ጊልያድ አብረን ተምረናል። ሆንግ ኮንግ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዲሠራ ስለፈለጉ ለተጨማሪ ሥልጠና ወደ ጊልያድ ተጠራ። a ፉ ሎን ራሞንን ‘እንዴት ናት?’ ብሎ ስለ እኔ ጠየቀው። በኋላም ከፉ ሎን ጋር መጻጻፍ ጀመርን።

 ፉ ሎን ደብዳቤ መጻጻፋችን መጠናናት እንደሆነ ገና ከመነሻው ነው ግልጽ ያደረገልኝ። ሆንግ ኮንግ ውስጥ አብሮት የሚያገለግለው ሚስዮናዊ ሃሮልድ ኪንግ ነበር፤ አዘውትሮ ወደ ፖስታ ቤት ይሄድ ስለነበር ፉ ሎን ለእኔ የሚጽፋቸውን ደብዳቤዎች ለመላክ ተስማማ። ሃሮልድ፣ ፉ ሎን ለእኔ በሚልካቸው ፖስታዎች ላይ ትናንሽ ሥዕሎች ይሥልልኝ ወይም አጫጭር ማስታወሻዎች ይጽፍልኝ ነበር፤ ለምሳሌ “ቶሎ ቶሎ እንዲጽፍ አበረታታዋለሁ!” እንዳለኝ ትዝ ይለኛል።

ከፉ ሎን ጋር

 እኔና ፉ ሎን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ከተጻጻፍን በኋላ ለመጋባት ወሰንን። ሰባት ዓመት ገደማ ያገለገልኩባትን ፔሩን ለቅቄ ወጣሁ።

በሆንግ ኮንግ አዲስ ሕይወት

 ኅዳር 17, 1965 ከፉ ሎን ጋር ተጋባን። ሆንግ ኮንግን ለመልመድ ጊዜ አልወሰደብኝም፤ ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ከሌሎች ሁለት ባልና ሚስት ጋር እንኖር ነበር። ቀን ላይ ፉ ሎን ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ሆኖ የትርጉም ሥራ ይሠራል፤ እኔ ደግሞ አገልግሎት እወጣለሁ። ቻይንኛ መማር ከባድ ነበር፤ ሆኖም ሌሎቹ ሚስዮናውያን እህቶችና ውዱ ባለቤቴ በትዕግሥት ረድተውኛል። መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናው ልጆችን መሆኑም አዲስ ቋንቋ መማር የሚፈጥረውን ውጥረት ቀንሶልኛል።

ስድስቱ የሆንግ ኮንግ ቤቴል ቤተሰብ አባላት በ1960ዎቹ አጋማሽ። እኔና ፉ ሎን መሃል ላይ ነን

 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ፉ ሎን አዲስ ለመጡ ሚስዮናውያን ቻይንኛ እንዲያስተምር ተወሰነ። በመሆኑም ሆንግ ኮንግ ውስጥ ግወን ዶንግ በተባለ አካባቢ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። b በዚያ አካባቢ አገልግሎቱ በጣም አስደሳች በመሆኑ ብዙ ጊዜ ወደ ቤት መመለስ አልፈልግም ነበር!

 በ1968 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለ አዲስ ማስጠኛ መጽሐፍ ወጣ፤ ይህ መጽሐፍ በመውጣቱ በጣም ነው የተደሰትኩት። በተለይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ክርስትና የማያውቁ ሰዎችን ለማስጠናት የእውነት መጽሐፍ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” ከተባለው ቀደም ሲል ከነበረው መጽሐፍ ይበልጥ ቀላል ነው።

 ሆኖም አንድ ያላስተዋልኩት ነገር ነበር፤ ተማሪዎቹ በጽሑፉ ላይ ያለውን ጥያቄ ስለመለሱ ብቻ እውነት የገባቸው ይመስለኝ ነበር። ለምሳሌ አንደኛዋ ጥናቴ እውነት መጽሐፍን አጥንታ ብትጨርስም በአምላክ መኖር እንደማታምን የገባኝ በኋላ ላይ ነበር። ጥናቶቼ ስለሚማሩት ነገር ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ ተጨማሪ ጥያቄዎችን መጠየቅና መወያየት እንዳለብኝ ተማርኩ።

