ክርስቲያናዊ ሕይወት
በአምላክ ቃል ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ
የአምላክ ቃል ሕይወታችንን ይለውጣል። (ዕብ 4:12) ይሁንና በውስጡ ከሚገኘው መመሪያና ምክር ጥቅም ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ‘የአምላክ ቃል’ መሆኑን ማመን ይኖርብናል። (1ተሰ 2:13) ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ። በምታነቡበት ጊዜ መጽሐፉን ያስጻፈው ይሖዋ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለማስተዋል ሞክሩ። ለአብነት ያህል፣ የምሳሌ መጽሐፍን በመመርመር በውስጡ ያለው ምክር ጊዜ የማይሽረው መሆኑን አስተውሉ።—ምሳሌ 13:20፤ 14:30
የጥናት ፕሮጀክት ጀምሩ። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ፈልጉ። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ” በሚለው ሥር “በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጽፏል” የሚለውን ተመልከቱ። በተጨማሪም በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተጨማሪ መረጃ ሀ3 ሥር የሚገኘውን ሐሳብ በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዳልተለወጠ ያላችሁን እምነት ማጠናከር ትችላላችሁ።
እምነት እንዲኖረን ያደረገን ምንድን ነው?—በአምላክ ቃል ላይ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
-
በካርናክ፣ ግብፅ ባለው ቤተ መቅደስ ግድግዳ ላይ የተገኘው ነገር የአምላክ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው?
-
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዳልተለወጠ እንዴት እናውቃለን?
-
መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ መቆየቱ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?—ኢሳይያስ 40:8ን አንብብ።