ክርስቲያናዊ ሕይወት
የመንግሥቱ መዝሙሮች ድፍረት ይሰጣሉ
ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት አምላክን በመዝሙር አወድሰዋል። (ሥራ 16:25) በዘመናችንም ቢሆን በናዚ ጀርመን በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕና በሳይቤሪያ በግዞት የነበሩ ወንድሞቻችን የመንግሥቱን መዝሙሮች ይዘምሩ ነበር። ከእነዚህ ምሳሌዎች ማየት እንደሚቻለው መዝሙሮች ፈተና እየደረሰባቸው ላሉ ክርስቲያኖች ድፍረት የመስጠት ኃይል አላቸው።
ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ የተባለው አዲስ የመዝሙር መጽሐፍ በቅርቡ በበርካታ ቋንቋዎች ይዘጋጃል። መጽሐፉ እንደደረሰን መዝሙሮቹን በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን ላይ በመለማመድ ግጥሞቹን በቃላችን ለመያዝ ጥረት እናድርግ። (ኤፌ 5:19) እንዲህ ካደረግን በፈተና ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ መዝሙሮቹን እንድናስታውስ ይረዳናል። የመንግሥቱ መዝሙሮች በተስፋችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይረዱናል። በፈተና ውስጥ ስንሆን ያደፋፍሩናል። ጥሩ ስሜት ሲሰማን ደግሞ የሚያነቃቁ ግጥሞች ያሏቸው መዝሙሮቻችን የልባችንን ሐሴት እንድንገልጽና ‘በደስታ እንድንዘምር’ ያስችሉናል። (1ዜና 15:16፤ መዝ 33:1-3) እንግዲያው ሁላችንም ከመንግሥቱ መዝሙሮች ጥቅም ለማግኘት የቻልነውን ያህል ጥረት እናድርግ!
የጉልበት ሠራተኞችን ያበረታታ መዝሙር የሚለውን ቪዲዮ ተመልከቱ። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሩ፦
-
ወንድም ፍሮስት መዝሙር እንዲያቀናብር ያነሳሳው ምንድን ነው?
-
መዝሙሩ በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ወንድሞችን ያበረታታቸው እንዴት ነበር?
-
በዕለት ተዕለት በሚያጋጥሙህ በየትኞቹ ሁኔታዎች ሥር የመንግሥቱ መዝሙሮች ሊያጠናክሩህ ይችላሉ?
-
ከመንግሥቱ መዝሙሮች መካከል የትኞቹን በቃልህ መያዝ ትፈልጋለህ?