ክርስቲያናዊ ሕይወት
በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ለዓይነ ስውራን መመሥከር
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ ዓይነ ስውራን የማያውቁትን ሰው ማነጋገር ይፈራሉ። በመሆኑም ለእነሱ መመሥከር ክህሎት ይጠይቃል። ይሖዋ ለዓይነ ስውራን ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል። (ዘሌ 19:14) እኛም ቅድሚያውን ወስደን ዓይነ ስውራንን በመንፈሳዊ በመርዳት የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን።
ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
-
ዓይነ ስውራንን “ፈልጉ”። (ማቴ 10:11) ዓይነ ስውር የሆነ የቤተሰብ አባል ያለው ሰው ታውቃላችሁ? ዓይነ ስውራንን ለመርዳት ተብለው የተዘጋጁ ጽሑፎችን የሚፈልጉ ትምህርት ቤቶች፣ እንክብካቤ የሚሰጡ ተቋማት ወይም ሌሎች ድርጅቶች በክልላችሁ ውስጥ አሉ?
-
በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት አሳዩ። ከዓይነ ስውራን ጋር ስትነጋገሩ ወዳጃዊ በሆነ መልኩ የምትቀርቧቸውና ልባዊ አሳቢነት የምታሳዩአቸው ከሆነ ስጋታቸው ሊጠፋ ይችላል። የክልላችሁን ሰዎች ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ጉዳዮችን በማንሳት ውይይት ለመጀመር ሞክሩ።
-
መንፈሳዊ እርዳታ ስጡ። የይሖዋ ድርጅት አጥርቶ የማየት ችግር ያለባቸውን ወይም ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ሲል ጽሑፎችን በተለያዩ ፎርማቶች አዘጋጅቷል። ግለሰቡ የሚፈልገው የትኛውን እንደሆነ ጠይቁት። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ፣ የጽሑፍ አገልጋዩ የጽሑፍ ትእዛዝ ሲልክ ዓይነ ስውር የሆነው ግለሰብ የሚፈልገውን ፎርማት በትክክል ማዘዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል።