በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ ሕይወት

የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ነጥቦች

የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ነጥቦች

የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንደ ማንኛውም የጉባኤ ስብሰባ ሁሉ ይሖዋ ያደረገልን ዝግጅት ነው፤ እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች ለመነቃቃት ያስችለናል። (ዕብ 10:24, 25) አስፋፊዎቹን ማቀናጀትን፣ ክልል መስጠትንና ጸሎትን ጨምሮ ስብሰባው የሚወስደው ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባት ደቂቃ ሊሆን ይገባል። (የስምሪት ስብሰባው የሚካሄደው ከሌላ የጉባኤ ስብሰባ በኋላ ከሆነ ደግሞ የሚወስደው ጊዜ ከዚህም አጭር መሆን አለበት።) ስብሰባውን የሚመራው ሰው፣ አስፋፊዎች በዕለቱ በአገልግሎት ላይ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ሐሳብ ተዘጋጅቶ ማቅረብ አለበት። ለምሳሌ ቅዳሜ ዕለት አገልግሎት የሚወጡት ብዙዎቹ አስፋፊዎች በሳምንቱ መሃል አገልግሎት አይወጡም፤ ስለዚህ አስፋፊዎች አገልግሎት ላይ ምን እንደሚሉ ማስታወሱ ብቻውን በቂ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ምን ጠቃሚ ሐሳቦችንም ማንሳት ይቻላል?

  • ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ላይ የሚገኝ የውይይት ናሙና

  • ወቅታዊ ሁኔታዎችን ወይም ዜናዎችን ተጠቅሞ ውይይት መጀመር ስለሚቻልበት መንገድ

  • ሰዎች ለሚያነሱት የተቃውሞ ሐሳብ መልስ መስጠት ስለሚቻልበት መንገድ

  • በአምላክ መኖር የማያምን፣ በዝግመተ ለውጥ የሚያምን፣ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ወይም በክልላችሁ ውስጥ ያልተለመደ እምነት የሚከተል ሰው ቢያጋጥማችሁ እንዴት ማነጋገር እንደምትችሉ

  • jw.org ድረ ገጽ፣ JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለን አንድ ገጽታ መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ

  • ከማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ አንዱን መጠቀም ስለሚቻልበት መንገድ

  • በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ስለሚቻልበት መንገድ፤ ለምሳሌ በስልክ ምሥክርነት፣ በደብዳቤ ምሥክርነት፣ በአደባባይ ምሥክርነት፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ወይም ጥናት በመምራት

  • ደህንነትን ስለ መጠበቅ፣ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው ስለ ማስተናገድ፣ መልካም ምግባር ስለ ማሳየት፣ አዎንታዊ አመለካከት ስለ መያዝ ወይም እነዚህን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች ሐሳብ ማቅረብ

  • ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ በተባለው ብሮሹር ላይ የሚገኝ አንድ ትምህርት ወይም ቪዲዮ

  • የአገልግሎት ጓደኛችንን ማበረታታትና መርዳት ስለምንችልበት መንገድ

  • ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ አንድ ጥቅስ ወይም ከመስክ አገልግሎት ጋር በቀጥታ የተያያዘ የሚያበረታታ ተሞክሮ