 በግወን ዶንግ የተወሰኑ ዓመታት ካገለገልን በኋላ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ተመለስን፤ በዚያም ፉ ሎን የሆንግ ኮንግ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በእነዚያ ዓመታት በቤት ጽዳት እንዲሁም እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ሠርቻለሁ። ፉ ሎን በሚስጥር የሚያዙ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የሚጓዝበት ጊዜ ነበር፤ በእነዚህ ወቅቶች አብሬው ባልጓዝም እሱን ለመደገፍ የምችለውን ሁሉ በማድረጌ እደሰት ነበር።

ፉ ሎን የኢሳይያስ ትንቢት የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ ሁለት በጥንታዊው እና ቀለል ባለው የቻይንኛ የፊደል አጣጣል መውጣቱን ሲያበስር

ያልጠበቅሁት ለውጥ አጋጠመኝ

 በ2008 አንድ አሳዛኝ ክስተት አጋጠመኝ፤ በአንድ ጀምበር ሕይወቴ ምስቅልቅሉ ወጣ። ውዱ ባለቤቴ ፉ ሎን ጉዞ ላይ እያለ በድንገት ሕይወቱ አለፈ። ይህ የሆነው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ሊከበር ትንሽ ሲቀረው ነበር። ልቤ በሐዘን ተሰበረ። ወንድሞችና እህቶች እኔን ለማጽናናት ተረባረቡ። በመታሰቢያው በዓል ላይ ስሜቴን መቆጣጠር በጣም አታግሎኝ ነበር፤ በዓሉ ላይ ለተጋበዘች አንዲት እንግዳ ጥቅሶች እያወጣሁ ማሳየቴ ነው እንባዬን ለመቆጣጠር የረዳኝ። ፉ ሎን የሚወደው አንድ ጥቅስ አበረታቶኛል፦ “‘እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁ” ይላል።​—ኢሳይያስ 41:13

 ፉ ሎን ከሞተ ከሰባት ዓመት በኋላ የሆንግ ኮንግ ወንድሞች ለጤንነቴ የተሻለ ክትትል ማግኘት እንድችል ተለቅ ወዳለ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድዛወር ሐሳብ አቀረቡልኝ። በመሆኑም በ2015 ወደ ደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርኩ፤ ቅርንጫፍ ቢሮው በ1947 እውነትን ከሰማሁበት አካባቢ ብዙም አይርቅም።

 በይሖዋ አገልግሎት በርካታ አስደሳች ዓመታት አሳልፌያለሁ፤ ይሖዋም የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየቴ እንደባረከኝ ይሰማኛል። ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ካሉ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ጋር አሁንም እንገናኛለን። ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ያደረግነውን ትንሽ የሚመስል አስተዋጽኦ እንደሚባርከው ተመልክቻለሁ። ለምሳሌ በ1958 የፔሩ አስፋፊዎች 760 ነበሩ፤ በ2021 ግን 133,000 ገደማ ደርሰዋል። በ1965 በሆንግ ኮንግ 230 ገደማ አስፋፊዎች ነበሩ፤ በ2021 ቁጥራቸው ጨምሮ 5,565 ደርሰዋል።

 ዕድሜዬ ስለገፋ የድሮዬን ያህል ማድረግ አልችልም። የፈቃደኝነት መንፈሴ ግን አሁንም እንደ ቀድሞው ነው፤ ይሖዋ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ብዙ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ አውቃለሁ። ያን ጊዜ እኔም በፈቃደኝነት “አዎ፣ እሄዳለሁ” ብዬ ራሴን ለማቅረብ እጓጓለሁ።

a ፉ ሎን ሊያንግ እንዴት ወደ እውነት እንደመጣ የሚገልጽ ዘገባ በ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 51 ላይ ይገኛል

b ፉ ሎን ሊያንግ በግወን ዶንግ ስላከናወነው አገልግሎት የሚገልጽ ዘገባ በ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 63 ላይ ይገኛል