ክርስቲያናዊ ሕይወት
በመስከረም ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚካሄድ ልዩ ዘመቻ
በመስከረም ወር በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች በሙሉ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ለመጋበዝ ልዩ ጥረት እናደርጋለን። አስፋፊዎች ለ30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚዎች መሆን ይችላሉ። በዚህ ልዩ ዘመቻ የምንካፈለው እንዴት ነው?
-
በምንመሠክርበት ወቅት፦ የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ የብሮሹሩን የጀርባ ሽፋን ተጠቀሙ፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ሞክሩ። ተመላልሶ መጠየቆችን ጨምሮ ቀደም ሲል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለማስታወስ ጥረት አድርጉ። ከዚህ ቀደም ለማጥናት ፈቃደኛ ያልነበሩ ቢሆንም እንኳ አዲሱ የማስጠኛ ዘዴያችንና ብሮሹሩ ትኩረታቸውን ሊስበው ይችላል። ብሮሹሩን በተዘጉ ቤቶች መተው ወይም ቀደም ሲል ፍላጎት እንዳላቸው ላልገለጹልን ሰዎች ከደብዳቤ ጋር መላክ አይኖርብንም። የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ በዚያ ወር ተጨማሪ የስምሪት ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል።
-
ሌሎች አጋጣሚዎች፦ ጉባኤያችሁ የጽሑፍ ጋሪ የሚጠቀም ከሆነ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር ከፊት ለፊት እንዲታይ አድርጉ። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ብሮሹሩን ሲወስዱ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማጥናት የሚችሉበት ዝግጅት እንዳለ ግለጹላቸው። ጥናቱ የሚካሄደው እንዴት እንደሆነ እዚያው በአጭሩ አሳዩአቸው፤ ወይም ሌላ ጊዜ ለማሳየት ዝግጅት አድርጉ። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ብቃት ያላቸው አስፋፊዎች በክልሉ ውስጥ ወደሚገኙ የንግድ ቦታዎች ሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ሰዎችን እንዲጋብዙ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። ለሥራ ባልደረቦቻችሁ ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክሩ ለምታገኟቸው ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ግብዣ ማቅረብ ትችላላችሁ።
ኢየሱስ ‘ሰዎችን እያስተማርን ደቀ መዛሙርት እንድናደርጋቸው’ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ማቴ 28:19, 20) ይህ ልዩ ዘመቻ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ተጠቅመን ይህን ተልዕኮ ለመፈጸም እንደሚረዳን ተስፋ እናደርጋለን።