ክርስቲያናዊ ሕይወት
እውነተኛ አምልኮ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች መገንባትና በጥሩ ሁኔታ መያዝ
እስራኤላውያን ቤተ መቅደሱን ለመገንባት ብዙ ጉልበትና ወጪ ማፍሰስ ጠይቆባቸዋል። ይሁንና የግንባታ ሥራውን በቅንዓት ደግፈዋል። (1ዜና 29:2-9፤ 2ዜና 6:7, 8) የቤተ መቅደሱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ እስራኤላውያን ቤተ መቅደሱን የያዙበት መንገድ ምን ዓይነት መንፈሳዊ አቋም እንደነበራቸው የሚጠቁም ነው። (2ነገ 22:3-6፤ 2ዜና 28:24፤ 29:3) በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የመንግሥት አዳራሾችንና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባት፣ ለማጽዳትና ለመጠገን ብዙ ጊዜና ጉልበት ያውላሉ። ሆኖም በዚህ መንገድ ከይሖዋ ጋር መሥራት ትልቅ መብት ከመሆኑም ሌላ የቅዱስ አገልግሎታችን አንዱ ክፍል ነው።—መዝ 127:1፤ ራእይ 7:15
በሚከተሉት መንገዶች ተሳትፎ ማድረግ እንችላለን፦
-
ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ ወንበሮችን ማስተካከልና የወዳደቁ ነገሮችን ማነሳሳት። እንዲህ ለማድረግ ሁኔታህ የማይፈቅድልህ ከሆነ የተቀመጥክበትን አካባቢ ማስተካከል ትችላለህ።
-
በመንግሥት አዳራሹ መደበኛ የጽዳትና የጥገና ሥራ መካፈል። ይህን ሥራ በርከት ብሎ መሥራት ሥራውን አስደሳችና ቀላል ያደርገዋል።—lv 92-93 አን. 18
-
የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ። ‘አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ሁለት ሳንቲሞች’ እንኳ ከልብ ተነሳስቶ መዋጮ ማድረግ ይሖዋን ያስደስተዋል።—ማር 12:41-44
-
ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ለቲኦክራሲያዊው ሥራ የሚያገለግሉ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በማደሱ ሥራ በፈቃደኝነት መካፈል። በዚህ ሥራ ለመሳተፍ የግንባታ ባለሙያ መሆን አይጠይቅም።