ክርስቲያናዊ ሕይወት
ትዳራችሁን ታደጉ
ይሖዋ የጋብቻ ቃለ መሐላን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ባለትዳሮች አንዳቸው ከሌላው ጋር መጣበቅ እንዳለባቸው ገልጿል። (ማቴ 19:5, 6) ብዙዎቹ የአምላክ አገልጋዮች አስደሳች ትዳር አላቸው። ሆኖም ፍጹም የሆነ ትዳር የለም። በትዳር ውስጥ ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀርም። በዚህ ጊዜ፣ ባለትዳሮች ችግር ካጋጠማቸው መፍትሔው መለያየት ወይም መፋታት ነው የሚለው የተለመደ አመለካከት እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ታዲያ ያገቡ ክርስቲያኖች ትዳራቸውን መታደግ የሚችሉት እንዴት ነው?
አምስት ጠቃሚ እርምጃዎችን እንመልከት።
-
ማሽኮርመምና ሥነ ምግባር የጎደለው መዝናኛ የትዳርን ጥምረት ያዳክማሉ፤ በመሆኑም እንደነዚህ ካሉት ነገሮች በመራቅ ልባችሁን ጠብቁ።—ማቴ 5:28፤ 2ጴጥ 2:14
-
ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠናክሩ፤ እንዲሁም ትዳራችሁ እሱን የሚያስደስት እንዲሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።—መዝ 97:10
-
ምንጊዜም አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ትናንሽ ቢመስሉም እንኳ የትዳር ጓደኛችሁን የሚጠቅሙ የደግነት ድርጊቶችን አከናውኑ።—ቆላ 3:8-10, 12-14
-
አክብሮት በተሞላበት መንገድ አዘውትራችሁ ትርጉም ያለው የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ።—ቆላ 4:6
-
ለትዳር ጓደኛችሁ የሚገባውን የምታደርጉለት በፍቅር ይሁን።—1ቆሮ 7:3, 4፤ 10:24
ክርስቲያኖች ለትዳራቸው አክብሮት በማሳየት የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት ይችላሉ።
‘በጽናት ሩጡ’—የውድድሩን ሕግ አክብሩ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
-
አንድ ትዳር ጥሩ አጀማመር ቢኖረውም እንኳ ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ?
-
ባልና ሚስት በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንደጠፋ በሚሰማቸው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚረዷቸው እንዴት ነው?
-
ይሖዋ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ምን መመሪያዎችን ሰጥቷል?
-
ትዳር የሰመረ እንዲሆን ባልም ሆነ ሚስት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?