ክርስቲያናዊ ሕይወት
ዓመታዊ ስብሰባዎች ፍቅር ለማሳየት አጋጣሚ ይከፍቱልናል
በዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ በጣም የምንደሰተው ለምንድን ነው? በጥንቷ እስራኤል እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ የምናደርጋቸው ትላልቅ ስብሰባዎችም በመቶዎች፣ ብሎም በሺዎች ከሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ለማምለክ አጋጣሚ ይሰጡናል። በስብሰባዎቹ ላይ የሚቀርብልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያስደስተናል። በተጨማሪም ከጓደኞቻችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን። ለስብሰባዎቻችን ያለን ጥልቅ አድናቆት ሦስቱንም ቀናት እንድንገኝ ያነሳሳናል።
በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ፣ እኛ ስለምናገኘው ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ስለምንችልበት መንገድም ማሰብ ይኖርብናል። (ገላ 6:10፤ ዕብ 10:24, 25) በር ላይ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በማስቀደም ወይም ለራሳችንና አብረውን ለሚኖሩ ሰዎች ብቻ ወንበር በመያዝ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት መስጠት እንችላለን። (ፊልጵ 2:3, 4) ትላልቅ ስብሰባዎች አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት ጥሩ አጋጣሚ ይከፍቱልናል። ከፕሮግራሙ በፊትና በኋላ እንዲሁም በምሳ እረፍት ወቅት፣ ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገር ጥረት ማድረግ እንችላለን። (2ቆሮ 6:13) በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት የምንመሠርተው ወዳጅነት ለዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል! ከሁሉም በላይ ደግሞ ሌሎች ሰዎች የምናሳየውን እውነተኛ ፍቅር ሲመለከቱ ከእኛ ጋር ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ሊነሳሱ ይችላሉ።—ዮሐ 13:35
“ፍቅር ለዘላለም ይኖራል”! ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
-
ወንድሞች በ2019 በተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ለተገኙት ልዑካን ፍቅራቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
-
በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነትና ፍቅር በጣም አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?
-
የበላይ አካል አባላት ስለ የትኞቹ የክርስቲያናዊ ፍቅር ገጽታዎች አብራርተዋል?
-
በጀርመንና በደቡብ ኮሪያ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ክርስቲያናዊ ፍቅር ወንድሞቻችን አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው እንዴት ነው?
-
ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?