ክርስቲያናዊ ሕይወት
ትንሣኤ—በቤዛው አማካኝነት የተገኘ ስጦታ
የመታሰቢያው በዓል፣ በቤዛው አማካኝነት ወደፊት በምናገኛቸው በረከቶች ለምሳሌ እንደ ትንሣኤ ባሉ ተስፋዎች ላይ ለማሰላሰል ጥሩ አጋጣሚ ይከፍትልናል። ይሖዋ የሰው ልጆች እንዲሞቱ ዓላማው አልነበረም። የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን በጣም አሳዛኝ ነገሮች መካከል አንዱ የሆነው ለዚህ ነው። (1ቆሮ 15:26) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በአልዓዛር ሞት ምክንያት ሲያለቅሱ መመልከቱ አሳዝኖታል። (ዮሐ 11:33-35) ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ ይሖዋ የምንወደውን ሰው በሞት በማጣት የሚደርስብንን ሐዘን ሲመለከት እንደሚያዝን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐ 14:7) ይሖዋ አገልጋዮቹን ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል፤ እኛም ይህን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ይኖርብናል።—ኢዮብ 14:14, 15
ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ስለሆነ ትንሣኤ የሚከናወነው በየተራ እንደሆነ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። (1ቆሮ 14:33, 40) በቀብር ሥርዓት ፈንታ ከሞት የተነሱ ሰዎችን የምንቀበልበት ዝግጅት ይኖራል። በተለይ ሐዘን ሲያጋጥምህ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ታሰላስላለህ? (2ቆሮ 4:17, 18) ይሖዋ ቤዛ ስላዘጋጀና የሞቱ ሰዎች ተነስተው በሕይወት እንደሚኖሩ የሚገልጽ ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲሰፍር በማድረጉ ታመሰግነዋለህ?—ቆላ 3:15
-
ከሞት ተነስተው ለማየት የምትጓጓው የትኞቹን ጓደኞችህን ወይም ዘመዶችህን ነው?
-
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች መካከል በተለይ እነማንን ለማግኘት ትጓጓለህ?